Popular Posts

Friday, August 24, 2018

9ኙ የፍቅረ ንዋይ ምልክቶች

ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡10
ገንዘብ በንግዱ አለም እንደ መግባቢያ ቋንቋ ነው፡፡ ገንዘብ በንግዱ አለም የልውውጥ መሳሪያ ነው፡፡ አሁን የምናውቅው ሳንቲምና የብር ኖት ባልነበረበት ጊዜ ሰዎች የሚለዋወጡት በአሞሌ ጨው እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ገንዘብ በራ ክፉ አይደለም፡፡ ገንዘብን የምናይበት አስተያየት ግን ክፉም መልካምም ሊሆን ይችላል፡፡ ለገንዘብ ያለን ግምት ሊሳሳት ይችላል፡፡ ገንዘብ የክፋት ስር አይደለም፡፡
ገንዘብን መውደድ ግን የክፋቶች ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ ከገንዘብ ጋር ያለ የተሳሳተ ግንኙነት የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ ከገንዘብ ጋር በማያመች አካሄድ መጠመድ ክፋትን ሁሉ ያሰራናል፡፡  ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ሲዛባ ከእግዚአብሄና ከሰው ጋር የለን ግንኙነት ሁሉ ይዛባል፡፡
ሰው እግዚአብሄርን እንዲወድ እንጂ ገንዘብን እንዲወድ አልተፈጠረም፡፡ ሰው በልቡ ለእግዚአብሄር ስፍራ እንዲሰጥ እንጂ ለገንዘብ በልቡ ስፍራ እንሰዲሰጥ አልተፈጠረም፡፡ ሰው እግዚአብሄርን ጌታው እንዲያደርግ እንጂ ገንዘብን ጌታ እንዲያደርግ አልተሰራም፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር እንዲገዛ እንጂ ለገንዘብ እንዲገዛ ወይም ደግሞ ለሁለቱም እንዲገዛ አልተፈጠረም፡፡ 
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። የማቴዎስ ወንጌል 6፡24
ሰው ባንድ ጊዜ ሁለቱንም ለመውደድ አቅም የለውም፡፡ ሰው ገንዘብን ሲወድ እግዚአብሄርን መውደድ ያቅተዋል፡፡ ሰው ገንዘብንም ሰውንም መውደደ አይችልም፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርንና ሰውን እንዲወድ ስለሆነ የገንዘብ ፍቅር የሰውን የህይወት አላማ ያስታል፡፡
ሰው በእግዚአብሄር ክብር የተፈጠረው እግዚአብሄርንና ሰውን እንዲያገልግል እንጂ ገንዘብን እንዲያገለገል አይደለም፡፡
የገንዘብ ፍቅር ማንንም ሰው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይብዛም ይነስም ሊይዝ የሚችል ፈተና ነው፡፡ የገንዘብ ፍቅር ለድሃ እና ለሃብታም ብቻ የተለየ አይደለም፡፡ ድሃ የገንዘብ ፍቅር ሊኖርበት ይችላል ሃብታምም እንዲሁ የገንዘብ ፍቅር ሊኖርበት ይችላል፡፡ ድሃም ከገንዘብ ፍቅር ከምኞት ራሱን ጠብቆ ሊኖር ይችላል፡፡ ሃብታም በገንዘቡ ላለመያዝ ራሱን ሊጠብቅ ይችላል፡፡
ሰው የገንዘብ ፍቅር እንዳለበት የሚያሳዩ ምልክቶችን እንመልከት፡፡
1.      ገንዘብ ሲኖረን የምንደሰት ሳይኖረን የምንከፋ ከሆንን የገንዘብ ፍቅር እንዳለብን ምልክቱ ነው
የሰው መኖሪያ እግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ግን የምኖረው በገንዘብ ነው ብሎ ካሰበ የማይገባውን እያደረገና ራሱን ከእግዚአብሄር ልጅነት ደረጃ እያዋረደ ነው፡፡
መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፥ የዘላለምም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፤ ጠላትህን ከፊትህ አውጥቶ፦ አጥፋው ይላል። ኦሪት ዘዳግም 33፡27
ሰው የሚኖረው በገንዘብ ሳይሆን በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡4
ሰው የሚኖረው በክርስቶስ ፍቅር ነው፡፡
አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። የዮሐንስ ወንጌል 15፡9
2.     ሰውን የምንቀርበው ለመጥቀም ሳይሆን ለመጠቀም ከሆነ የገንዘብ ፍቅር እንዳለብን ምልክቱ ነው፡፡
ቆም ብለን በአካባቢያችን ያሉትን ሰዎች እንመልከት፡፡ የቀረብናቸውን ሰዎች የቀረብናቸው የልብ መነሻ ሃሳባችን ሰዎችን ልንጠቅማቸው ነው ወይስ ልንጠቀምባቸው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የገንዘብ ፍቅር እንዳለብን ወይም እንደሌለብን ያመለክተናል፡፡
እንደ እርሱ ያለ፥ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፥ ማንም የለኝምና፤ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፥ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡20-21
3.     ገንዘብ ላለው ሰው ልዩ አያያዝ ካሳየንና ገንዘብ የሌለውን ሰው ችላ ካልን በገንዘብ ፍቅር እንደተያዝን ማረጋገጫው ነው፡፡
ሰውን የምናከብርው ወይም የምንቀው ባለው የገንዘብ መጠን ከሆነ የገንዘብ ፍቅር ይዞናል ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ያለውን እያከበረን ገንዘብ የሌለውን እየናቅን የገንዘብ ፍቅር የለብንም ብንል እንዋሻለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፡፡ ሰውን እንደ ሰውነቱ ካላከበርንና ገንዘብ ላለው ትኩረታችን ከጨመረ ገንዘብ ለሌለው ደግሞ ትኩረታችን ከቀነሰ የገንዘብ ፍቅር እንደያዘን ከዚህ በላይ ማረጋገጫ መፈለግ የለብንም፡፡  
የወርቅ ቀለበት ያደረገና የጌጥ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢገባ፥ እድፍ ልብስም የለበሰ ድሀ ሰው ደግሞ ቢገባ፥ የጌጥ ልብስም የለበሰውን ተመልክታችሁ፦ አንተስ በዚህ በመልካም ስፍራ ተቀመጥ ብትሉት፥ ድሀውንም፦ አንተስ ወደዚያ ቁም ወይም ከእግሬ መረገጫ በታች ተቀመጥ ብትሉት፥ ራሳችሁን መለያየታችሁ አይደለምን? የያዕቆብ መልእክት 2፡2-3
4.     ገንዘብ ባገኝ ህይወቴ ይለወጣል ብለን የምናስብ ከሆነ በገንዘብ መውደድ ወጥመድ ውስጥ ወድቀናል፡፡
በገንዘብ ፍቅር የሚያዘው ሃብታም ብቻ አይደለም፡፡ የገንዘብ ፍቅር ፈተና የድሃ ብቻ አይደለም፡፡ የገንዘብ ፍቅር ሃብታምና ደሃ አይለይም፡፡ ሃብታም ያለውን ገንዘብ እንዴት እንደሚይዘው በማየት የገንዘብ ፍቅሩ ይለካል፡፡ ድሃ የሌለውን ገንዘብ እንዴት እንደሚመኝ በማየትና ገንዘብን ለማግኘት የሚሄድበትን አካሄድ በማየት የገንዘብ ፍቅሩ ይታያል፡፡
ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡9
ገንዘብ የሌለው ሰው ገንዘብ ቢኖረኝ ህይወቴ ይለወጣለ ብሎ ካሰበ ስቷል፡፡ የሰውን ህይወት የሚለውጠው የእግዚአብሄር አሰራር እንጂ ገንዘብ አይደለም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ካልረዳው ገንዘብ ስላለው ምንም አያመጣም፡፡ ሰው እግዚአብሄር ከረዳው ገንዘብ ባይኖረውም ምንም አይጎድልበትም፡፡
ሰው የህይወት ቁልፉ ባለጠግነት ጋር ነው ብሎ ካሰበ በገንዘብ ፍቅር ወጥመድ ውስጥ ወድቋል፡፡ የህይወት ስኬት ቁልፍ ያለው የሁሉም ዳኛ የሆነው እግዚአብሄር ጋር እንጂ ባለጠግነት ጋር አይደለም፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤
ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-24
ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጣቸው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሳቸው ዘንድ፥ ችግረኛውን ከመሬት ያስነሣል፥ ምስኪኑንም ከጉድፍ ያስነሣል፤ የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፥ በእነርሱ ላይም ዓለምን አደረገ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2፡8
5.     ደሃን የምንጠላ ከሆንንና ድህነትን የምንፈራ ከሆንን በገንዘብ ፍቅር ተነድፈናል ማለት ነው፡፡
እግዚአብሄር በክርስቶስ ሁሉን ነገር ሰጥቶን ሳለ አሁንም ደሃ እንደሆንን የሚሰማን ከሆነ የገንዘብ ፍቅር አለብን ማለት ነው፡፡ ከድሃ ጋር መገናኘት ድህነቱን የሚያካፍለን ከመሰለን በገንዘብ ፍቅር ወጥመድ ውስጥ ወድቀናል፡፡ ድህነትን የምንፈራ ከሆነና ሰው የሚኖረው በእግዚአብሄር ፀጋ እንደሆነ ካልተረዳን በገንዘብ ፍቅር ህይወታችነ ተይዞዋል፡፡ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ የወጣ ሰው ድህነት ምንም እንደማይቀንስ ስለሚያውቅ ድህነትን አይፈራም፡፡ የገንዘብ ፍቅር የሌለበት ሰው ሁሉን በሚያስችል በክርስቶስ ሁሉን እንደሚችል እንጂ ድህነትም ሃብትም ምንም እንደማያመጡ ልካቸውን ያወቀና የናቃቸው ሰው ነው፡፡ ድህነትን እንዳይመጣብን በመፍራትና የማይገባንን ነገር ሁሉ ማድረግ  የገንዘብ ፍቅር ምልክት ነው፡፡ ድህነትን መፍራትና ከእግዚአብሄር ነገር በላይ ማክበር የገንዘብ ፍቅር ምልክት ነው፡፡
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13
6.     ፀሎታችን በህይወት ለውጥ እና በአሳድገኝ ሳይሆን በገንዘብ ስጠኝ ከተሞላ የገንዘብ ፍቅር እንዳለብን ምልክቱ ነው፡፡
በፀሎታችን ክርስቶስን እንድንመስል ካልተጋንና ገንዘብ የህይወት ጥያቄያችንን ሁሉ ይመልሳል ብለን ካሰብን በገንዘብ ፍቅር ተይዘናል፡፡ እግዚአብሄርን የመምሰል ባህሪዎች በህይወታችን እንዲበዙ የምናስብና የምንሰራ ካልሆንን ፀሎታችን የተሞላው ገንዘብ ስጠኝ ላይ ከሆነ በገንዘብ ፍቅር ሃሳብ ተታልለለናል፡፡
እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2፡6-7
7.     ሰውን በሙያችንና በስጦታችን ከማገልገል ይልቅ ከሰው ስለምናገኘው ገንዘብ ይበልጥ ካሰብን የገንዘብ ፍቅር በልባችን አለ ማለት ነው፡፡
ሰውን አገልግሎታችን እንደሚገባው እንደ ክቡር ፍጥረት ሳይሆን እንደ መጠቀሚያ ብቻ የምናየው ከሆንን በገንዘብ ፍቅር ተይዘናል ማለት ነው፡፡ ትኩረታችን መጥቀም ላይ ሳይሆን በእኛ መጠቀም ላይ ከሆነ በገንዘብ ፍቅር ተንድፈናል ማለት ነው፡፡ የምናደርገውን አገልግሎት የምናደርገው በገንዘብ ማግኘት አላማ ላይ ከሆነ በገንዘብ ፍቅር ወጥመድ ውስጥ ወድቀናል ማለት ነው፡፡ ከፍ ያለ ገንዘብ ለማግኘት ብለን ራሳችንን የምናካብድና አገልግሎታችንን የምናወሳሰብ ከሆነ የገንዝብ ፍቅር እንዳለብን ምልክት ነው፡፡
እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። የማቴዎስ ወንጌል 23፡14
8.     ለገንዘብ ብልን ከዋሸን የገንዘብ ፍቅር አለብን ማለት ነው፡፡
ለገንዘብ ብለን የልጅነት ክብራችን የምንጥል ከሆንን ለገንዘብ ብለን አቋማችንን የምንለዋውጥ ከሆንንነ በገንዘብ ፍውቅር ተይዘናል፡፡ ለጥቅም ብለን ሰውን ከካድን የገንዘብ ፍቅር አለብን ማለት ነው፡፡ ለገንዘብ ፍቅር የሰውን ፍቅር ካጣጣልነና ለግንኙነት ያለን ክብር ከወደቀ በገንዘብ ፍቅር ተይዘናል፡፡ ከወዳጅነት ይልቅ ጥቅም ከበለጠብን የገንዘብ ፍቅር ይዞናል ማለት ነው፡፡
ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ወደ ዕብራውያን 12፡16
የህብረትን ዋጋ የምናጣጣል ከሆነና ለጥቅም ብለን ከወዳጅ መለየት የሚቀልብን ከሆንን በገንዘብ ፍቅር ተይዘናል፡፡
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። መጽሐፈ ምሳሌ 18፡1
9.     ለእግዚአብሄር መንግስትና ፅድቅ ከማሰብ ይልቅ ስለኑሮ የምንጨነቅ ከሆንንነ በገንዘብ ፍቅር ተይዘናል፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡31-33
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ገንዘብ #ብር #ብልፅግና #ስኬት #ስምረት #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment