Popular Posts

Wednesday, July 11, 2018

እግዚአብሔር በመሥዋዕት ደስ ይለዋልን?

ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:22
እግዚአብሄር ድሃ አይደለም የሚያስፈልገውን ነገር አናቀርብለትም፡፡ እግዚአብሄር የጎደለው አይደለም የሚጎድለውን አናሟላለትም፡፡
የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፥ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው። ብራብም ለአንተ አልነግርህም፥ ዓለምና ሞላው የእኔ ነውና። የፍሪዳውን ሥጋ እበላለሁን? የፍየሉንስ ደም እጠጣለሁን? መዝሙረ ዳዊት 50:10-13
እግዚአብሄር እቅድ የሚያወጣለት ሰው አልፈለገም፡፡ እግዚአብሄር አማካሪ አላስፈለገውም፡፡ እግዚአብሄር ምክር የሚሰጠው ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር አቅድ የሚያወጣለት ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር ለእርሱ የሚያስብለት ሰው አይፈደልግም፡፡
ምድር ከመፈጠርዋ በፊት እግዚአብሄር ምድርን ለአላማው ፈጠረ፡፡ እኛ ከመፈጠራችን በፊት ለአላማ ተፈጥረናል፡፡ እግዚአብሄር ስለምድር እቅድ አለው፡፡ እግዚአብሄር ስለምድር የወደፊት ሁኔተ የሚያማክረው ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአበሄር ስለእኛ ህይወት ምክርን የሚለግሰው ሰውን አልፈለገም፡፡
የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?፡13-14
የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ወደ ሮሜ ሰዎች 11፡34-35
ሰው በራሱ አነሳሽነት እግዚአብሄርን ሊያገለግልበት የሚፈልገውን መንገድ እግዚአብሄር አይወደውም፡፡ ሰው በራሱ አነሳሽነት እግዚአብሄርን ሊያስደስት የሚሄድበትን መንገድ እግዚአብሄር አይፈልገውም፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ለማገልገል መሞከር ባዶ ሃይማኖት ነው፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ለማስደሰት መሞከር ሞኝነት ነው፡፡ ሰው በራሱ መንገድ እግዚአብሄርን ደስ ለማሰኘት መሞከር የእግዚአብሄርን አዋቂነት አለመረዳት ነው፡፡
እግዚአብሄር የራሱ መንገድ አለው፡፡ እግዚአብሄር ሊመለክ የሚፈልገው በራሱ መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንድታስደስቱት የሚፈልገው በራሱ መንገድ ነው፡፡
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው መሪ ፈልጎ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ታዛዠ ፈልጎ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አዲስ ነገር አንዲፈጥርለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ያዘዘውን እንዲያደርግ ነው፡፡
በራሳችሁ አነሳሽነት ለእግዚአብሄር ከምታደርጉለት ነገር በላይ ያዘዛችሁን ነገር ብታደርጉ ይበልጥበታል፡፡ ለእግዚአብሄር ትልቅ ነገር ከምታደርጉለት ያዘዛችሁን ትንሽዋን ነገር ብታደርጉለት ይመርጣል፡፡ ለእግዚአብሄር ልዩ ነገር ከምታደርጉለት እርሱ እንድታደርጉለት የፈለገውን ያንኑ ነገር ብታደርጉለት ይሻለዋል፡፡ ለእግዚአብሄር መልካም የሚመስለውን ነገር ከምታደርጉ እርሱ ያዘዘውን ነገር ብታደርጉ ይመረጣል፡፡
ሳኦል እግዚአብሄር ሲልከው ከብቶቹን ሁሉ ግደል ምንም ነገር እንዳታስቀረ ሁሉን አጥፋ ብሎ ነው፡፡ ሳኦል ግን ጠቢብ የሆነ መሰለው፡፡ ሳኦል ግን ከእግዚአብሄር በላይ አስተዋይ የሆነ መሰለው፡፡ ሳኦል ግን ከእግዚአብሄር የተሻለ ሃሳብ ያገኘ መሰለው፡፡ ሳኦል ግን አንድ አዲስ ሃሳብ መጣለት፡፡ ሳኦል ግን እግዚአብሄርን ማስደነቅ ፈለገ፡፡ ስለዚህ ሳኦል ለእግዚአብሄር የሚሰዋውን መርጦ በማስቀረት አታድርግ የተባለውን ነገር አደረገ፡፡ ሳኦል እግዚአብሄር ባልጠየቀው ነገር ሊያስደስተው ፈለገ፡፡
በዚህ አግዚአብሄር ጎሽ አላለውም፡፡ በዚህ እግዚአብሄር ተቆጣ፡፡ እግዚአብሄርን አለመታዘዝ እንደሟርተኛ ሃጢያት እንደሆነ እግዚአብሄር በነቢዩ ተናገረ፡፡
ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:፡23 
አሁንም ብዙ ሰዎች እግዚአብሄር እንዲያደርጉ የጠየቃቸው ነገር ቀላል ሆኖባቸዋል፡፡ ምንም ቀላል ቢመስል እግዚአብሄር የተናገረህን ከማድረግ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አሁንም እግዚአብሄር የፈለገባቸውን ትተው የተሻለ ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም ብዙዎች እግዚአብሄርን ከመታዘዝ ይልቅ መስዋእት በማቅረብ እግዚአብሄርን ሊያስደንቁት የሚጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ አሁንም እግዚአብሄርን ከመታዘዝ ይልቅ በራሳቸው መንገድ እግዚአብሄርን ለማገልገል በመሞከር ህይወታቸውን በከንቱ የሚያባክቡ ሰዎች አሉ፡፡
አልሁም፦ ቃሌን ስሙ፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 11፡4
እግዚአብሄር ሰው አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ሰርፕሪዝ አይደረግም፡፡ እግዚአብሄር ሰርፕራዝ የሚያደርገው ሰው አይፈልግም፡፡ እግዚአብሄር የሚፈልገው ያለውን የሚሰማና የሚያደርግን ሰው ነው፡፡
ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15:22
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#የእግዚአብሄርምክር #የእግዚአብሔርፈቃድ #እግዚአብሔር #እንደተፃፈ #ማታዘዝ #ዓመፀኝነት #ምዋርተኛ #ኃጢአት #እልከኝነትም #ጣዖትንና #ተራፊም #ማምለክ  #መባ #መሥዋዕት ##እምነት #የሰውአሳብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment