በመልካም ጀምረው በብቃት የሚጨርሱ ብዙ የተባረኩ አገልጋዮች አሉ፡፡ ብዙ ሰዎች በመልካም ይጀምሩና ሲፈፅሙ አይታይም፡፡
እግዚአብሄር እንድንጀምር ብቻ ሳይሆን እንድንጨርስም ይፈልጋል፡፡ መጀመር ወሳኝ እንደሆነ ሁሉ መጨረስም በጣም ወሳኝ ነው፡፡
ለአክሪጳም፦ በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4፡17
በመልካመ ጀምረን በብቃት እንዳንጨርስ የሚያደርጉንን ምክንያቶች እንመልከት
ፍጥነትን አለመረዳት
የክርስትና ህይወትና አገልግሎት እንደማራቶን እንጂ እንደመቶ ሜትር ሩጫ አይደለም፡፡ የመቶ ሜትር ሩጫ የሚፈልገው ጉልበት ነው፡፡ የማራቶን ሩጫ ግን ጉልበት ብቻ ሳይሆን ጥበብን ትግስትን ይፈልጋል፡፡ በአገልግሎት ውስጥ ብዙ የሚያደክምና የሚያሳምም ነገር አለ፡፡ የማራቶን ሩጫ የሚጠይቀው ጉልበት ብቻ ሳይሆን ህመምን የመታገስ ችሎታንም ነው፡፡ የማራቶን አሸናፊዎች ምንም ህምም የሌለባቸው ይመስለናል፡፡ እንዲያውም ታላቁን ህመም የሚካፈሉት የማራቶን አሸናፊዎች ናቸው፡፡ በክርስትናና አገልግሎት ለመዝለቅ ከፈለግን ከመጠን በላይ መፍጠን የለብንም፡፡ በክርስትናና እና በአገልግሎት መዝለቅ ከፈለግን የእግዚአብሄርን አሰራር እና እርምጃ መታገስ አለብን፡፡ በክርስትናና እና በአገልግሎት መዝለቅ ከፈለግን በጣም ከሚሮጡ አገልጋዮች ውድድር ራሳችንን ማግለል አለብን፡፡
የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል። መፅሃፈ ምሳሌ 4:18
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። መጽሐፈ ምሳሌ 28፡20
በህይወትና በአገልግሎት ረጅም መንገድ መሄድ ከፈለግን እግዚአብሄርን መቅደም የለብንም፡፡ ምንም ነገር ከማድርጋችን በፊት እግዚአብሄርን ህልውና መፈለግ መጠበቅና መከተል አለብን፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። መጽሐፈ ምሳሌ 13፡11
የማራቶብ ሯጭ ጉልበት ይሰማኛል ብሎ እንደ ስምንት መቶ ሜትር ሯጭ መሮጥ ቢጀምር ማንም ጠቢብ የማራቶን ሯጭ ቀድሞኛል ብሎ አይከተለውም፡፡ የማራቶን ሯጭ ጉልበት ይሰማኛል ብሎ እንደ ስምንት መቶ ሜትር ሯጭ መሮጥ ቢጀምር ጠቢቦቹ ቀስ ብለው በጊዜያቸው ሮጠው ሲደርሱ መንገድ ላይ ቆሞ ይገኛል፡፡ አገልግሎት እንደማራቶን ሩጫ ጉልበትን የመቆጠብ ጥበብ ፣ ትእግስትንና ህምምን የመቋቋም ችሎታን ይጠይቃል፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ ወደ ዕብራውያን 12፡1-2
ዘመንን አለመረዳት
ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ የምንወጣበት ጊዜ አለው የምንወርድበት ጊዜ አለው፡፡ ኢየሱስንም እናንግስህ ያሉት ጊዜ ነበር ስቀለው የተባለበትንም ጊዜ ነበር፡፡ ብዙ ሰዎች የተከተሉት ጊዜ ነበር አስራ ሁለቱ ብቻ የቀሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚያ ሁሉ ግን አገልግሎቱን እንዲቀጥል ያደረግው የእግዚአብሄርን አሰራር መረዳቱ ነው፡፡
ኢየሱስ ብዙ ህዝም ሲከተሉት አልተደነቀም ሁሉም ትተውት ሲሄዱም አልደነገጠም፡፡
ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም። ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፦ እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን? አለ። የዮሐንስ ወንጌል 6፡66-67
ኢየሱስ ዝነኛ የሆነበት ጊዜ ነበር የተደበቀበት ጊዜ ደግሞ ነበር፡፡ ጌታ ኢየሱስን የሚመለከት እነጂ ዝናንና መጥፋተነ የሚመለከት በአገልግሎት የሚፀና አይደለም፡፡
ሁሉም፦ ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። የማርቆስ ወንጌል 1፡27-28
ኢየሱስ ስለሃጢያታችን ለመሞት ነውርን መናቅ ነበረበት፡፡ ኢየሱስ ዝናውንና መልካም ስሙን በሰው ዘንድ መጠበቅ ቢፈልግ ኖሮ ለመስቀል ሞት የታዘዘ አይሆንም ነበር፡፡
እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ወደ ዕብራውያን 12፡1-2
በእግዚአብሄር አለመታመን
በእግዚአብሄር የሚታመን ሰው በእርሱ የጀመረውን እራሱ እንደሚፈፅመው ያምናል፡፡ አገልግሎቱ ከእግዚአብሄር እንደተሰጠው የማያምን ሰው ግን እራሱ በስጋው ሊፈፅጽመው ሲሞክር መንገድ ላይ አለክልኮ ከአገልግሎት ሩጫ ያቋርጣል፡፡
ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና። ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2፡13
ራስን አለመረዳት
በክርስትና በራሳችን ስንደክም የሚያበረታ የእግዚአብሄር ፀጋ አለ፡፡ ሰው ራሱን ከእግዚአብሄር ፀጋ ለይቶ ካየ አገልግሎቱን ሊዘልቅ አይችልም፡፡ እኛ ስንደክም ድካማችንን የሚሸፍን የእግዚአብሄር ፀጋ ባይኖር ኖሮ አገልግሎት የማይታሰብ ነው፡፡
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 12፡9-10
ራስን አለመግዛት
አገልግሎት የራሱ ክብርና የራሱ ህግ አለው፡፡ ህጉን አለመጠበቅና ለስጋ አርነት መስጠት ከአገልግሎት ብቁ አንዳንሆንና እንድንጣል ያደርገናል፡፡
የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን። ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፥ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 9፡25-27
በክርስትናና በአገልግሎት በእግዚአብሄር ቤት እንዴት በእውነት መኖር እንዳለብን ማወቅ አለብን፡፡
ብዘገይ ግን፥ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። 1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፡15
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ጻድቃን #የታመነ #መቀጨት #ፍጥነት #ጥበብ #ድካም #ብርታት #ዝና #ነውር #ስጋ #ዘመን #መውጣት #መውረድ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ትጋት #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ጥቂትበጥቂት #ሙሉቀን #እየተጨመረ #በረከት #ትግስት #መሪ
No comments:
Post a Comment