Popular Posts

Tuesday, July 24, 2018

የጥርጥር አለም ምልክቶች

የእምነት አለም አለ የጥርጥር አለም አለ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት በሚገኘው በእምነት አለም ውስጥ የሚያገኛቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሰው በጥርጥር አለም ውስጥ የሚያጣቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሃጢያቱ እንደሞተና እንደተነሳ የማያምን ሰው ለእምነቱ ምንም መሰረት ስለሌለው ሁሌም በጥርጥር ውስጥ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጌታን አምኖና ተከትሎ ነገር ግን እምነቱን የማያሳድግ ልቡን ከጥርጥር ፣ ካለማመን እና ፍርሃት የማይጠብቅ ሰው ደግሞ አለ፡፡ ይህ ሰው አልዳነው የዘላለም ህይወት የለውም ባይባልም ነገር ግን እግዚአብሄር በምድር እንዲሰራ ያዘጋጀለትን ስራ በእምነት መፈፀም ያቅተዋል፡፡ የእግዚአብሄር መንገድ ሁሉ በእምነት ስለሆነ እግዚአብሄርን በሙላት በመከተል ፍሬ ማፍራት ይሳነዋል፡፡ ካለእምነት እግዚአብሄርን ማስደሰርት ስለማይቻል በአጠቃላይ ከእግዚአብሄር ጋር በእምነት በመገናኘት እግዚአብሄን ማስደሰት ይሳነዋል፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
በተለይ ደግሞ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ነገር ግን አለምን መስሎ የእግዚአብሄርን ቃል ስለህይወቱ በሚለው ላይ የማይቆምና በአካሄዱ አለምን የሚመስል ሰው በጥርጥር አለም ሲኖር ምን ምልክቶች እንዳሉት እንመልከት፡፡
1.      የጥርጥር አለም የጭንቀት አለም ነው
እምነት ከጭንቀት ያሳርፋል፡፡ እምነት የሚያስጨንቀንን በሚያስብልን ላይ በመተማመን እንድንጥል ያደርገናል፡፡ እምነት በእግዚአብሄር ቃል የማይታየውን አለም ስለሚያሳይ ከጭንቀት ያሳርፋል፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ስለህይወቱ የሚለውን ነገር ከቃሉ የማይሰማና በእርሱ ላይ የማይቆም ሰው ስለሚጠራጠር በጭንቀት ያባክናል፡፡
እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡7
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። የማቴዎስ ወንጌል 13፡22
2.     የጥርጥር አለም ያለመርካት አለም ነው
የእምነት አለም የእርካታ አለም ነው፡፡ የእምነት ሰው ባለው ይረካል ለተጨማሪ ነገር ይዘረጋል፡፡ የጥርጥር ሰው ግን ባለውም ስለማይረካ ለተጨማሪ ነገር ሲዘረጋም በእምነት ስላይደለ አይሆንለትም፡፡
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6
3.     የጥርጥር አለም የፉክክር አለም ነው
የእምነት አለም የትኩረት አለም ነው፡፡ የእምነት አለም በአላማ ላይ ብቻ የሚያተኩር በአካባቢ ስላለ ነገር የማይጨነቁበት ከአለም ከንቱ ውድድር ራስን የሚያገሉበት የእረፍት እና የትኩረት አለም ነው፡፡ በተቃራኒው የጥርጥር አለም አላስፈላጊ የፉክክር ጦርነት ውስጥ የሚገባ ፣ የራስ ህይወት ላይ ሳይሆን የሌላ ሰው ህይወት ላይ የሚተኩር ፣ የራስ ኑሮን ዝም ብሎ ከመኖር ይልቅ ከሌሎች ኑሮ ጋር በማስተያየት የሚቀናበትና የሚያስቀናበት ከንቱ የፉክክር አለም ነው፡፡
ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10፡12
4.     የጥርጥር አለም የፍርሃት አለም ነው
የእምነት አለምን የሚመራው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ የእምነትን አለም የሚመራው ከእግዚአብሄር ቃል የሚገኘው ተስፋ ነው፡፡ የጥርጥርን አለም የሚመራው ደግሞ በጭንቀትና ፍርሃት ነው፡፡ የጥርጥርን አለም የሚያንቀሳቅሰው ፍርሃት ነው፡፡ ሰው ደግሞ ለፍርሃት ስላልተሰራ በፍርሃት የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ትክክል አይሆኑም፡፡
እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 1፡7
5.     የጥርጥር አለም የመናወጥ አለም ነው
የእምነት አለም የመፅናት አለም ነው፡፡ የእምነት አለም ያለመናወጥ አለም ነው፡፡ የእምነት አለም የመረጋጋተ አለም ነው፡፡ የእምነት አለም ያለመቸኮል አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም የመናወጥ አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም የመቅበዝበዝ ያለመፅናት ያለማረፍ አለም ነው፡፡
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምን አያፍርም። ትንቢተ ኢሳይያስ 28፡16

መዝሙረ ዳዊት 46፡1-2
አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።
6.     የጥርጥር አለም ያለማረፍ የጥልና የክርክር አለም ነው
የእምነት አለም የእረፍትና የሰላም አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም ሰላመ የሌለበት የረብሻ አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም የጥልና የክርክር አለም ነው፡፡ የእምነት አለም እግዚአብሄርን ተስፋ ስለሚያደርግ ከሰው ተስፋ አድርጎ አያዝንም፡፡ የጥርጥር አለም እግዚአብሄርን ተስፋ ስለማያደርግ ከሰው ለማስወጣት ይጣላል ይከራከራል፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ የያዕቆብ መልእክት 4፡1-2
7.     የጥርጥር አለም የራስ ወዳድነትና የጥላቻ አለም አይደለም፡፡
የእምነት አለም የእግዚአብሄር ቃል አለምና የእግዚአብሄር መንፈስ አለም ስለሆነ የፍቅር አለም ነው፡፡ የጥርጥር አለም ግን በእግዚአብሄር ቃል ስለማይመራ የራስ ወዳድነትና የጥላቻ አለም ነው፡፡
በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና። ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡6
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
የእምነት አለም ፅሁፌን ማንበብ ከፈለጉ https://www.facebook.com/notes/abiy-wakuma-dinsa/%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%88%9D%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8A%A0%E1%88%88%E1%88%9D-%E1%8A%AD%E1%89%A5%E1%88%AD/10156812620939255/
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእምነትተጋድሎ #የእግዚአብሄርቃል #ቃሉንመስማት #ደስታ #ሰላም #እርካታ #ክብር #ገድል #ነፃነት #ሞገስ #ሃይል #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment