Popular Posts

Sunday, July 8, 2018

መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው

በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 612-13
የሆድ ነገር ብዙ ሰዎችን የማይፈልጉትን እንዲያደርጉ ያስደርጋቸዋል፡፡ የሚጠፋው የሆድ ነገር ብዙ ሰዎችን ያዋርዳል ከአላማም ያደናቅፋል፡፡ ብዙ ለጌታ ሲሮጡ የነበሩትን ሰዎችን የሆድ ነገር አሳስሮ ሽባ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ ብዙ ሰዎች ስለሆድ ብለው ራእያቸውን ጥለው እጅግ ያለቅሳሉ፡፡
ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ወደ ዕብራውያን 12፡16
ጌታ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም እንዳለ የሆድ ነገር የሰለጠናበቸው ሰዎች ጌታ እንደሚገባ ሊሰለጥንባቸው አይችልም፡፡ የሆድ ነገር የሚገዛቸው ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ለጌታ ሊገዙ አይችሉም፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። የማቴዎስ ወንጌል 6፡24
ሰው እያደገ ሲሄድ ፍላጎቱ በዚያው መጠን ስለሚጨምር የሆድ ፈተና የሌለበት ሰው የለም፡፡ ሁሉም ሰው ነገ ስለሚበላው ነገር በሆዱ ይፈተናል፡፡ ሁሉም ሰው የያዘውን እውነት እንዲያመቻምችና ሆዱን እንዲሞላ ተከታታይ ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ ሁሉ ሰው ስለሆድ ምክኒያት ህሊናው የማይፈቅድውን ነገር እንዲያደርግ ይፈተናል፡፡
ትራባለህ ታጣለህ የሚል ማስፈራራትን ከሰማን የያዝንውን የእግዚአብሄር ቃል እውነት እንጥላለን፡፡ ነገር ግን ብራብም ባጣም አላዬን አልሸጥም ካልን ብንራብም ብናጣም ምንም አንሆንም ነገር ግን አላችን እናስፈጽማለን፡፡ ሃዋሪያው መጥገብንም መዋረድንም አውቀዋለሁ ሲል የማያውቅህን ሄደህ አስፈራራ የሚል ይመስላል፡፡ ሃዋሪያው ማግኘትንም ማጣትንም ልካቸውን ስላወቀ አንዳቸውም ከአላማው አያስፈራሩትም አያስቆሙትም፡፡ ማጣትና መዋረድ የሚያስፈራውና የሚያስቆመው የማያውቀውን ሰው ነው፡፡ መጉደልን የሚያውቅ ሰው ሁሉን የሚያስችለው እግዚአብሄር እንጂ መራብ በህይወቱ ላይ ምንም ስለማይቀንስ መብዛት በህይወቱ ላይ ምንም ስለማይጨምር ማጣት አያስፈራራውም፡፡
እኛ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ስንፈልግ ለሆድ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ይሰጠናል ብለን የእግዚአብሄርን ቃል ካመንን  የእግዚአብሄርን ፈቃድ በዘመናችን አገልግለን ማለፍ እንችላለን፡፡
ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡12-13
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#መሰረታዊፍላጎት #ነፃነት #አትጨነቁ #ቅድሚያ #ምንእንበላለን #ምንእንጠጣለን #ምንእንለብሳለን #አስቀድማችሁ #ፅድቁን #የአለምሃሳብ #የባለጠግነትማታለል #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment