Popular Posts

Tuesday, July 3, 2018

የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ

አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና። ትንቢተ ኢሳይያስ 541-3
የእግዚአብሄርን ሃሳብ በሙላት አገልግለን እንዳናልፍ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ የአእምሮ ውስንነት ነው፡፡ የአእምሮ ውስንነት የስጦታ ጠላት ነው፡፡ የአእምሮ ውስንነት የውጤት እንቅፋት ነው፡፡
ሰው ምንም ነገር ኖሮት አእምሮው ግን ከተወሰነ  ምንም ማድረግ አይችልም ተወሰነ ማለት ነው፡፡ ሰው ምንም ነገር ኖሮት ልቡ ከደከመ አቃተው ደከመ ማለት ነው፡፡ ሰው ምንም በእድሜ ወጣት ቢሆን ልቡ ካረጀ አረጀ ደከመ ማለት ነው፡፡
ኢያሱም ሸመገለ በዕድሜም አረጀ እግዚአብሔርም አለው፦ አንተ ሸመገልህ፥ በዕድሜህም አረጀህ፤ ያልተወረሰች እጅግ ብዙ ምድር ገና ቀርታለች፤ መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 13፡1
ሰው ለማሸነፍ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ኖሮት በልቡ አይችልም ካለ ስለማይሞክር አይችልም፡፡ የእስራኤል ህዝብ እግዚአብሄር ከእነርሱ ጋር ሆኖ አንችልም በማለት ለማሸነፍ ለመውረስ የቀረበላቸውን እድል አበላሹ፡፡   
ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን፦ በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ። ኦሪት ዘኍልቍ 13፡31
ሰዎች አንችልም የሚሉት በተለያየ ምክኒያት ነው፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የሚወስኑበትን ነገር ጥሰው ከዚህ አታልፍም ብሎ የሚወስናቸውን ነገር ሁሉ በማለፍ እችላለሁ ማለት ከቻሉ ይችላሉ፡፡
ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና፦ ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ። ኦሪት ዘኍልቍ 13፡30
እግዚአብሄር ፂዮንን አእምሮዋን እንድታሰፋና ትልቅ ከሆነው ከእግዚአብሄር ትልቅን ነገር እንድትጠብቅ ይናገራታል፡፡ እግዚአብሄር  በነቢዩ አማካኝነት ፂዮን ከወሰናት ነገር አልፋ እንድታይ ያበረታታል፡፡ ፂዮን መጠበቅዋን እንዳታሳንስ እግዚአብሄር ይናገራታል፡፡  
የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና። ትንቢተ ኢሳይያስ 54፡2-3
ሰዎች በተለይ ካለፉበት የህይወት ተሞክሮ ተነስተው ይህን ማድረግ አልችልም ፣ ከዚህ ማለፍ አልችልም እነዚህ ማድረግ አልችልም ብለው ራሳቸውን ይወስናሉ፡፡
እግዚአብሄር ደግሞ ሁልጊዜ በምንም ነገር እንዳንወሰን ፣ ለራሳችን የሰጠነውን ድንበር እንድናልፍና ከገደበን ነገር አልፈን ራሳችንን እንድንዘረጋ ያበረታናል፡፡
እርሱም፦ ሄደሽ ከጐረቤቶችሽ ሁሉ ከሜዳ ባዶ ማድጋዎችን ተዋሺ አታሳንሻቸውም አላት። መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 4፡3
ለእግዚአብሄር ታእምር ማድረግ ቀላል ነው፡፡ እግዚአብሄር ጊዜን የሚፈጅበት የእኛን ልብ በማዘጋጀት ነው፡፡ እግዚአብሄር በህይወታችን ታእምራትን ሲያደርግ መጀመሪያ የሚያዘጋጀው እኛን ነው፡፡ እኛ እንድንሰፋ እንድንዘጋጅ እንድንቆፍር እንድናሰፋ ይፈልጋል፡፡ ራሳችን አስፍተን ካልጠበቅን ታአምር ሲመጣ ከታእምራቱ እንደሚገባን መጠቀም ያቅተናል፡፡
እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ሸለቆ ሁሉ ጕድጓድ ቆፈሩ። እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ነፋስ አታዩም፥ ዝናብም አታዩም፥ ይህ ሸለቆ ግን ውኃ ይሞላል፤ እናንተም ከብቶቻችሁም እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ። መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 3፡16-17
ዛሬ እግዚአብሄር ወዳየልህ ወደሚቀጥለው የህይወት ደረጃ የወሰነህ ነገር ምንድነው? ይህን ማድረግ እችላለሁ ይህንን ማድረግ ግን አልችልም ብለህ የደመደምከው ነገር ምንድነው? የእግዚአብሄርን ቃል ፈልግ፡፡
እምነት ከመስማት ነው መስማትንም በእግዚአብሄር ቃል ነውና፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17
የራስህን ህይወት በእግፍዚአብሄር ቃል እንጂ በልምድህ ወይም በሰዎች አስተያየት አትመዝን፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል እንዳለ ተቀበል፡፡ ቃል ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል፡፡
ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። የማርቆስ ወንጌል 9፡23
አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ እልል በዪ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነቺቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቈጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና፥ ዘርሽም አሕዛብን ይወርሳልና፥ የፈረሱትንም ከተሞች መኖሪያ ያደርጋልና። ትንቢተ ኢሳይያስ 54፡1-3
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #አስፊ #ይዘርጉ #አትቆጥቢ #አስረዝሚ #አፅኚ #ትሰፋፊያለሽ #ይወርሳል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #መርገጥ #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መቃተት #መንበርከክ #መጠበቅ #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment