Popular Posts

Wednesday, July 4, 2018

ዘመናዊው ፈሪሳዊ

አንዳንዴ ሰዎች አገልጋይ የሚለውን ስም ካለአግባብ ሲጠቀሙበት ስናይ አገልጋይነት ትርጉሙ ተለወጠ እንዴ? ያሰኛል፡፡ አገልጋይ ማለት ሁሉን ለማገልገል የተዘጋጀ ሁሉን ካስቀመጠ በኋላ የሚቀመጥ ትሁት ሰው ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ግን አገልጋይ ማለት እርሱ ካልተቀመጠ ማንም የማይቀመጥ ከሰው ሁሉ በላይ የተከበረ ሰው ተብሎ ይተረጎማል፡፡ አገልጋይ የከበሬታን ወንበር የሚፈልግ ሲሆን ይታያል፡፡ በተለይ አገልጋይ ብዙዎች የሚያዩትና የሚከተሉት በፈሪሳዊያን ትምህርት ሲወሰድ እጅግ ያሳዝናል፡፡
የፈሪሳዊያን ትምህርት እንደ እርሾ ነው፡፡ ጥቂት በጥቂት ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው እርሾ የፈሪሳዊነት የትምህርት ሂደት ጥቂት በጥቂት ነው፡፡ በዚህም ዘመን ማንም ሰው ይብዛም ይነስም በፈሪሳዊያን ትምህርት ሊያዝ ይችላል፡፡ ሰው ፈሪሳዊ ሆኖ የሚመረቅበት የተወሰነ ቀን የለውም ነገር ግን ፈሪሳዊያን ያላቸውን ምልክት በማየት ምን ያህል ከፈሪሳዊያን ትምህርት የነፃን እንደሆንን ራሳችንን መፈተን እንችላለን፡፡
እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ። የሉቃስ ወንጌል 11፡43
አገልጋይ በከበሬታ ስም ካልተጠራ ቅር የሚለው ናቁኝ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ወደደም ጠላም የፈሪሳዊነት አስተሳሰብ ይዞታል ማለት ነው፡፡
በገበያም ሰላምታና፦ መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። እናንተ ግን፦ መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፦ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። የማቴዎስ ወንጌል 23፡7-10
አገልጋይ ሁሉንም ከመታገስ ይልቅ ማንንም የማይታገስ ሲሆንና ሁሉ ግን ሊታገሰው የሚገባ ከሆነ የፈሪሳዊነት ትምህርት ውስጥ በፈሪሳዊነት እርሾ ውስጥ ገብቶ ተነካክቷል ማለት ነው፡፡
አገልጋይ ሁሉ እንዲያገለግሉት ከሌሎች ሁሉ በላይ የተመረቀ ተወርዋሪ ኮከብ እንደሆነ ሌሎች እርሱን ሊያገለግሉ የተወሰነባቸው አድርጎ ካሰበ አገልጋይነት ጠፍቶበታል ማለት ነው፡፡
እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም። የማቴዎስ ወንጌል 20፡28
አገልጋይ በአገልጋይነቱ ብቻ ከሚያገለግላቸው ሰዎች የተሻለ ነገር ከፈለገ ከአገልግሎት ወድቋል ማለት ነው፡፡ በአገልጋይነቱ ብቻ ከሚያገለግለው ህዝብ በላይ የላቀን ነገር ለራሱ የሚፈልግ ሰው አገልጋይ አይደለም፡፡   
ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፥ እነሆ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ። ትንቢተ ኤርምያስ 45፡5
ፈሪሳያን ራሳቸውን እንደ ጠቃሚ ካህን ሌላውን እንደ ተጠቃሚ ህዝብ ያያሉ፡፡ ፈሪሳዊያን ራሳቸውን እንደባራኪ ሌላውን ሰው ሁሉ አንደተባራኪ ይቆጥራሉ፡፡ ፈሪሳዊያን እግዚአብሄር በእነርሱ እንጂ በሌላ በማንም እንደማየጠቀም ያስባሉ፡፡ ፈሪሳዊያን ራሳቸውን ከህዝብ ጋር ማየት አይፈልጉም፡፡ ፈሪሳዊያን ራሳቸውን ከህዝብ ይለያሉ፡፡ በአዲስ ኪዳን ካህንና ምእመን የሚባለ ነገር የለም፡፡ በአዲስኪዳን በክርስቶስ አምነን የዳንን ሁላችን ካህናት ነን፡፡
አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፦ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። የማቴዎስ ወንጌል 23፡9-10
ፈሪሳያን የህይወት ንጽፅህና ስለሌላቸውና በህይወታቸው መልካም ምሳሌ በመሆን ማንም ላይ ተፅእኖ ማድረግ ስለማይችሉ ህጉ እንዲህ ይላል በማለት ለራሳቸው ጥቅም በሃይል ያመቻቹታል፡፡
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡2-3
ፈሪሳዊያን እግዚአብሄር ስለሚያየው ስለልባቸው መቆሸሽ ግድ የላቸውም፡፡ ማስተካከል የሚፈልጉት ሰው የሚያየውን የውጫዊውን ነገር ብቻ ነው፡፡
ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል፡፡ እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። የሉቃስ ወንጌል 11፡39-41
ሳኦል በሃጢያት ሲያዝ በህዝቡ ዘንድ ብቻ እክብረኝ እንዳለው ከእግዚአብሄር ጋር ስላላቸው ነገር ግድ የላቸውም፡፡
እርሱም፦ በድያለሁ፤ አሁን ግን በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊትና በእስራኤል ፊት፥ እባክህ፥ አክብረኝ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 15፡30
በዚህ ምክኒያት ፈሪሳያን በእግዚአብሄር ስለማያምኑ ይጠቅመኛል ብለው የሚያስቡትን ከሰው የሚመጣው ክብር እንጂ ከእግዚአብሄር የሚመጣውን ክብር አይፈልጉትም፡፡ ከሰው ስለሚመጣው ክብር ዋጋ ይከፍላሉ ከእግዚአብሄር ስለሚመጣው ክብር ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ አይደሉም፡፡ 
እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? የዮሐንስ ወንጌል 5፡44
ፈሪሳዊያን ምንም ነገር የሚያደርጉት በህዝብ ዘንድ ምን ያስገኝልኛል በሚል ስሌት ብቻ ነው፡፡ የሚያሳውቃቸው ዝነኛ የሚያደርጋቸው ካልሆነ በስተቀር ማንንም ማገልገል አይፈልጉም፡፡ ስምና ዝናቸውን የሚያወጣ ከመሰላቸው ደግሞ የተሳሳተም ነገር ያደርጋሉ፡፡
የፈሪሳዊያን ትምህርት አስከፊነቱ ትምህርቱ ህይወታቸውን በጣም ከማባከኑ የተነሳ ዋጋቸውን በምድር ተቀብለዋል እንደሚባሉት ሰዎች ያስብላቸዋል፡፡
ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። የማቴዎስ ወንጌል 6፡1-2
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ፈሪሳዊ #ግብዝ #ውጭውን #ውስጡን #ልብ #ውበት #ዋጋ #ፊት #ባህሪ #ፍቅር #ልብ #ሃዘን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment