Popular Posts

Saturday, August 18, 2018

መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያንን የመሰረተው ክርስቶስ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የራሱ አጀንዳ የለውም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አላማና ተልእኮ ክርስቶስን ማክበር ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አጀንዳ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሰረተበትን አላማ በቤተ ክርስቲያን ማስፈፀም ነው፡፡
ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል። እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። የዮሐንስ ወንጌል 16፡13-14
የመንፈስ ቅዱስ አላማ የክርስቶስ አላማ በምድር ላይ እንዲፈፀም ማመቻቸት ማደራጀትና መርዳት ነው፡፡
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። የሐዋርያት ሥራ 13፡1-2
የመንፈስ ቅዱስ ስራ ክርስቶስ የሚከብርበትን አገልጋይ በቤተክርስቲያን መሾምና ሃላፊነቱን እንዲወጣ በየእለቱ መርዳት ነው፡፡  
በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። የሐዋርያት ሥራ 20፡28
መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ያለው ማንንም ሰው ለማክበር አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን የሚሰራው ለማንም ሰው ክብር አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያለው ቤተክርስትያን በቃሉ እየኖረች እንደሆነ ለመከታታልና ቃሉን ለማስታወስ እና ለመተርጎም ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በየእለቱ በቤተክርስቲያን የሚሰራው ክርስቶስን ለማክበር ነው፡፡  
የመንፈስ ቅዱስ ተልእኮ ሰዎችን ዝነኛ ማድረግ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ተልእኮ ሰዎች ኢየሱስን እንዲያውቁና እንዲከተሉ ቤተ ክርስቲያንን መርዳት ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ተልእኮ እኛን ህይወታችንን በመቀደስና በመለየት ለሌሎች መልካም ምስክር እንድንሆን በመርዳት ሃጢያተኛን መውቀስ ነው፡፡
እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፤ ስለ ኃጢአት፥ በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም፥ ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ የዮሐንስ ወንጌል 16፡8-10
መንፈስ ቅዱስ በምድር ያለው የወንጌል ተልእኳችንን እለት ተእለት እንድንፈፅም ለመምራትና ክርስቶስን በተሻለ ሁኔታ እንድንሰብክ ለመርዳት ነው፡፡
በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ የሐዋርያት ሥራ 16፡6
የእግዚአብሄርን ቤተክርስቲያን ሙሉ አላማ እንድንረዳ እግዚአብሄር መንፈስን ሰጥቶናል፡፡
መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው። እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡10፣12
የመንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ የመኖር አላማ እኛ ለክርስቶስ ብቻ እንድንኖር ማገዝ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አላማ እውነት የሌለበትን እርኩሰትንና ውሸትን ከቤተ ክርስቲያን መፅዳት ነው፡፡
ጴጥሮስም፦ ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? የሐዋርያት ሥራ 5፡3
መንፈስ ቅዱስ እኛን ከአለም ምኞት ሁሉ አላቅቆ ለእርሱ ብቻ እንድንሆን በቅንአት ይመኛል፡፡
አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል። ወይስ መጽሐፍ፦ በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን? የያዕቆብ መልእክት 4፡4-5
መንፈስ ቅዱስ የራሱ አላማ የለውም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ የጀመረውን ቤተ ክርስቲያን የመመስረት ስራን ለመጨረስ በምድር አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ራሱን ወይም ማንንም ሰው ለማክበር በምድር ላይ የለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ለማክበር ይሰራል፡፡ ማንኛውም የመንፈስ ስራ ከእግዚአብሄር መንፈስ እንደሆነ የምናውቅው ክርስቶስን በማክበሩ ነው፡፡ ክርስቶስን የማያከብር ክብሩን ወደሌላ ወደማንም የሚወስድ መንፈስ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አንድና ብቸኛ አላማ በነገር ሁሉ ክርስቶስን ማሳየትና ማክበር ነው፡፡  
እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። የዮሐንስ ወንጌል 16፡14
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ቤተክርስቲያን #ህብረት #አምድ #መሰረት #ራስ #መሪ #መንፈስቅዱስ #ክብር #አካል #ማታለል #ቤተ ክርስቲያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment