Popular Posts

Friday, August 6, 2021

ከዘር ማንዘር ለሚመጣ መርገም ፍቱን መድሃኒቱ


ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ በተቀበለ ሰው ላይ መርገም ሊሰራበት ወይንም ደግሞ ከዘር ማንዘር ሊተላለፍበት ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ በጥቂት ቃላት ለመመለስ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡

እንደፈለግነው ያልተለወጠውን የህይወታችን ክፍል አይተን "እንዴ መርገም አለብኝ እንዴ?" ብለን እንጠይቅ ይሆናል፡፡ ሰዎችም ህይወታችንን አይተው "ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ መርገም አለበት እንዴ?" ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡

አያቶቻችን ለሰሩት ሃጢያት እኛ ዋጋን እንከፍላለን የሚለው አነጋገር አያስኬድም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ የህይወት ስኬታችን የእግዚአብሄርን ቃል በመስማታችንና በመታዘዛችን ላይ ሳይሆን በአያቶቻችንና በቅድመ አያቶቻችን ፅድቅና ሃጢያት ላይ ብቻ ይደገፍ ነበር፡፡

ነገር ግን ሊሰርቅ ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ስለሌላ የማይመጣው ሰይጣን ቅድመ አያቶቻችንን ያጠቃበትን ጥቃት በእኛ ላይ አይሰነዝርም ማለት ግን ሞኝነት ነው፡፡ ጠላት ዲያቢሎስ ከቅድመ አያቶቻችን ያገኘውን አምልኮ ከእኛ ለማግኘት አይመኝም ማለት ግን አይቻልም፡፡

የኢየሱስ ተከታዮች ብንሆንም ባንሆንም ቅድመ አያቶቻችንን ሲዋጋ የነበረው መንፈስ እኛንም በዚያው አኳሃን ይዋጋናል፡፡

በምንም አኳሃን ይዋጋን መፍትሄው ምንድነው የሚለውን ካወቅን ከብዙ ጭንቀት እናርፋለን፡፡

መርገም የሚለውን በምንም አቅጣጫ እንረዳው በሰይጣን ውጊያም ሆነም አልሆነም በህይወታችን እድገት ባላሳየንበት አቅጣጫ እድገት ለማሳየትና ለመለወጥ መፍትሄው ምንድ ነው ብንል መልሱ የእግዚአብሄርን ቃል መጠበቅ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል እየጠበቅን ከሆንን ደግሞ መርገም አለብኝ የለብኝም ብሎ ከመጨነቅና ወዲህ ወዲያ ብሎ ቅፅበታዊ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የእግዚአብሄርን ቃል በመጠበቅ መቀጠል ብቸኛ መፍትሄ ነው፡፡

ተግዳሮታችን መንፈሳዊም ይሁን አይሁን የእግዚአብሄርን ቃል በመፈልግና በመጠበቅ የማይፈታ ምንም አይነት የሰው ልጆች ጥያቄ እንደሌለ ማወቅ ይገባናል፡፡

በእርጋታ የእግዚአብሄርንም ቃል ከተከተልን ይዘግይም ይፍጠንም የማይሰበር ምንም አይነት ችግር የለም፡፡

የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራውያን 4፡12

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.dinsa.37/

ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የመንፈስፍሬ #ፍቅር #ሰላም #ደስታ #ዘር #መርገም #ባህሪ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #የእግዚአብሄርህይወት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #በጎነት #የዋሃት #ራስንመግዛት #ትግስት #መሪ

 

No comments:

Post a Comment