Popular Posts

Wednesday, July 4, 2018

መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ

ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡10-11
ሰው እንደፈለገ እየኖረ ህይወትን ማየት አይችልም፡፡ ሰው ያመጣለትን እየተናገረ የህይወትን ደስታ ማየት አይችልም፡፡ ሰው እንደልቡ እያደረገ የህይወትን እርካታ ማየት አይችልም፡፡
በህይወት መልካም ቀኖች የሚባሉ ቀኖች አሉ፡፡ በህይወት የእርካታና የደስታ ቀኖች አሉ፡፡ በህይወት የእረፍት ቀኖች አሉ፡፡ ሰው እነዚህን ነገሮች ካደረገ ህይወትን ያጣጥማል፡፡ ሰው አነዚህን ነገሮች ካላደረገ ህይወትን አያይም፡፡
ሁላችንም እግዚአብሄርን ተስፋ እናደርጋለን፡፡  እነዚህን የሚያድርግ ሰው ግን ካልተመለሰ በስተቀር ህይወትንና መልካሞችን ቀኖች ሊያይ አይችልም፡፡ እነዚህን ነገሮችን በማድረግ የሚቀጥል ሰው ካለተመለሰ በስተቀር ህይወትንና መልካሞችን ቀኖች ከማየት ተስፋ መቁረጥ አለበት፡፡ ሁሉም ሰው መልካምን ቀኖች ለማየት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን መልካምን ቀኖች ለማየት የሚያስችሉትን ነገሮች የሚያደርገው ሁሉም ሰው አይደለም፡፡   
በህይወቱ እርካታን ማየት የሚወድ ሰው ሊያደርጋቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ በህይወት እርካታ የሚገኘው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡
1.      መላሱን ከክፉ ይከልክል
ለህይወቱ ዋጋ የሚሰጥ ህይወትን የሚወድና መልካም ቀኖችን ማየት የሚፈልግ ሰው መላሱን ክፉ ከመናገር መከልከል አለበት፡፡ ክፉ ነገርን ዋጥ ማድረግ አለበት፡፡ ክፉን እንዳይናገር ራሱን መግዛት አለበት፡፡ ክፉን እንዳይናገር ትሁት መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለሌላወ ሰው የሚናገረው መልካም ነገር ከሌለ ዝም ማለት አለበት፡፡ ክፉ መናገር ራሳነ ያቆሽሻል፡፡ ክፉ መናገር መንፈስ ቅዱስን ያሳዝናል፡፡ ክፉ መናገር እግዚአብሄ ከእኛ ጋር እዝንዳይሆን ደርጋል፡፡ ክፉ መናገር ከህይወት ያጎድለናለናል፡፡
ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡29-30
2.     ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤  
በልቡ አንድን ነገር ይዞ ሌላን ነገር የሚናገር ሰው መልካም ቀኖችን ማየት አይችልም፡፡ በልቡ የሚፈልገው ነገር ሸፍኖ በተልኮል በማሳሳት ሌላ ነገር የሚናገር ሰው መልካምን ቀኖች ማየት አይችልም፡፡ ግልፅ ያልሆነ ሰውና ክፋትን ሽፍኖ እውነተኛ መስሎ ሰዎችን የሚያሳስት ሰው መልካም ቀኖችን ማየት አይችልም፡፡  
ነገር ግን የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኮል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም፤ እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ሁሉ ራሳችንን እናመሰግናለን። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 42
እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥1 የጴጥሮስ መልእክት 2፡1
3.     ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥
ሰው ከእግዚአብሄር የሚመጡትን መልካሞቹን ቀኖች ተስፋ ካደረገ ከከፉ ፈቀቅ ማለይት አለበት፡፡ በክፋት እየዋኘ የእግዚአብሄርን መልካምነት መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ ሰው ክፋትን እያሰበ ፣ ክፋትን እየተናገረና ክፋትን እያደረገ እግዚአብሄር ከእኔ ጋር ነው ማለት አይችልም፡፡ ሰው ከክፋት ጋር አለመተባበር አለበት፡፡ መልካሞችን ቀኖች ማየት የሚፈልግ ሰው ሁሉ ክፋትን መጸየፍ አለበት፡፡
ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡9
4.     መልካምንም ያድርግ
ለህይወቱ ዋጋ ያለውና መልካሙን ቀኖች ማየት የፈለገ ሰው የየትኛውም ችግር አካል መሆን አይፈልግም፡፡ መልካም ቀኖችን ማየት ሚፈልግ ሰው የመፍትሄ አካል መሆን ይፈልጋል፡፡ መልካሞችን ቀኖች ማየት የሚፈልግ ሰው ስለሰው መልካም ያስባል መልካመ ይናገራል መልካምን ያደርጋል፡፡ መልካሞችን ቀኖች ማየት የሚፈክልግ ሰው ከመልካምነት ውጭ ክፉ በማድረግ በእግዚአብሄ አምሳል የተፈጠረን ሰው በመራገም ከእግዚአብሄር ጋር አይጣላም፡፡
በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን፤  የያዕቆብ መልእክት 3፡9
ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡16-17
5.     ሰላምን ይሻ ይከተለውም
መልካችን ቀኖች ማየት የሚፈለግ ሰው ረብሻን አይመርጥም ሰላምንም ግን ይከተላል፡፡ ሰው ሰላምን የማይመርጠውና ረብሻን የሚመርጠው በህይወቱ ሰላም ሳይኖረው ሲቀር ነው፡፡ መልካሞቹን ቀኖች ማየት የሚፈልግ ሰው በጥላቻና በረብሻ ውስጥ የሚመጣውን መቆሳሰል አይፈልገውም፡፡ ለህይወቱ ዋጋ የሚሰጥ ሰው ግን ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ለማድረግ ይጥራል፡፡  
ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡18
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡3
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ባርኩ #ክፉ #መልካም #በረከት #ልትወርሱ #ትህትና #መልካምነት #መከባበር #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አንደበት #ከንፈር #ስድብ

No comments:

Post a Comment