ሰው በእግዚአብሄር አምሳል ተፈጥሮአል፡፡ ሰው ለእግዚአብሄር ክብር ተፈጥሯል፡፡ ሰው የተፈጠረበትን አላማ አግኝቶ ካልፈፀመው ህይወቱን ያባክናል፡፡ ሰው እግዚአብሄር ለእርሱ ያለውን አላማ አግኝቶ ከፈፀመው ግን በህይወት ይሳካል፡፡ ሰው እግዚአብሄር በህይወቱ ሊሰራ ያለውን አይቶ ከተባበረ ከእግዚአብሄር ጋር በመስራቱ ውጤታማ ይሆናል፡፡
ስለዚህ ነው ሰው ራእይ ያስፈልገዋል የምንለው፡፡ ሰው ራእይ ከሌለውና የእግዚአብሄርን አላማ በህይወቱ ካላገኘ በከንቱ ይተጋል፡፡
ራእይ ባይኖር ሕዝብ መረን ይሆናል፤ ምሳሌ 29፡18
እግዚአብሄር ካልመራን በስተቀር ለእግዚአብሄር ብለን የምናደርጋቸው ሁሉ እግዚአበሄር አይቀበላቸው፡፡ እግዚአብሄር የሃሳብ እጥረት የለበትም፡፡ እግዚአብሄን በራእይ አንረዳውም፡፡ እግዚአብሄር ህይወታችን በምን መንገድ መሄድ እንዳለበት እቅዱ አለው፡፡
ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም። ኤርምያስ 29፡11
በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም። ዮሃንስ 1፡1-5
በመጀመሪያው ቃል ወይም ራእይ ነበረ
ምንም ባልነበረ ጊዜ ቃል ነበረ፡፡ ሁሉን የሚያመጣው ራእይ ስለሆነ ምንም ሳይኖር የሚቀድመው ራእይ ነው ፡፡ በራሳችን አነሳሽነት የሆነ ቦታ እየሄድን እግዚአብሄርን እግረመንገዳችንን ከመንገድ ላይ የምንጭነው ነገር አይደለም፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ተጠቅሞ መሄድ የሚፈልግበት የራሱ እቅድ አለው፡፡ ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት የሚቀድመው የእግዚአብሄርን ፈቃድ መፈለግ ነው ወይም ራእይን መቀበል ነው፡፡ ምንም ነገር ለማድረግ ከመፈለጋችን በፊት ራእይን መፈለግ አለብን፡፡ ምክኒያቱም ነገሮች በእግዚአብሄር የሚሆኑት በራእይ ነው፡፡
ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ
ራእይ አውጥተን አውርደን የምንቀርፀው ሳይሆን ከእግዚአብሄር የምንቀበለው ነው፡፡ የእኛ የህይወት ንድፋችን ያለው በእግዚአብሄር ዘንድ ነው፡፡ ራእይ ከእግዚአብሄር ይገኛል እንጂ ከሁኔታዎች አይገኝም፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንደፈጠረንና ለምን እንደሰራን ስለሚያውቅ ራእይን ሊሰጠን የሚችው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሚደግፈው ራእይ ከሰዎች ፣ ከሁኔታዎች ፣ ከሃሳባችንና ከምኞታችን አይገኝም፡፡
ቃልም እግዚአብሔር ነበረ
ራእይ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ቃልን ያዝነው ማለት እግዚአብሄርን ያዝነው እንደማለት ነው፡፡ እንዲሁም ራእይ አለን ማለት የእግዚአብሄር ሙሉ እርዳታ ከእኛ ጋር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ራእይን ወይም የእግዚአብሄርን ፈቃድ በተከተልንበት የህይወታችን ክፍል በእግዚአብሄር ሙሉ የውክልና ስልጣን የምንመላላስ እንሆናለን፡፡ እግዚአብሄር ሃላፊነትን በሰጠን አካባቢ ሙሉ ስልጣን አለን፡፡ ራእይ በተቀበልንበት የእግዚአብሄርን አላማ ባወቅንበት የህይወታችን ክፍል ሁሉ ሰይጣንም ፣ ሁኔታዎችም ፣ ሰዎችም ፣ ሊያቆሙን አይችሉም፡፡
በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። ኢያሱ 1፡5
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን የእግዚአብሄር ሙሉ የውክልና ስልጣን ስለሚያስፈፅሙ አማልክት የሚላቸው፡፡
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ ዮሐንስ 10፡34-35
ሁሉ በእርሱ ሆነ
እግዚአብሄር ፈቃዱን በሙሉ ስለሚደግፍ ራእይ ሁሉንም ያመጣል፡፡ ራእያችን ምግባችን ነው ፣ ራእያችን ልብሳችን ነው ፣ ራእያችን እርካታችን ነው ፣ ራእያችን ውበታችን ነው ፣ ራእያችን ዝናችን ነው ፣ ራእያችን ሙላታችን ነው ፣ ራእያችን ደስታችን ነው ፣ ራእያችን ሞገሳችን ነው፡፡ ራእያችንን ተከትለን የሚጎድልብን መልካም ነገር አይኖርም፡፡
በእርሱ ሕይወት ነበረች
የእግዚአብሄር ህይወት የሚፈሰው በራእያችን ውስጥ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ህይወት ማስተላለፍ ከፈለግን ከእግዚአብሄር ስለህይወታችን ያለውን አላማ መግኘትና የእግዚአብሄርን እቅድ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ በራእያችን ስንሄድ ህይወትን እንሸከማለን፡፡ በራእያችል ስንኖር ህይወትን እናካፍላለን፡፡ በራእይ ስንኖር ህይወት ይሆንልናል ህይወትም ይበዛልናል ህይወትንም እናካፍላለን፡፡ እኛም ሆነ የምናገለግላቸው ሰዎች እውነተኛውን ህይወት ማጣጣም የሚችሉት በራእይ ስንኖር ነው፡፡
ከሆነውን አንዳች ያለእርሱ አልሆነም
ትርጉም ያለው ነገር ማድረግ ካለብን በራእይ ነው፡፡ ካለ ራእይ ምንም ነገር አይሆንም፡፡ ካለ ራእይ ዘላለማዊ ነገር ሊደረግ አይችልም፡፡ ካለ ራእይ እውነት ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ የእግዚአብሄርን ነገር ማድረግ ካለብን በራእይ ብቻ ነው፡፡
ህይወትም የሰው ብርሃን ነበረች
ሁላችንም እግዚአብሄር እንዲጠቀምብን እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሄር ሆይ ተጠቀምብን የሚለው የልባችን የዘወትር ጩኸት ነው፡፡ ለሰዎች ብርሃንን የምናካፍለው የእግዚአብሄን ህይወት በማካፈል ነው፡፡ ህይወት ያለው ፣ የሚሰራ ፣ የሚያድግና የሚበዛ አገልግሎት ለማገልገል ራእይ ወሳኝ ነው፡፡ ራአይ ካለን ህይወት ይኖረናል፡፡ ራእይ ካለን እንደዘር የሚሰራ ፣ የሚበዛና ፣ የሚያሸንፍ ነገር ይኖረናል፡፡
ብርሃንም በጠለማ ይበራል
ጨለማ ያለበትን የሚያውቀው እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ብርሃንን ሲሰጠንና ፈቃዱን ሲገልጥልን ብቻ ነው በጨለማ ላይ ብርሃንን ማብራት የምንችለው፡፡ የእግዚአብሄርን የፈቃዱን እውቀት ራእይን ስናገኝ ብርሃንን ለሰዎች እናስተላልፋለን፡፡ ሰዎችን ላስጨነቃቸው ጨለማ ላይ ብርሃን ፣ ለድካማቸው ብርታት ፣ ለበሽታቸው መድሃኒት ፣ ለውድቀታቸው መነሳትና ለሞታቸው ህይወት እናካፍላለን፡፡
ጨለማም አላሸነፈውም
ጨለማን ለማሸነፍ መታገል አይጠይቅም ፡፡ ለጨለማ ብርሃንን ማብራት ብቻ በቂ ነው፡፡ ብርሃንን ሊቋቋም የቻለ ጨለማ እንደሌለ ሁሉ ራእይን ሊቋቋም የሚችል አንድም ሃይል ከሰማይ በታች የለም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #እይታ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ቃል #አሸናፊ #አማልክት #የእግዚአብሄርእቅድ #የእግዚአብሄርፈቃድ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment