Popular Posts

Follow by Email

Friday, July 27, 2018

የሰናፍጭ ቅንጣት እምነት

ሐዋርያትም ጌታን፦ እምነት ጨምርልን አሉት። ጌታም አለ፦ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር። የሉቃስ ወንጌል 17፡5-6
እምነት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ካለ እምነት ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት አይቻልም፡፡ ካለእምነት ከእግዚአብሄር መቀበል አይቻልም፡፡ ካለ እምነት ከእግዚአብሄር ጋር ሰርቶ ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ በአጠቃላይ ያለ እምነት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
ኢየሱስ እምነት ጨምርልን ለሚለው ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልሰጠም፡፡ ኢየሱስ እምነትን ጨምርልን የሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ እንደሆነ አምኖ ይጨመርላችኋል አላለም፡፡ ኢየሱስ እምነት ጨምርልን ለሚለው ጥያቄ የመለሰው መልስ ሃዋሪያቱ ባላቸው እምነት ምን እያደረጉ እንደሆነ የሚፈትን ነው፡፡
ሁሉም ክርስትያን እምነት አለው፡፡  እያንዳንዱ ኢየሱስን የሚከተል ሰው የእምነትን መጠን ተካፍሏል፡፡  
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡3
እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄርን ቃል ከመስማት ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል የሰማ ሰው ሁሉ እምነት አለው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17
ልዩነት የሚያመጣው የምንሰማውን ቃል እንደት እንደምንሰማ ፣ በምንሰማው ቃል እንዴት እርምጃ እንደምወስድና በቃሉ እርምጃ ወሰድን በፅናት እንዴት እንደምንቀበል ነው፡፡
የሃዋሪያቱ ችግር የእምነት ትንሽነት ችግር አይደለም፡፡ እምነት እምነት ነው፡፡ እምነት የሚሰራ ነው፡፡ ለመስራት የማይበቃ እምነት የለም፡፡ እምነት ከሆነ ይሰራል፡፡
የሰውም ጥያቄ የእምነት ጭማሬ ጥያቄ አይደለም፡፡ ያለንን እምነት በሚገባ ከተጠቀምንበት በህይወታችን ስኬታማ እንሆናለን፡፡
በመፅሃፍ ቅዱስ የነቢይ ሚስት የነበረችው እዳ የነበረባት ሴት ወደኤልሳ እንዲረዳት ስትጮህ ኤልሳ ያላት በቤትሽ ምን አለ? ነው፡፡
ከነቢያትም ወገን ሚስቶች አንዲት ሴት፦ ባሌ ባሪያህ ሞቶአል፤ ባሪያህም እግዚአብሔርን ይፈራ እንደ ነበረ አንተ ታውቃለህ፤ ባለ ዕዳ ልጆቼን ባሪያዎች አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል ብላ ወደ ኤልሳዕ ጮኸች። ኤልሳዕም። አደርግልሽ ዘንድ ምን ትሻለሽ? በቤትሽ ያለውን ንገሪኝ አላት። እርስዋም፦ ለእኔ ለባሪያህ ከዘይት ማሰሮ በቀር በቤቴ አንዳች የለኝም አለች። መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ 4፡1-2
እግዚአብሄር ተአምር የሰራው በቤትዋ ባለው በራስዋ ነገር ተጠቅሞ ነው፡፡
አሁንም እግዚአብሄር በህይወታችን ታእምር የሚሰራው ባለን እምነት ተጠቅሞ ነው፡፡
ብዙ ሰው ግን እግዚአብሄር በተአምር እምነቴን ቢጨምር እኮ ብሎ በከንቱ ይመኛል፡፡ ችግርህ የመጣው በቂ እምነት ስለሌለህ አይደለም፡፡ ችግርህን የሚፈታው ተጨማሪ እምነት በማግኘት ላይ አይደለም፡፡ ችግርህ የመጣው ያለህን እምነት ባለመጠቀም ነው፡፡ ችግርህ የሚፈታው ያለህን አምነት ተጠቅመህ እንዴት ፍሬያማ እንደምትሆን በማወቅ ነው፡፡
ተጨማሪ እምነት ሳያስፈልገን ያለንን እምነት ወደውጤት የምናደርስበት 5 መንገዶች
1.      እምነት አስፈላጊ እንደሆነ ተረዳ
ከእግዚአብሄር በአጋጣሚ የምታገኘው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር እንደ ልጅ ከሰው አምነትን ይጠብቃል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት እምነት ይጠይቃል፡፡ በህይወትህ እምነት እንደሚያስፈልግህ እወቅ፡፡ ካለ እምነት እግዚአብሄርን ማስደሰት እንደማትችል አጥብቀህ ተረዳ፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
2.     እምነትን ለመጠበቅ ትጋ
እምነት የልብ ነው፡፡ ልብህን ከጥርጥር ካልጠበቅክ እምነትንም ልትጠብቅ አትችልም፡፡ ካልተጠነቀቅክ ጥርጥር እምነትን ከልብህ ያጠፋዋል፡፡ ጥርጥርን በልብህ ካስተናገደከው እመነትህ ሊሰራ አይችልም፡፡
እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል። የማርቆስ ወንጌል 11፡23
አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና። መጽሐፈ ምሳሌ 4፡23
በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል። የሉቃስ ወንጌል 8፡12
3.     በእምነት ነገር ሰነፍ አትሁን
እምነት የሰነፎች አይደለም፡፡ አምነት ትጋትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ሰው እግዚአብሄርን በእምነት ለመፈለግ ስንፍና ስላለበት በቀላሉ እግዚአብሄር የለም በማለት እግዚአብሄርን ከመፈለግ ይጋት ያቋርጣል፡፡
ሰነፍ በልቡ፦ አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም።መዝሙረ ዳዊት 14፡1
4.     እምነት የግፈኞች ነው
እምነት ገድል ስለሚጠይቅ የለስላሳ ሰዎች አይደለም፡፡ እምነት የግፈኞች ነው፡፡ እምነት ያነሰን ነገር የማይቀበሉ ሰዎች ነው፡፡
ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። የማቴዎስ ወንጌል 11፡12
እምነት ምንም ምክንያት አይቀበልም፡፡ እምነት የሚፈልገውን እስከሚያገኝ የሙጥኝ የሚል ነው፡፡
እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። የማቴዎስ ወንጌል 15፡25-28
እምነት በቃሉ ወደኋላ አያፈገፍግም፡፡
ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። ወደ ዕብራውያን 10፡38  
5.       እምነት መፅናትን ይጠይቃል
የሚታየው ሁሉ ከማይታየው የተገኘ ነው፡፡ ሰው በእርሻው ደክሞ መልካምን ዘር ዘርቶ ለፍሬ መጠበቅ አለበት፡፡ እንዲሁ እግዚአብሄርን በቃሉ ያመንንበት ነገር ከማይታየው ወደሚታየው አለም አስከሚመጣ ድረስ መፅናት ይገባናል፡፡ ሁሉንም እንደ እግዚአብሄር ቃል ካደረግን በኋላ እምነት መፅናትን ይጠይቃል፡፡
የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ወደ ዕብራውያን 10፡36
በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። ወደ ዕብራውያን 6፡11-12
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #የሰናፍጭቅንጣት #መፅናት #ትጋት #እምነት #መናገር #ግፈኞች #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ልብ #እምነት #ቃል #ማሰላሰል #ማድረግ #ሁሉይቻላል #ጥርጥር #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment