Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, July 10, 2018

እግዚአብሔር የገቢ ምንጫችሁ ሲሆን

የገቢ ምንጫችሁ የሆነ ሰው ወደዳችሁም ጠላችሁም የወደፊት እድላችሁን ይወስናል፡፡ የገቢ ምንጫችሁን የሚያመጣ ሰው የሚለውን ላለመስማት ከባድ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ነው፡፡ ወደዳችሁም ጠላችሁም የገቢ ምንጫችሁን የሚያመጣ ሰውን ራእይ በህይወታችሁ ታስፈፅማላችሁ፡፡
በገንዘብ ስለተገዙት ባሮች መፅሃፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ይህንኑ ነው፡፡ ስለባሮች መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር እናንተ ክርስትያን ስለሆናችሁ የምታገለግሉትና የምትታዘዙት ጌታን ክርስቶስን ነው እንዲሁም የርስትን ብድራት የምትቀበሉት ከእርሱ ነው እያለ እግዚአብሄር ምንጫቸው መሆን እንዳለበት ያስተምራል፡፡ እግዚአብሄር ቀጣሪያቸውና ከፋያቸው ሲሆን በነፃነት ሰውን በማገልገል እግዚአብሄርን እንደሚያገለግሉ መፅሃፍ ቅዱስ ያስተምራል፡፡  
የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡6-8
ጌታ የገቢ ምንጫችሁ እግዚአብሄር ሲሆን ሰዎች እንዲያዩዋችሁ ለታይታ መኖርን ታቆማላችሁ፡፡
ሰዎች የገቢ ምንጫችሁ ሲሆኑ ከሰው እንጂ ከእግዚአብሄር የሚገኘውን ክብር ማግኘት አትፈልጉም፡፡ ሰዎች የገቢ ምንጫችሁ ሲሆኑ ከልባችሁ ሳይሆን ሰዎችን እያያችሁ ለታይታ ብቻ ትኖራላችሁ፡፡ ሰዎች የገቢ ምንጫችሁ ሲሆኑ ሰውን እንጂ እግዚአብሄርን ለማስደሰት አትፈልጉም፡፡
እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? የዮሐንስ ወንጌል 5፡44
ጌታ የገቢ ምንጫችሁ ሲሆን ለጌታ ብቻ ለመኖር ነጻነትን ታገኛላችሁ፡፡
አገልጋይ ለኑሮ ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ቤተክርስትያን በምድር ላይ ተልእኮዋን ለመወጣት ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡ ለራእይ ማሳካት ገንዘብን እንዲሰጡ እግዚአብሄር ሰዎችን ይጠቀማል፡፡ ነገር ግን ሰዎች እግዚአብሄርን በመታዘዝ በገንዘባቸው ያገለግሉናል እንጂ የገቢ ምንጫችን በመሆን የሚፈልጉትን ነገር የሚያስደርጉን መሆን የለባቸውም፡፡ የገቢ ምንጫችን ሲሆን ብቻ ነውእግዚአብሄር የሰጠንን ነገር በገንዘቡ ሊገዛ የሚፈልግ ሰው ካለ እምቢ እንድንል አቅም የሚኖረን፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን እንደ ሀዋርያቱ  የእግዚአብሄርን ስጦታ በገንዘቡ ሊገዛ የሚመጣውን ሰው ከገንዘብህ ጋር ጥፋ ማለት እንችላለን፡፡
ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና። እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። የሐዋርያት ሥራ 8፡18-20
ጌታ የገቢ ምንጫችሁ ሲሆን ማንም ሰው አያስፈራራችሁም
ጌታ የገቢ ምንጫችሁ ሲሆን ማንም ሰው የእኔን ፍላጎት ካላሟላህ ገንዘብ መስጠትን አቆማለሁ ብሎ አያስፈራራችሁም፡፡ ሰው እናንተን በማገልገል እግዚአብሄርን እንደሚያገለግል ካልተሰማው ለእርሱም ለእናንተም አይጠቅምም፡፡ በገንዘቡ የሚያስፈራራችሁን ሰው በሰላም እንዲሄድ ትፈቅዱለታላችሁ፡፡ እግዚአብሄር ሰዎችን ሲጠቀም እግዚአብሄር በልባችን ያስቀመጠውን ራእይ እንድናደርግ እንጂ ገንዘብ የሚሰጡንን ሰዎች ራእይ እንድናደርግ አይደለም፡፡ በእነርሱ ውስጥ ያለውን ራእይ ማድረግ ከፈለጉ እኛ እናስፈልጋቸውም፡፡ እኛ  ከእግዚአብሄር የተቀበልነው በቂ ራእይ አለን፡፡ እግዚአብሄር የገቢ ምንጫችን ሲሆን ማንም ሰው እኔ የምፈልገውን ነግው የምታደርገው ካለበለዚያ ዋ ብሎ አያስፈራራንም፡፡ 
ሌሎች በእናንተ ላይ ይህን መብት የሚካፈሉ ከሆኑ እኛማ ይልቁን እንዴታ? ነገር ግን የክርስቶስን ወንጌል እንዳንከለክል በሁሉ እንታገሣለን እንጂ በዚህ መብት አልተጠቀምንም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡12
ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን ማንም ሰው ክብራችሁን እንዲነካ አትፈቅዱለትም፡፡
ጌታ ምንጫችህ ሲሆን ማንም ሰው እኔ ባልሰጠው ይሞታል ብሎ ክብራችንን እንዲያዋርድ አንፈቅድለትም፡፡ ጌታ ምንጫችህ ሲሆን ማንም ሰው እኔ ባልደርስለት ዋጋ የለውም ነበር እንዲል አንፈቅድም፡፡ ለጌታ ልንሰጥና ልናገለግለውም ራሳችንን ሰጥተን የጌታን ስራ ለመስራት ሰውን አንለምንም፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን የወንጌል ማህበርተኛ ለመሆን ሰዎችን በራሳችን ወጭ እናገለግላለን፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን በነፃ ወንጌልን የማገልገል ትምክታችንን ማንም ከንቱ እንዲያድርግብን አንፈቅድም፡፡
እኔ ግን ከእነዚህ ሁሉ ምንም አልተጠቀምሁም። እንዲህ እንዲሆንልኝ ይህን አልጽፍም፤ ማንም ትምክህቴን ከንቱ ከሚያደርግብኝ ሞት ይሻለኛልና። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡15
እንግዲህ ደመወዜ ምንድር ነው? ወንጌልን እየሰበክሁ በወንጌል ካለኝ መብት በሙሉ እንዳልጠቀም ወንጌልን ያለ ዋጋ ብናገር ነው። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡18
ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን በእኛ ማግኘት ጌታ ብቻውን ይመሰገናል፡፡
ጌታ ምንጫችን ሲሆን የጌታን ክብር ለማንም ስጋ ለባሽ እንሰጠም፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን ማንንም ሰው እንደ አዳኛችን አናይም፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን ለእኛ የሚሰጡ ሰዎች ለጌታ በመስጠታቸው እግዚአብሄርን ያመሰግናሉ እንጂ ራሳቸውን አያመሰግኑም፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን ለእግዚአብሄር የሚሰጡ ሰዎች ለጌታ በመስጠታቸው ራሳቸውን እንደ እድለኛ ይቆጥራሉ፡፡ ጌታ ምንጫችን ሲሆን በህይወታችን የጌታና የሰው ክብር ከሚቀላቀል ሰዎች የሚያደረጉልን ጥቅም ቢቀርብን ይሻለናል፡፡ 
አብራምም የሰዶምን ንጉሥ አለው፦ ሰማይንና ምድርን ወደሚገዛ ወደ ልዑል እግዚአብሔር እጄን ከፍ አድርጌአለሁ፤ አንተ፦ አብራምን ባለጠጋ አደረግሁት እንዳትል፥ ብላቴኖቹ ከበሉት በቀር ከእኔ ጋር ከሄዱትም ድርሻ በቀር፥ ፈትልም ቢሆን የጫማ ማዘቢያም ቢሆን፥ ለአንተ ከሆነው ሁሉ እንዳልወስድ አውናን ኤስኮልም መምሬም እነርሱ ድርሻቸውን ይውሰዱ። ኦሪት ዘፍጥረት 14፡22-24
ጌታ ምንጫችን ሲሆን በእናንት ማግኘት ማንም እንዲጠራ አትፈቅዱም
ጌታ ምንጫችን ሲሆን ለእኛ የሚሰጥ ሰው ለእግዚአብሄር እንደሰጠ መቁጠር አለበት፡፡ እንደው ለእኛ አዝኖ ብቻ የሚያድርግልንን አንቀበለም፡፡ እኛ ብዙዎችን ባለጠጋ የምናደርግ ሁሉ የእኛ የሆነ የእግዚአብሄር አገልጋዮች እንጂ የሚታዘንልን ምስኪን ሰዎች አይደለንም፡፡  
ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡10
ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን በሙሉ ልቡ ያልሆነ በስስት የሚሰጠውን ሰው አልቀበለም ማለት ትችላላችሁ
ጌታ ምንጫችን ሲሆን ብቻ ነው በደስታ ከሚሰጠው ሰው ብቻ የምንቀበለው፡፡ ደስ ሳይለው በልቡ እየሰሰተ የሚሰጥን ሰው ላለመቀበል ድፍረቱ የሚኖረን ጌታ ምንጫችን ሲሆን ብቻ ነው፡፡
የቀናተኛን ሰው እንጀራ አትብላ፥ ጣፋጩ መብልም አይመርህ፤ በልቡ እንዳሰበ እንዲሁ ነውና፤ ብላ ጠጣ ይልሃል፥ ልቡ ግን ካንተ ጋር አይደለም። መጽሐፈ ምሳሌ 23፡6-7
ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን ለሰዎች ስለሚበዛው ስሌት እንጂ ስጦታቸውን ፈላጊ አትሆኑም
ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን ህይወታችሁን ይለውጣል ብለላችሁ ተስፋ የምታደርጉት አንድም ሰው ከሰማይ በታች አይኖርም፡፡ ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን ሰዎች ለእግዚአብሄር ስራ ስለመስጠታቸው ለሰዎች ስለሚበዛው ስሌት እንጂ ስጦታቸውን ፈላጊ አትሆኑም፡፡
በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡17
ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን የእግዚአብሄርን ቃል በነፃነት ለመኖርና ለመስበክ ድፍረት ይኖተራችሁዋል፡፡ ጌታ ምንጫችሁ ሲሆን ለሰው ብላችሁ የእግዚአብሄርን ቃል እውነት አታመቻምቹም፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ምንጭ #አቅራቢ #ሰጭ #ጭንቀት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment