Popular Posts

Tuesday, July 31, 2018

የሁለቱ አለማት ጉዞ

በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡8-9
ክርስትና የሁለት አለም ጉዞ ነው፡፡ ክርስትና በአንድ በኩል በሰማያዊ ስፍታ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የመባረክ ስልጣን ነው፡፡ በሌላ በኩል ክርስትና የዚህ አለም ገዢ በሚገዛበት በምድር ላይ በተግዳሮት የመኖርና የእግዚአብሄርን መንግስት የማስፋት የእንግዳ አለም ተልእኮ ነው፡፡ በሰማያዊ ስፍራ መባረክና የህይወት ተግዳሮት ሁለቱ እርስ በእርሳአቸው የሚቃወሙ ሃሳቦች አይደሉም፡፡ ተግዳሮቱን በአሸናፊነት የምንወጣው በሰማያዊ ስፍራ ስለተባረክን ነው፡፡ ተግዳሮቱ ሁሉ የመጣብን ተግዳሮቱን ተቋቁመን የምናልፍበት በረከት ሁሉ በህይወታችን ስላለን ነው፡፡ ሁለቱ እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ አንዱን ብቻ ከለጠጥነው እንስታለን ሁለቱንም በሚዛናዊነት ከያዝነው እንበረታለን፡፡  
ክርስትና በአንድ በኩል የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ የዮሐንስ ወንጌል 1፡12
ክርስትና ከሞት የመነሳትና ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ስፍራ የመቀመጥ መንፈሳዊ ማእረግ ነው፡፡
በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡6-7
ክርስትና የንጉሱ የእግዚአብሄር ቤተሰብነት ማእረግ ነው፡፡ ክርስትና የነገስታት ቤተሰብን አባልነት ስልጣን ነው፡፡
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡9
ክርስትና በጠላት ሃይል ሁሉ ላይ ያለ ታላቅ ስልጣን ነው፡፡
እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። የሉቃስ ወንጌል 10፡19
ክርስትና የእግዚአብሄር ሙሉ እርዳታ ያለበት የምድር ጉዞ ነው፡፡ ክርስትና ብዙ እንቅፋቶች ያሉበት የተግዳሮትም ጉዞ ነው፡፡
ታላቅ መዝገብ በህይወታችን አለ ነገር ግን ለሰው የሚደርሰው መከራ ሁሉ ደግሞ ይደርስብናል፡፡  
ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 2 ቆሮንቶስ 47-9
1.      በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም
እግዚአብሄር ስለጠራን ብቻ ሁሉም ነገር ፀጥ ብሎ አይገዛልንም፡፡ ነገሮች የሚገዙልን በሃይል ነው፡፡ ሁሉም ነገር አቅማችንን የሚፈትሽ ይመስላል፡፡ ሁሉም ነገር ይፈታተነናል፡፡ ሁሉም ነገር ይገፋናል፡፡ ሁሉም ነገር አገራችን እንዳይደለ ያስታውሰናል፡፡ ሁሉም ነገር እንደማይወደን እንደማይቀበለን ተቃውሞውን ባገኘው አጋጣሙ ሁሉ ያሳየናል፡፡
ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። የማቴዎስ ወንጌል 11፡12
ነገር ግን የሚያስጨንቀንን በእርሱ ላይ ስለምንጥል አንጨነቅም፡፡ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን ስንፈልግ ሁሉ ነገር ስለሚጨመርልን አንጨነቅም፡፡ እኛ የእግዚአብሄርን ስራ ስንሰራ እርሱ የእኛን ስራ ስለሚሰራ ለእግዚአብሄር መንግስት ስራ እንጂ ለጭንቀት ጊዜ የለንም፡፡ ሁሉም ይገፋናል በማንም አንጨፈለቅም፡፡
ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።  ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡35-37
2.       እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም
እግዚአብሄር እረኛችን ነው ሁልጊዜ ይመራናል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ ነገሮች ሁሉ ጥቁርና ነጭ ሆነው በግልፅ አይታዩንም፡፡ አንዳንዴ እናመነታለን፡፡ አንዳንዴ ግራ እንጋባለን፡፡ አንዳንዴ ያልተመለሰ ጥያቄ ይኖረናል፡፡ አንዳንዴ እግዚአብሄር ለዚህ አሳልፎ አይሰጠኝም ያልነው ነገር ይደርስብናል፡፡ አንዳንዴ አስበን የማናውቅው መከራ ውስጥ እናልፋለን፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንቆቅልሽ ይሆኑብናል፡፡ ነገር ግን በልባችን ያለው የተስፋ ድምፅ ከማመንታታችን ድምፅ ይበልጣል፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። ወደ ሮሜ ሰዎች 4፡18
በተስፋ ደስ ስለሚለን በመከራ እንታገሳለን፡፡
በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡12
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡3-4
3.       እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም
የሚያሳድዱን አሉ እንጂ የሚቀበሉን አልጠፉም፡፡ የማይፈልጉን አሉ እንጂ በክብር የሚፈልጉን ብዙ አሉ፡፡ በውስጣችን ያለውን የሚንቁ አሉ እንጂ በውስጣችን ያለውን የእግዚአብሄርን ፀጋ የሚያውቁና የሚያደንቁ ሁልጊዜ አይጠፉም፡፡ ፊታችንን ማየት የማይፈልጉ አሉ እንጂ ፊታችንን ለማየት የሚናፍቁ አይጠፉም፡፡ ንግግራችንን የሚጠሉ  አሉ እንጂ የአፋችንን ቃል በጉጉት የሚጠብቁ የሚወዱን በዘመናት መካከል አይጠፉም፡፡
በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡15-16
ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ። ወደ ገላትያ ሰዎች 4፡15
4.       እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው ማለት አንወድቅም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አባታችን ነው ማለት እንወድቃለን አንጂ አንጠፋም ማለት ነው፡፡ ጠፉ ስንባል እንበዛለን፡፡ ሞቱ ስንባል በትንሳኤ እንነሳለን፡፡ ለጊዜው ሊጥለን እንጂ እግዚአብሄር ሃይላችን ስለሆነ ሊያጠፋን የሚችል ሃይል ከሰማይ በታች የለም፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። የዮሐንስ ወንጌል 12፡24
አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡8-10
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #መከራ #ፈተና #ሞት #በሁሉ #እንገፋለን #አንጨነቅም #እናመነታለን #ተስፋአንቆርጥም #እንሰደዳለን #አንጣልም #እንወድቃለን #አንጠፋም #ህይወት #ስጋ #መፅናት #መታገስ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment