በክርስትና ለህይወትና ለአገልግሎት ምቹ ሁኔታዎች
ያስፈልጋሉ፡፡ ለህይወትና ለአገልግሎት ተስማሚ ሁኔታዎች ካልተፈጠሩ በስተቀር ጌታን እንደሚገባው ማገልገል አንችልም፡፡ ለተሳካ የክርስትና
ህይወትና አገልግሎት የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች እንመልከት
አገልግሎት የሚጀምረው ስለኑሮ መጨነቅ ስንተው
ነው
ጭንቀት ራሱን የቻለ ከባድ ስራ ነው፡፡ ፊት ከሰጡት
ጭንቀት የሰውን ህይወት በቁሙ የሚውጥ ከአገልግሎት ሽባ የሚያደርግ አደገኛ ጠላት ነው፡፡ ጭንቀት አህዛብን በህይወታቸው ዘመን ሁሉ
እንደባሪያ የሚያስገዛ ጨካኝ ጌታ ነው፡፡ አገልግሎት ለእግዚአብሄር ከመገዛት ይጀምራል፡፡ ሰው ምንም ያህል ቢሞክር እና ቢጥር ለገንዘብና
ለጌታ መገዛት አይችልም፡፡
ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።የማቴዎስ ወንጌል 6፡24
ሰው እግዚአብሄርን ለማገልገል የሚያስጨንቀውን
የኑሮ ሃላፊነት በእግዚአብሄር ላይ መጣል አለበት፡፡ ሰው ለማገልገል ነፃ የሚሆነው ጭንቀቱን በእግዚአብሄር ላይ በጣለበት መጠን
ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ፦ ምን እንበላለን?
ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ነገር ግን አስቀድማችሁ
የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡31-34
አገልግሎት የሚጀምረው በምህረት መመላለስ ስንጀምር
ነው
በእግዚአብሄር ምህረት የተደረገለት ሰው ብቻ ያገለግላል፡፡
በእግዚአብሄር ምህርት ያልተደረገለት ሰው ባይኖርም ምህረት እንደተደረገለት የማያውቅ ሰው ግን አለ፡፡ ሰው ምህረት በተማረ መጠን
ብቻ ሰዎችን መማር ይችላል፡፡ የተማረበትን መጠን የተረዳ ሰው በዚያው መጠን ብቻ ሊያገለግል ይችላል፡፡ አገልግሎት የምህረት አምላክ
እግዚአብሄርን በምድር ላይ መወከል ነው፡፡ አገልግሎት በጥላቻና በጥል መካከል በምህረት መመላስ ነው፡፡ አገልግሎት ለሚጠሉን ርህራሄንና
ፍቅርን ማሳየት ነው፡፡ አገልግሎት በምህረት ለሌሎች ምሳሌ መሆን ነው፡፡
ስለዚህ ምክንያት ምሕረት እንደ ተሰጠን መጠን ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡1
አገልግሎት የሚጀምረው ያለኝ ይበቃኛል ስንል ነው
አገልግሎት ሰዎችን ማሳረፍ ነው፡፡ አገልግሎት
ለሰዎች የእረፍት ምሳሌ መሆን ነው፡፡ ያላረፈ ሰው ሰዎችን ሊያሳርፍ አይችልም፡፡ ያላረፈ ሰው ለሰዎች እረፍት ምሳሌ ሊሆን አይችልም፡፡
ጉድለቱ ላይ የሚያተኩር ሰው ግን ከራሱ አልፎ ሌሎችን ሊደርስ አይችልም፡፡ ጉድለቱ ላይ የማያተኩር ሰው ነፃ ሰው ነው፡፡ ጉድለቱ
ላይ የሚያተኩር ሰው ሊያገለግል ይችላል፡፡ ጉድለቱ ላይ የሚያተኩር ሰው ለማገልገል ነፃ ይሆናል፡፡ ያለኝ ይበቃኛል የሚል ሰው ለሌሎች
መልካም ምሳሌ በመሆን ማገልገል ይችላል፡፡
ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4፡11
ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን
መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 6፡6
አገልግሎት የሚጀምረው ሰዎችን መውደድ ስንጀምር
ነው
እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሄርን ለማገልገል
እግዚአብሄር ለወደደው ሰው ፍቅር ያስፈልገናል፡፡
ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ፦ ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም፦ በጎቼን አሰማራ። የዮሐንስ ወንጌል 21፡17
ሰውን የማይወድና ለሌላው ራሱን አሳልፎ የማይሰጥ
ሰው የራሱ ጥቅም የሚፈልግ ሞያተኛ እንጂ አገልጋይ አይደለም፡፡
እረኛ ያልሆነው በጎቹም የእርሱ ያልሆኑ ሞያተኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም ይነጥቃቸዋል በጎቹንም ይበትናቸዋል። የዮሐንስ ወንጌል 10፡12
አገልግልግሎት የሚጀምረው የባለጠግነት ምኞት ከህይወታችን
ሲሞት ነው
አገልግሎት በእግዚአብሄር ቃል ማፍራትና ሌሎች
በእግዚአብሄር ቃል እንዲያፈሩ ምሳሌ መሆን ነው፡፡ የባለጥግነት ምኞት የእግዚአብሄር ቃል በህይወታችን ፍሬ እንዳያፈራ የሚያንቅ
ህይወትን ካለፍሬ የሚያስቀር የመንፈሳዊ ህይወትና አገልግሎት ጠር ነው፡፡
የባለጠግነት ምኞት ራሱን የቻለ የህይወት ዘመን ከባድ ስራ ነው፡፡ የባለጠግነት ምኞት ያለበት ሰው እግዚአብሄርን የሚያገለግልበት
ጊዜና አቅም አይኖረውም፡፡
በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። የማቴዎስ ወንጌል 13፡22
ኀጥእ
ቀኑን ሁሉ ምኞትን ይመኛል፤ ጻድቅ ግን ይሰጣል፥ አይሰስትም። መጽሐፈ ምሳሌ 21፡26
በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም። የሉቃስ ወንጌል 8፡14
አገልግልግሎት የሚጀምረው ተቀብያለሁ ረክቻለሁ
የምሰጠው ነገር አለኝ ስንል ነው
በእግዚአብሄር ፊት ያለውን ክቡር ቦታ ያልተረዳ
ሰው እግዚአብሄርን እንደሚገባው ሊያገልግል አይችልም፡፡ በእግዚአብሄር እንደተወደደ እርግጠኛ ያልሆነ ሰው እግዚአብሄርን ሊያገለግል
አይችልም፡፡ እግዚአብሄር እንደሚንከባከበው የማያውቅ ሰው እግዚአብሄርን
ለማገልገል አቅም ያጣል፡፡ ያልተሰጠው ነገር እንደሌለ ሁሉ የእርሱ እንደሆነ የተረዳ ሰው ብቻ እግዚአብሄርን እንደሚገባው ማገልገል
ይችላል፡፡
ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡10
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma
Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች
https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር
#አገልግሎት #መዋረድ
#መርካት #ፀጋ
#እውቀት #ኢየሱስንተመልክተን
#አማርኛ #ስብከት
#መዳን #መፅሃፍቅዱስ
#ብፅእና #እምነት
#ታላቅነት #ማገልገል
#አቢይ #አቢይዋቁማ
#አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment