Popular Posts

Thursday, August 30, 2018

ከጥበብ የተለየች ቆንጆ

የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት። መጽሐፈ ምሳሌ 11፡22
የኛውም ወርቅ እርያን አንደማያሳምረው ሁሉ የትኛውም የውጭ ውበት የውስጡን ሰውን አያሳምረውም፡፡ ሰው የሚያምረው በውስጡ ነው፡፡ የሰው ውበቱ የውስጥ ማንነቱ ነው፡፡ የሰው ማንነቱ ውስጡ ነው፡፡ የሰው ዋናው ክፍል ባህሪው ነው፡፡ የሰው ዋናው ስብእናው ነው፡፡ በእርያ አፍንጫ ላይ እንዳለ የወርቅ ቀለበት ጥበብ የሌለው ሰው ውበትንም እንዲሁ ግንጥል ጌጥ ነው፡፡  
 ሲጀመር ቁነጅና የተለያየ ነው፡፡ የሰው መልክ እንደ እጁ አሻራ የተለያየ ነው፡፡ የስው የመልክ አይነት እንዲሁ እጅግ ብዙ ነው፡፡ የሰው የቁንጅና መመዘኛም እንዲሁ የተለያ ነው፡፡
የሰው መመዘኛ እንደስሜቱ እጅግ ተለዋዋጭ ከመሆኑ የተነሳ ቁንጅናችን በየሰአቱ የሚለዋወጥ ሁሉ ይመስለናል፡፡ እንዳንድ በጣም ቆንጆ የሆንን አንዳንዴ ደግሞ ያን ያህል ቆንጆ እንዳልሆንን እናስባለን፡፡ አንዳንዴ መስታዎች ከፊታችን እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ ሌላ ጊዜ ግን በመስታዎት ራሳችንን ማየት ሊያስፈራን ይችላል፡፡ የሰው ስሜት በተለዋወጠ ቁጥር ለቁንጅና ያለው መመዘኛም ይለዋወጣል፡፡
ውበት ቋሚ የታመነ ምስክር ሊሆን አይችልም፡፡ ውበት አታላይ ነው፡፡ ውበት ዋናውን የውስጠኛውን ሰው ባለቤቱን ሰው ሊሸፍንብን ይችላል፡፡ ውበትን ተከትለን እግዚአብሄርን የምትፈራውን ሴት ልናጣ እንችላለን፡፡ ውበትን ተከትለን እግዚአብሄርን የማትፈራው ሴት ላይ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ ውበትም ከቆዳ ያለፈ ስለሰው ሁለንተና ሊነግረን አይችልም፡፡
ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። መጽሐፈ ምሳሌ 31፡30
ውበት ዘላቂ አይደለም፡፡ ውበት ከንቱ ነው፡፡ ውበት ጊዜያዊ ነው፡፡ ቁንጅና ያልፋል ይጠፋል፡፡ እግዚአብሄርን መፍራት ግን የማያልፍ የማይጠፋ ሁል ጊዜ ሃብትና ውበት ነው፡፡
የውጭው ውበት እየጠፋ ይሄዳል፡፡ የውስጡ ውበት ግን በጊዜ ብዛት እየታደሰ እየቆነጀ እያማረ ውብ እየሆነ ይሄዳል፡፡
ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡16
እውነተኛ ውበት የልብ ውበት እንጂ የወንድ ቁመና አይደለም
እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 16፡7
ደግነቱ እውነተኛ ውበት ጥበብ ነው፡፡ እውነተኛው ውበት የልብ ባህሪ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ውበት የየዋህነትና የዝግተኝነት ባህሪ ነው፡፡
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡3-4
እውነተኛው ውበት መልካምነት ነው
እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፡9-10
የሰው ውበቱ በውጭ የሚታየው አይደለም፡፡ የሰው ውበቱ በልቡ ያለው ነው፡፡
እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 23፡28
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ውበት #ቁንጅና #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment