Popular Posts

Follow by Email

Monday, August 20, 2018

አዲሱን ዘመን ከጅማሬው የሚያስረጀው

ስለአዲስ አመት ሳናስብ ልባችን በደስታ ይሞላል፡፡ አዲስ አመት አዲስ ነው፡፡ አዲስ አመት አዲስ ተስፋን አዲስ እድልን ይዞ ይመጣል፡፡ አዲስ አመት ይዞ የሚመጣውን አዲስ እድል በሚገባ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡
አዲስ አመት በራሱ አዲስ አይደለም፡፡ አዲስ አመት ከአዲስ ሰው ጋር ካልተገናኘ ዋጋ የለውም፡፡
አዲስ አመት አዲስ ሰው ይጠይቃል
አዲስ አመት ከአዲስ ሰው ጋር ካልተገናኘ አዲስነቱ ይቀራል፡፡  
በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። የማቴዎስ ወንጌል 9፡16-17
ሰው በአዲስ አመት እድሎች በሚገባ ለመጠቀም እግዚአብሄር ያዘጋጀለትን የመዳኛ መንገድ መቀበል አለበት፡፡ ሰው ዳግመኛ መወለድ አለበት፡፡ ሰው አዲስ ፍጥረት መሆን አለበት፡፡
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። አዲስ አመት አዲስ ሰው ይጠይቃል፡፡ አዲስ አመት አዲስ አእምሮ ይጠይቃል፡፡ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡17
በሃጢያቱ ንስሃ ያልገባ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሊታረቅ አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ያዘጋጀለትን የመዳኛ ኢየሰስ ክርስቶስን ያልተቀበለ ሰው የእግዚአብሄር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ዘመን ቢለዋወጥም ህይወትን አያየም፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 3፡36
አዲስ አመት አዲስ አእምሮ ይጠይቃል
ሰው የተፈጠረው ፍፁም ተደርጎ በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ ሰው ሰይጣን ሰምቶ ሲታዘዝ ህይወቱ ተበላሸ፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3
ሰው ህይወቱን ያስረጀው የአስተሳሰሰቡ መበላሸት እንደሆነ ሁሉ የሰውን ህይወት የሚለውጠው አንድ ነገር የአስተሳሰብ መታደስና መለወጥ ነው፡፡  
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡2
የሰው ህይወቱ የሚለወጠው በአእምሮው መታደስ ነው፡፡
አዲስ አመት አዲስ መታዘዝን ይጠይቃል
ሰው ዘመኑ የሚለወጠው በቀንና በጊዜ ሳይሆን በእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ዘመኑ የሚለወጠወ ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ሲለወጥ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ከተሳካ ጳግሜ 5 ቀን ህይወቱ ሊሳካ ይችላል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ከተበላሸ መስከረም 1 ቀን ህይወቱ ሊበላሽ ይችላል፡፡ የሰው ዘመን አዲስ የሚሆነው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ሲሳካ እግዚአብሄርን ሲፈራና እግዚአብሄርን በቃሉ ሲታዝዝ ብቻ ነው፡፡
ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ። ትንቢተ ሚልክያስ 4፡2
ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የዮሐንስ ወንጌል 14፡21፣23
አዲሱ ዘመን በእውነት አዲስ እንዲሆንልን እግዚአብሄር ያዘጋጀውን የመዳኛ መንገድ የኢየሱስን አዳኝነት በመቀበል አዲስ ፍጥረት እንሁን፡፡ አዲስ ፍጥረት የሆንን ሁላችን ደግሞ አእምሮዋችንን በእግዚአብሄር ቃል በማደስ እግዚአብሄር በአዲሱ ዘመን ለህይወታችን ያዘጋጀውን የህይወት ለውጥ አዲስ እድል ለመቀበል እንዘጋጅ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሄርን በመፍራትና ቃሉን በመታዘዝ እግዚአብሄር በአዲሱ ዘመን ያዘጋጀውን እድል እንጠቀምበት፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ሃሳብ #መልካም #መታዘዝ #ቅድስና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #አዲስእድል #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #አስተሳሰብ #አእምሮ #አዲስአመት #ቃል #ልጅ

No comments:

Post a Comment