የመንጋ ፍትሕ በእንግሊዝኛው Mob justice የሚባለው ነው፡፡ የመንጋ ፍትሕ በማህበረሰብ ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ህዝብ በመንግስት የፍትህ አካላት ላይ እምነት ሲያጣ ነው፡፡ ፍትህን ያመጣሉ በሚባሉት የመንግስት የፍትህ አካላት በሙስናና በተለያዩ ችግሮች ከመዘፈቃቸው የተነሳ ህዝቡ በእነርሱ ላይ እምነት ሲያጣ ፍትህን በራሱ እጅ ለማምጣት በስሜታዊነት የሚወስደው የተሳሳተ የጥቃት እርምጃ አማራጭ የመንጋ ፍትህ ነው፡፡
የመንጋ ፍትህ እጅግ አደገኛ አካሄድና እና የታለመለትን የፍትህን ጥያቄ በፍፁም ሊመልስ የማይችል ዲሞክራሲንና የህግ የበላይነትን የሚያቀጭጭ ፍትህን የሚያዛባ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
ለዲሞክራሲያዊ ሃገር የህግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ የህግ የበላይነት ማለት ደግሞ ሰው ሁሉ በሀገሪቱ ህግ የሚተዳደርና ማንም ሰው በህግ ከተቀመጠለት ገደብ የማያልፍ ካለፈም በህጉ መሰረት የሚቀጣበት አካሄድ ነው፡፡
የህግ የበላይነት አንዱ መግለጫ የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ነው፡፡ ከሰብአዊ መብቶች አንዱ ደግሞ አንድ ሰው በነፃ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ታይቶ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ጥፋተኛ እንዳልሆነና ነፃ እንደሆነ የሚቆጠርበት የህግ ሽፋን ነው፡፡
አንድ ሰው በተከሰሰበት በማንኛውም ወንጀል በፍርድ ቤት እስኪፈረድበት ድረስ ወንጀለኛ አይደለም ነፃ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው በተከሰሰበት በማንኛውም ወንጀል በፍርድ ቤት እስካልተፈረደበት ድረስ ነፃ ሰው ሆኖ ይኖራል፡፡
ይህ የመንጋ ፍትህ ይህንን የሰውን የሰብአዊ መብት የሚጋፋ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
አንድ ነፃ ፍርድ ቤት የተከሳሹን ክስ ሰምቶ የመከላከያ ሃሳቡን አዳምጦ የቀረቡትን ማስረጃዎች ሰምቶ ውሳኔን ይሰጣል፡፡ ይህ የሚደረገው ማንም ስለተጠረጠረ ብቻ እና ስለተከሰሰ ብቻ ባልሰራው ወንጀል እንዳይቀጣ ለመከላከል ነው፡፡
በመንግስት አሰራር እንኳን መንግስት ራሱ ጠርጥሮ ፣ ራሱ ፈርዶ ራሱ እንዳይቀጣ የመንግስት አካላት በሶስት ክፍሎች ተከፍለዋል፡፡
በዲሞክራሲያዊ ስርአት መንግስት ያለውን ስልጣን በአግባቡ እንዳይጠቀም በሶስት ክፍሎች የተከፈለና ሶስቱ የመንግስት ክፍሎች እርስ በእርሳቸው የሚጠባበቁና የሚተራረሙ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በየደረጃው ያሉ ህግ አውጪ ምክር ቤቶች አሉ፡፡ ህግን ተርጓሚ የመንግስት አካል ፍርድ ቤት አለ፡፡ እንዲሁም ህግን አስፈጸፃሚ ፖሊስና የአቃቢ ህግ አካላት አሉ፡፡
የመንግስት ስልጣን እንኳን በሶስት ክፍሎች የተከፈለበት ምክኒያት መንግስት በአንድ የመንግስት ቢሮ ራሱ ህግ አውጪ ፣ ራሱ ከሳሽ ፣ ራሱ ፈራጅና ራሱ ቀጪ እንዳይሆን ነው፡፡ መንግስት እንኳን በሶስቱ የመንግስት ክፍሎች የተከፈለበት ምክኒያት ከመንግስት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም ህዝቡን ለመከላከል ነው፡፡
ሶስቱ የመንግስት አካላት እርስ በእርሳቸው ይጠባበቃሉ ይተያያሉ ይተራረማሉ፡፡
በመንጋ ፍትህ የህግ አውጪው ፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው በሌሉበት ሁኔታ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው አንዱን ሰው የሚጠረጥሩት ፣ የሚከሱት ፣ የሚፈርዱበትና ፍርዱን የሚያስፈፅሙበት ከሆነ የህግ የበላይነት አይኖርም፡፡ መንግስት ስልጣኑን አላግባብ እንዳይጠቀም በሶስት ዋና ክፍሎች ከተከፈለ በመንጋ ፍትህ ግን የሰዎች ስብስብ በመንግስት የሚፈራው ስልጣንን አላግባበ መጠቀምን ከመፀመ በጣም አሳዛኝና ዘግናኝ ነው፡፡ ይህ አንድ ቡድን የሚያደርገው የመንጋ ፍትህ የህግ የበላይነት ይሸረሽራል ስርአት አልበኝነት እንዲሰፍንና እውነተኛ ሳይሆን ጉልበተኛ የሚኖርባት አገር ያደርጋል፡፡
ከዚህ በፊት በቪድዮ የተለቀቀው በመስቀል አደባባይ ለተቃውሞ በወጡት ሰዎች ላይ የተደረገው መግረፍ እና ማሰቃየት የፍትህ ስርአቱን ያልተከተለ የመንግስት የህግን ስርአት መጣስ ምሳሌ ነው፡፡ የህግ አስፈፃሚው ጥፋተኛ ነው ብሎ የጠረጠረውን ሰው ይዞ ለህግ ተርጓሚው አካል ለፍርድ ቤት ከመስጠት ይልቅ ራሱ ጠርጥሮ ፣ ራሱ ፈርዶ ፣ ራሱ ፍርዱን ያስፈፀመበት ሁኔታ የመንግስት አካላት የስልጣን ድንበራቸውን መጣሳቸውን የሚያሳይ ምሳሌ ነው፡፡
እውነት ነው አስፈፃሚውም አካል ይሁን ህዝብ ራሱንና ሌላውን ለመከላከል የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ፖሊስ ምንም ማድረግ የማይችለውን በእጁ የገባውን ሰውን እንደዚያ ቀጥቅጦ ማሰቃየትና በአካል ላይ ጉዳት ማድረስ ራስን ወይም ሌላውን ከመከላከል መርህ ውጭ ነው፡፡
እንዲሁም በሰኔ 16 በጠቅላይ ሚንስሩ ላይ የሞከረን የቦንብ ጥቃት አደጋ ለመከላከል በህዝቡ የተወሰደው እርምጃ መልካም እና ራስንና ሌላውን ለመከላከል እርምጃ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ነግር ግን ከዚያ በኋላ መኪናን በማቃጠል የታየው የህዝብ ጥቃት የዚሁ የመንጋ ፍትህ ምሳሌ ነው፡፡
በዚያ በሰኔ 16 በህዝቡ የተደረገው የመንጋ ፍትህ በከፋ መልኩ በሻሸመኔ ታይቷል፡፡ ቦንብ ይዟል ተብሎ የተጠረጠረ ሰውን ይዞ ለፍትህ አካላት ከማቅረብንና ፍትህ የራሱን መንገድ እንዲከተል ከመትው ይልቅ ራስ ጠርጥሮ ራስ ፈርዶ ራስ ፍርድን ማስፈፀም ዲሞክራሲንና የህግ የበላይነትን የሚጎዳ የታሪክ ጠባሳ ነው፡፡
እነዚህ አይነት የመንጋ ፍትህ አካሄድ እንዳይደገም የዲሞክራሲ አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ ለመፍጠር የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎችና የመንግስት አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት ህብረተሰቡን የማስተማር ትልቅ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ፖለቲካ #ፀሎት #ፍርድቤት #ህግአውጪ #ህግአስፈፃሚ #ምክርቤት #ፖሊስ #ዲሞክራሲ #ህግተርጉዋሚ #ተቃውሞ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment