Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, August 22, 2018

የንስሃ ጥቅም

ዴሪክ ፕሪንስ የተባሉ የመፅሃፍ ቅዱስ አስተማሪ የእግዚአብሄር ሰው በቤተክርስትያን ውስጥ ትልቅ ችግርን የሚፈጥሩ ሰዎች ንስሃ ያልገቡ ሰዎች ናቸው ይላሉ፡፡ እውነትም በቤተክርስትያን ቆይተው ህይወታቸው ግን እንደሚገባው የማይለወጥ ሰዎች ንስሃ ያልገቡ ሰዎች ናቸው፡፡
ሰው ህይወቱ የሚለወጠውንስሃ በገባው መጠን ብቻ ነው ፡፡
አንዳንድ ሰው ንስሃን አስፈላጊነት ስለማይረዳ በንስሃ የሚፈታውን ችግሩን በሌላ ነገር ለመፍታት ሲሞክር ይንከራተታል፡፡ አንዳንድ ሰው ራሱን አዋርዶ ንስሃ ከሚገባ ይልቅ በመልካም ስራ የህይወቱን ችግር ሊያሸንፍ ሲጣጣር ህይወቱን ይገፋል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስድስተው ንስሃ የሚገባ ሰው ህይወት ነው፡፡ ንስሃ ያልገባ የማንኛውም ሰው መልካም ስራ እግዚአብሄርን አያስደስተውም፡፡
እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል። የሉቃስ ወንጌል 15፡10
አንዳንድ ሰው ደግሞ ይቅርታ ነፃ እንደሆነ ስለማይረዳ ንስሃ ከመግባትና መንገዱን ከመቀየር ይልቅ ለክፉ ስራው በመልካም ስራ ለመክፈል ይፈልጋል፡፡ ለክፉ ስራ የሚከፈል ምንም አይነት መልካም ስራ የለም፡፡
ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል። ትንቢተ ኢሳይያስ 64፡6
ሃጢያትን የሰራ ሰው ያሳዘነው እግዚአብሄርን ነው፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ ንስሃን እንጂ መማለጃን አይቀበልም፡፡ ክፉ ስራ ሰርተን እግዚአብሄርን በመልካም ስራ አናታልለውም፡፡
እንግዲህ አምላካችሁ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ፥ ታላቅ አምላክ ኃያልም የሚያስፈራም፥ በፍርድ የማያደላ፥ መማለጃም የማይቀበል ነውና እናንተ የልባችሁን ሸለፈት ግረዙ፥ ክእንግዲህ ወዲህም አንገተ ደንዳና አትሁኑ። ኦሪት ዘዳግም 10፡16-17
ንስሃ ያልገባ ሰው መልካም ስራ በእግዚአብሄር ፊት እንደመርገም ጨርቅ አፀያፊ ነው፡፡
ንስሃ መግባት ማለት ደግሞ ማልቀስ ማለት አይደለም፡፡ ንስሃ መግባት ማለት ደግሞ በሃጢያት ማዘን ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ንስሃ መግባት ማለት እግዚአብሄርን የሚያሳዝን የተሳሳተ መንገድ መሆኑን አውቆ ቀኝ ኋላ ዙር ብሎ ወደኋላ መመለስ ነው፡፡ ንስሃ ሃሳብን መለወጥ ነው፡፡ ንስሃ የህይወት ለውጥ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 122
እግዚአብሄር የሚቀበለው ንስሃ የገባ ሰውን የንስሃን ፍሬ ነው፡፡ ሰው ንስሃ ከገባ በኋላ መመለሱን የሚያሳየው በመልካም ስራ ነው፡፡
ከንስሃ ውጭ ሌላ የተሳሳተን ሰው ህይወት የሚለውጥ ምንም ነገር የለም፡፡ የሰው ህይወት የሚያርፈው በንስሃ ነው፡፡
የእስራኤል ቅዱስ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በጸጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፤ እናንተም እንቢ አላችሁ፥ ትንቢተ ኢሳይያስ 30፡15
ተመሳሳይ ነገር እያደረግን የይወት ለውጥ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ አዲሱን ወይንጠጅ በአሮጌ አቁማዳ እንደማያደርጉት ሁሉ ህይወታችን በአዲስ መንገድ እንዲጀመር አሮጌው መተው አለበት፡፡
በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። የማቴዎስ ወንጌል 9፡17
ስኬትና ክንውን ያለው ሃጢያትን በመደበቅ ሳይሆን መተው ላይ ነው፡፡ የምንነፃው ስለሃጢያታችንን ንስሃ ስንገባ ብቻ ነው፡፡
ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። መጽሐፈ ምሳሌ 28፡13
በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1፡9
ንስሃ ሃጢያትን ነቅሎ የመጣል ታላቅ ሃይል አለው፡፡ ንስሃ ህይወትን የመለወጥ እና የማደስ ሃይል አለው፡፡
እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል። የሐዋርያት ሥራ 3፡19-20 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ጌታ #ኢየሱስ #ሃሳብ #ቃል #እግዚአብሄር #መንፈስቅዱስ #ንስሃ #መለወጥ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #አእምሮ #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment