Popular Posts

Follow by Email

Sunday, August 19, 2018

በትክክለኛው ጊዜ በትክክለኛው ቦታ ላይ እንዳለን የምናውቅበት መንገድ

ኢየሱስን የምንከተል ሁላችን እግዚአብሄርን በፍፁም መከተል የዘወትር ረሃብና ጥማታችን ነው፡፡ በጌታ በኢየሱስ አዳኝነት የእግዚአብሄር ልጆች የሆንን ሁላችን እግዚአብሄር ካሰበልን ነገር ወደኋላ መቅረት ወይም ወደፊት መቅደም በፍፁም አንፈልም፡፡ ጌታን የምንከተል ሁላችን እግዚአብሄር በፈለገን ቦታ ፣ ጊዜና እና ሁኔታ ውስጥ ለመገኘት ዘወትር እንቀናለን፡፡   
የሁላችንም ጥማት ፈቃዱ ብቻ በህይወታችን እንዲሆን ነው፡፡ ረሃባችን እግዚአብሄር በልቡና በሃሳቡ እንዳለ እንዲሁ ማድረግ ነው፡፡ እግዚአብሄር ካሰበው ጊዜ አንድ ሰከንድ መዘግየትም ሆነ መፍጠንም አንፈልግም፡፡ እግዚአብሄር እንድንሆንለት ከፈለገን ቦታ አንድ ሳንቲም ሜትርም መራቅ አንፈልግም፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ከፈለገብን ደረጃ አንድ ደረጃም ማነስ አንፈልግም፡፡ በነገራችን ሁሉ አካሄዳችንን ከእግዚአብሄር ጋር ማድረግ እንፈልጋለን፡፡
ሄኖክም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዓመት ሆነ። ሄኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።  ኦሪት ዘፍጥረት 5፡24
ሁለንተናችንን ለእርሱ መስጠት በሁለንተናችን እርሱን ፈፅመን መከተል የዘወትር ጥማታችን ነው፡፡
ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር እርሱ ግን ያያታል እግዚአብሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ ብሎ ማለ። ኦሪት ዘዳግም 1፡36
ስለዚህ ሁልጊዜ እግዚአብሄር የሚጠብቅብኝ የእድገት ደረጃ ላይ ነኝ? ብለን ራሳችንን ደጋግመን እንጠይቃለን፡፡ እግዚአብሄር በአሁኑ ጊዜ እንዳደርግ የሚፈለግብኝን እያደረግኩኝ ነው ወይ? ብለን ደጋግመን እናወጣለን እናወርዳለን፡፡ እግዚአብሄር በልቡና በነፍሱ እንዳለ እንዲሁ እያደረግኩኝ ነው ወይ ብለን ራሳችንን እናያልንም፡፡
የታመነም ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፥ በልቤም በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፤ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፥ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 2፡35
በእግዚአብሄር ሃሳብ ውስጥ መሆናችንን ካላረጋገጥን በስተቀር በድፍረት ለእግዚአብሄር ሙሉ ለሙሉ ለመኖርና እና ፍሬማ ለመሆን ይሳነናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በፈለገን ቦታ ላይ መሆናችንን ካረጋገጥን በእግዚአብሄር ድፍረታችን ይበዛል ለእግዚአብሄር መንግስት ይበልጥ የሚጠቅሙ ሰዎች እንሆናለን፡፡
1.      እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው
እግዚአብሄር ይወደናል፡፡ እግዚአብሄር የወደደን መልካም ሰዎች ስለሆንን አልነበረም፡፡ እግዚአብሄር ሁሌም ይወደናል፡፡ እግዚአብሄር በምክንያት ስላልወደደን በምክንያት አይጠላንም፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ላይ ያለው አላማ ፍቅር ነው፡፡ ስፋቱ ጥልቀቱ ከፍታው ከመታወቅ የሚያልፈቅውን በእግዚአብሄር ፍቅረ እንድንኖር ተጠርተናል፡፡
ከቅዱሳን ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቅነቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል፥ ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ፥ እስከ እግዚአብሔርም ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3፡18-19
አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። የዮሐንስ ወንጌል 15፡9
2.     እኛ እግዚአብሄር እንዲመራን ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሄር እኛን ሊመራን ይፈልጋል
እግዚአብሄር ለክብሩ ፈጥሮናል፡፡ እግዚአብሄር እንዲመራን እና ከእኛ ጋር በሚገባ ህብረትን ሊያደርግ በመልኩና በአምሳሉ ፈጥሮናል፡፡ እኛ እግዚአብሄር እንዲመራን ከሚፈልገው በላይ እርሱ እኛን ሊመራን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር ሊመራን ይፈልጋል፡፡
ከእኛ የሚጠበቀው ፈቃዱን ለማድረግ መፈለግ ብቻ ነው፡፡
ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፥ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል። የዮሐንስ ወንጌል 7፡17
3.     እኛ እግዚአብሄር እግዚአብሄርን መስማት ከምንችለው በላይ እግዚአብሄር እኛን ይመራናል
እግዚአብሄርን የምንሰማው ጥሩ ሰሚዎች ስለሆንን ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን የምንሰማው እርሱ ጥሩ ተናጋሪ ስለሆነ ነው፡፡ እግዚአብሄር ከተናገረ ሰው መስማት ይችላል፡፡ እግዚአብሄር የሚናገረው ሰው እንዲሰማ በሰው ቋንቋና በሰው ደረጃ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ፈቃድ እየፈለግን እንዳንስተው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ባንረዳው እንኳን በምህረቱ ባጠጋ ስለሆነ እግዚአብሄር የመገፍተር ያህል ፈቃዱ ውስጥ አስገብቶ ራሳችንን እናገኘዋለን እንጂ ከእግዚአብሄረ ጋር አንተላለፍም፡፡
እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ተናገረ፥ እኔም ይህን ብቻ ሰማሁ፤ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፥ መዝሙረ ዳዊት 62፡11
በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል። የራሱንም ሁሉ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ድምፁን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሻሉ እንጂ አይከተሉትም፥ የሌሎችን ድምፅ አያውቁምና። የዮሐንስ ወንጌል 10፡3-5
4.     እግዚአብሄር አይኑን በእኛ ላይ አፅንቷል
እግዚአብሄር በህይወታችን የሚሰራው ማስተማር እና መምራት ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ያስተምረናል ይመራናል በትክክል መከተላችንን አይኑን በእኛ ላይ ያፀናል፡፡ እግዚአብሄር አይተወንም አይጥለንም፡፡ እግዚአብሄ እንደ አይኑ ብሌን ይንከባከበናል፡፡
አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ። መዝሙረ ዳዊት 32፡8
በምድረ በዳ በጥማት፥ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው። ኦሪት ዘዳግም 32፡10
ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ፦ አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ ወደ ዕብራውያን 13፡5
5.     እግዚአብሄር እንድንፈራው ብቻ ሳይሆን በምህረቱም እንድንታመን ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሄር እንድንፈራው ብቻ ሳይሆን ድካማችንን በሚሸፍን በምህረቱ እንድንታመን ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር በሚፈሩት፥ በምሕረቱም በሚታመኑት ይደሰታል። መዝሙረ ዳዊት 147፡11
እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ መዝሙረ ዳዊት 33፡18
6.     እግዚአብሄር በእኛ ደስተኛ ነው
እኛንና እግዚአብሄርን ያጣላን የሃጢያት ግድግዳ ተንዷል፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ የሃጢያት ስርየት ስራ ተደስቷል፡፡ እግዚአብሄር በክርስቶስ ረክቷል፡፡ እግዚአብሄር እኛን የሚያየን በክርስቶስ ነው፡፡
አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። የሉቃስ ወንጌል 12፡32
እግዚአብሄር ድንገት ያልተደሰተበት ነገር ቢኖር ይናገረናል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ከርስቶስ ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን አላፈረብንም፡፡
ስለዚህም ምክንያት፦ ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ በማኅበርም መካከል በዜማ አመሰግንሃለሁ፤ ደግሞም፦ እኔ በእርሱ እታመናለሁ፤ ደግሞም፦ እነሆኝ እኔን እግዚአብሔር የሰጠኝንም ልጆች ሲል ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። ወደ ዕብራውያን 2፡13
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ራዕይ #ምሪት #የእግዚአብሄርአጀንዳ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ምህረት #ምሪት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment