Popular Posts

Friday, August 24, 2018

የአዲስ ዓመት ውሳኔ - ከውድድር ራስን ማግለል

እግዚአብሄር ህይወታችንን እንድናይና እንድናስተካክል ጊዜንና ወቅቶችን ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር ጊዜን በወቅቶች ከፋፍሎ የሰጠን ምክንያቱ ህይወታችንን በየእለቱ ፣ በየሳምንቱ ፣ በየወሩና በየአመቱ እንድናይና እንድናመሰግን እንዲሁም እንድናስተካክል ነው፡፡
እግዚአብሄር ጨለማን የሰጠን አረፍ ብለን የእግዚአብሄርን ስራ እንድናስብ ራሳችንን እንድናይ ለነገው ህይወታችን እንድናቅድ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። መጽሐፈ ኢዮብ 37፡7
እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች ሁሉ ሥራውን ያውቁ ዘንድ፣ እያንዳንዱ ሰው እንዳይሠራ ይገታዋል። መጽሐፈ ኢዮብ 37፡7 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
እግዚአብሄር በአለማ ፈጥሮናል፡፡ ወደዚህ ምድር የመጣነው ወደዚህ አለም ከመምጣታችን በፊት ልንሰራው ያለው ስራ ስለነበረ ነው፡፡ ያንን እግዚአብሄር እንድንሰራ ያቀደውን ስራ ማግኘትና መፈፀም ፍሬያማ ያደርገናል፡፡
እያንዳንዳችን ለተለየ አላማ ተፈጥረናል፡፡ ድጋሚ አላማ ያለው ሰው በምድር ላይ የለም፡፡ እግዚአብሄር ድግግሞሽን አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር ለእንዳንዳችን የተለየ የህይወት አላማ አለው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡10
አንድ አይነት የህይወት አላማ ያላቸው ሁለት ሰዎች በምድር ላይ አይፈጠሩም፡፡
ከሌላው ሰው ጋር መወዳደር ወይም መፎካከር ክስረት የሚሆነው ልንፎካከርው የሚገባ ተመሳሳይ የህይወት አላማ ያለው ሰው በምድር ላይ ስለሌለ ነው፡፡
በምድር ላይ እግዚአብሄርን ያዘጋጀላቸውን የህይወት አላማ የማያውቁ ሰዎች ከመፎካከርና ከመወዳር ውጭ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ አለምን የሚያንቀሳቅሳት ቅናትና ፉክክር ነው፡፡ የእግዚአብሄርን አላማ በህይወታችን ለምንከተለ ለእኛ ግን ፉክክርና ውድድር አይመጥነንም፡፡  
ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፥ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል፤ ወደ ገላትያ ሰዎች 6፡4
ከሌላው ጋር በተፎካከርና በተወዳደርን ቁጥር እግዚአብሄር በህይወታችን ያስቀመጠውን አላማ መፈፀም ያቅተናል፡፡ በተወዳደርና በተፎካከርን ቁጥር እግዚአብሄር የሰጠንንን ስጦታ እግዚአብሄር ያልጠራን ስራ ላይ በማዋል እናባክነዋለን፡፡ በአለም በቅናትና በፉክክር አሸናፊ ለመሆንና ከንቱ ውዳሴን ለመቀበል የሚሮጥ ሰው እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጠውን ሃላፊነት መወጣት ያቅተዋል፡፡
ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡3
ሰው መፎካርና መወዳደር ያለበት እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጠውን ስራ ከግብ በማድረስ ብቻ ነው፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
በአለም ያሉ ሰዎች የእግዚአብሄር የህይወት አላማ በህይወታቸው ስለሌለ በገንዘብ ወይም በኑሮ ትምክት ስለሚኖሩ ሌላውን ለመብለጥ ሁሌ ይሰራሉ፡፡ በአለም ያሉ ሰዎች የሚታዘዙትና የሚከተሉት ጌታ ስለሌላቸው ሌላውን ለመብለጥ በኑሮ መመካት ህይወታቸውን ያባክናሉ፡፡
ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፡15-16
የእግዚአብሄርን ሃሳብ በህይወቱ የተረዳና ከቅናት ነፃ የሆነ ሰው እንኳን ከሌላው ጋር ሊወዳደር ይቅርና የራሱን የህይወት ሃላፊነት ለመወጣት ሮጦ አይጠግብም፡፡
በአዲሱ አመት መወሰን ካሉብን ነገሮች አንዱ እግዚአብሄር በህይወታችን የሰጠንን ስራ መጨረስ እንጂ በምንበላው ፣ በምንለብሰው ፣ በምንኖርበት ቤትና በምንነዳው መኪና ከማንም ከሌላ ሰው ጋር ላለመወዳደር መወሰንን ነው፡፡ የክርስቶስን ስም የተሸከምን ሁላችን በህይወትና በአገልግሎት ስኬታማ ለመሆን ከከንቱ የአለም ውድድር በፈቃዳችን ራሳችንን ማግለል ይኖርብናል፡፡
አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡8
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ቅናት #ክርክር #ውድድር #አላማ #ፉክክር #ማሰናከያ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment