Popular Posts

Sunday, August 5, 2018

የእግዚአብሄርን ድምፅ የመለየት ጥበብ

እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ከእርሱ ጋር እንዲግባባና እንዳይተላለፍ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው እግዚአብሄርን እንዲሰማና ለእግዚአብሄር እንዲመልስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው እግዚአብሄርን እየሰማ እና እየታዘዘ በምድር ያለውን ተልእኮ እንዲፈፅም ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው እግዚአብሄር በልቡና በሃሳቡ እንዳለ ተረድቶ ምድርን እንዲያስተዳድር እንደራሴ እንዲሆነው ነው፡፡
ሰው ሃጢያት ሰርቶ ከመውደቁ በፊት የእግዚአብሄርን ድምፅ በሚገባ ይሰማ ነበር፡፡ ሰው የእግዚአብሄርን ድምፅ ሰምቶ በታዘዘ ጊዜ ሁሉ ስኬታማ ነበር፡፡
እግዚአብሄር ስለሰው ልጆች ሃጢያት ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንዲሰቀል የሰጠንም ምክንያት እግዚአብሄር እንደገና ከሰው ጋር የነበረው የተሳካ መግባባት እንዲመለስ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በክርስቶስ ይቅር ሲልና ሲያድን ከእርሱ ጋር ያለው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲመለስ ፈልጎ ነው፡፡
አሁንም ሰው እንዲሰማውና እንዲረዳው እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር አሁንም ካለማቋረጥ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር አሁንም እንዲሰማ ይፈልጋል፡፡ ሰው የተፈጠረበትን አላማ ግቡን የሚመታው እግዚአብሄር ሲሰማ ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን በምድር ላይ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ ስሙኝ ካልሰማችሁኝ አይሳካላችሁም እያሉ የሚያስጠነቅቁ ብዙ ድምፆች በምድር ላይ አሉ፡፡ በምድር ላይ በምድር ላይ ሊሰሙ የሚሽቀዳደሙ ብዙ ድምፆች ይገኛሉ፡፡
እንድን ድምፅ መከተል ሳይሆን የእግዚአብሄርን ድምፅ መከተል ብቻ ወደ ውጤት ያመጣል፡፡ የእግዚአብሄር ከእነዚያ ድምፆች መካከል የእግዚአብሄርን ድምፅ መለየት ጥበብ ይጠይቃል፡፡
እንደየሰው መዘጃጀት መጠን ነው እንጂ ጌታ ኢየሱስን የሚከተል ሰው ሁሉ የእግዚአብሄን ድምፅ ሊሰማ ይችላል፡፡ የእግዚአብሄርን ድምፅ ሊሰማ የማይችል ኢየሱስን የሚከተል ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄርን ለመድማት በጌታ ህፃን የሆነ ሰው የለም፡፡ ጌታን የተቀበለ ማንም ሰው ጌታን ከተቀበለበት ቅፅበት ጀምሮ የእግዚአብሄርን ድምፅ መስማት ይችላል፡፡
ጌታን የሚከተል ሰው የእግዚአብሄርን ድምፅ የሚሰማው ከተናጋሪው ከእግዚአብሄር የመናገር ችሎታ እንጂ ከሰሚው የመስማት ችሎታ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ለልጆቹ በደረጃቸው በቋንቋቸው በሚገባቸው መንገድ ይናገራል፡፡ ሰው የሚያስተውል ከሆነ እግዚአብሄር ሰውን በሚገባው መንገድ ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።  መጽሐፈ ኢዮብ 33፡14
ሰው የእግዚአብሄርን ድምፅ ሰምቶ ፈቃዱን ለመታዘዝ የሚዘጋጅ ከሆነ እግዚአብሄር ለሰው በሚገባው መንገድ ይናገረዋል፡፡   
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 7፡17
ሰው የእግዚአብሄርን ድምፅ ለመስማት ራሱን የሚያዘጋጅና በእግዚአብሄር ቃል ከባቢ ውስጥ የሚቆይ ከሆነ እግዚአብሄር ይናገራል፡፡ የእግዚአብሄር ድምፅ የእግዚአብሄር ቃል መገለጥ ነውና የእግዚአብሄርን ቃል ከሰማንና ካሰላሰልን ድምፁን መለየት እንችላለን፡፡  
ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡15-17
ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። መዝሙረ ዳዊት 1፡2
እግዚአብሄርን ድምፅ በታላላቅ ነገሮች ውስጥ መጠበቅ የለብንም፡፡ እግዚአብሄር በመንፈስ ቅዱስ ለልባችን ሰላምን ይናገራል፡፡
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። የዮሐንስ ወንጌል 14፡27
እግዚአብሄር በልባችን ሰላም ይመራናል፡፡
በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፡15
እግዚአብሄር ሁልጊዜ ይናገራል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሄርን ድምፅ ለመለየት ጊዜ ልንወስድ ለፀሎት ጊዜ ልንሰጥ የእግዚአብሄርን ድምፅ ለመለየት መለማመድ ይገባናል፡፡
ቆይቼ እግዚአብሔር ደጅ ጠናሁት፥ እርሱም ዘንበል አለልኝ ጩኽቴንም ሰማኝ። መዝሙረ ዳዊት 40፡1
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ያድርጉ!
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ምሪት #ድምፅ #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment