እምነት ራሱን የቻለ ልዩ አለም ነው፡፡ እምነት ለየት ያለ አለም ነው፡፡
ተፈጥሯዊ አለም አለ፡፡ መንፈሳዊ አለም አለ፡፡ በተፈጥሮአዊ አምስቱ የስሜት ህዋሳቶች የሚታይ የሚዳሰስ የሚሰማ የሚቀመስ የሚሸተት አለም አለ፡፡ በተፈጥሯዊ አምስቱ የስሜት ህዋሳቶች የማይታይ የማይዳሰስ የማይሰማ የማይቀመስ የማይሸተት አለም አለ፡፡ በተፈጥሯዊው አይን የሚታይ አለም አለ፡፡ በተፈጥሯዊው አይን የማይታይ አለም አለ፡፡ በእምነት አይን የሚታይ አለም አለ፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡17-18
ሰው ምርጫ አለው፡፡ ሰው በተፈጥሯዊው አለም እይታ ለመኖር መወሰን ይችላል፡፡ ወይም ሰው በመንፈሳዊ አለም እይታ ለመኖር መወሰን ይችላል፡፡ ሰው በሚታየው ለመመላለስ ሊወስን ይችላል፡፡ ሰው በማይታየው ለመመላለስ ሊወስን ይችላል፡፡ ሰው በሚታየው ለመኖር መወሰን ይችላል፡፡ ሰው በእምነት ለመመላለስ መወሰን ይችላል፡፡
እንግዲህ ሁልጊዜ ታምነን፥ በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስምና 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5፡6-7
እምነት የሚመጣው በእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡ እምነት የሚመጣው የእግዚአብሄር ቃል በመቀበል ነው፡፡
እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ወደ ሮሜ ሰዎች 10፡17
የእምነት አለም የራሱ ተግዳሮቶች ቢኖሩትም የእምነት አለም የራሱ ክብሮች አሉት፡፡
1. የእምነት አለም የሃይል አለም ነው
ሰው እውነተኛውን ሃይል መለማመድ ከፈለገ በእምነት መኖር አለበት፡፡ እምነት የማይታየውን ማየት ይጠይቃል፡፡ የማይታየውን ማየት ደግሞ ለስጋ አይመችም፡፡ እምነት ስጋን ያናውጣል፡፡ እግዚአብሄርን መንፈስ ነው፡፡ በመንፈሳዊው አለም ከሚኖረው መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሄር ጋር መገናኘት የምንችለው በእምነት ብቻ ነው፡፡ ከእግዚአብሄር መቀበል የምንችለው በእምነት ብቻ ነው፡፡ የእግዚአብሄርን ሃይል የምንካፈለው በእምነት ብቻ ነው፡፡
ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ወደ ዕብራውያን 11፡11
በየእለት ህይወታችን የእግዚአብሄርን የሚያስችል ሃይልና ፀጋ የምንለማመደው በእምነት ነው፡፡
እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። ወደ ዕብራውያን 4፡16
2. የእምነት አለም የሞገስ አለም ነው
ሞገስ የተቀባይነት ሃይል ማለት ነው፡፡ ሞገስ ሲኖረን ተቀባይነትና ተሰሚነት ይኖረናል፡፡ ሞገስ ሲኖረን ሰዎች እሺ ይሉናል ይቀበሉናል፡፡ ሞገስ ሲኖረን ጥያቄያችንን ለመመለስ ሰዎች ይታዘዛሉ፡፡ ሞገስ እንደጥበብ የሚታይና የሚዳሰስ ነገር አይደለም፡፡
ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል። ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና። የያዕቆብ መልእክት 1፡5-6
ሞገስ በእምነት ከእግዚአብሄር የምንቀበለው የማይታይ ነገር ነው፡፡ ታዲያ በእግዚአብሄር ሞገስ የምንወጣውና የምንገባው በእምነት ነው፡፡
ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የማቴዎስ ወንጌል 6፡28-31
3. የእምነት አለም የነፃነት አለም ነው
የሰይጣን አለም መንፈሳዊ አለም ነው፡፡ የሰይጣን እስራት መንፈሳዊ አስራት ነው፡፡ ከባርነት ነፃ መውጣት ካለብን ከባርነት መንፈሳዊ አለም ወደነፃነት መንፈሳዊ አለም እንደተሸጋገርን ማመን አለብን፡፡ የእውነተኛን ነፃነት ትርጉም የምናጣጥመው በእምነት ለመኖር ስንወስን ብቻ ነው፡፡
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1፡13-14
4. የእምነት አለም የእርካታ አለም ነው
ሰው የተፈጠረው ለእምነት ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው የማይታየውን ብቻ ለማየት አይደለም፡፡ ሰው የተፈጠረው የማይታየውንብ እንዲያየ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው የሚታየውን እንዳያየን ነው፡፡ ሰው ምንም ቢኖረው በእምነት መኖር ካልጀመረ በስተቀር እርካታን አያየም፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። የዮሐንስ ወንጌል 3፡36
ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። የዮሐንስ ወንጌል 4፡13-14
5. የእምነት አለም የደስታና የሰላም አለም ነው
ሰው የተፈጠረው በእምነት እንዲኖር በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ እምነት ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት አለም ቢሆንም ነገር ግን በእምነት ውስጥ የሚገኘውን ደስታ በምንም ነገር ልናገኘው አንችልም፡፡ ሰው በእምነት ከእግዚአብሄር ጎን መሆኑን እንደማወቅ የሚያስደስተውና የሚያሳርፈው ነገር የለም፡፡ ሰው እውነተኛን ደስታ ማጣጣም ከፈለገ በሚታይ ነገር ሳይሆን በእምነት ለመኖር መወሰን አለበት፡፡
ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። የዮሐንስ ወንጌል 14፡27
ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሄር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም፡፡ ሰው በምድራዊ ቁሳቁስ እስከኖረ ድረስ በእምነት የሚገኘውን ደስታና ሰላም ሊካፈል አይችልም፡፡ ሁለት ወዶ አይሆንም፡፡ ሰው በምድር ተስፋ ይሆነኛል ብሎ የምድር ገንዘብን እስካልናቀ ድረስ የእምነትን ደስታ ሊያጣጥም አይችልም፡፡
እርሱም መልሶ፦ ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው። የማቴዎስ ወንጌል 4፡4
6. እምነት የገድል አለም ነው
ሰው የተፈጠረው ለገድል ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር ታላላቅ ፈተናዎች እንዲያልፍ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር እንዲያሸንፍ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር እንዲዋጋ እና ድል እንዲነሳ ነው፡፡ ሰው ለቀላልና ለትናንሽ ነገር አልተፈጠረም፡፡ ሰው የተፈጠረው ጥቂት ሰዎች ብቻ ለሚያገኙት የአሸናፊነት ህይወት ነው፡፡
በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤
ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። የማቴዎስ ወንጌል 7፡13
እምነት ውሳኔን ይጠይቃል፡፡ በሁለት ሃሳብ ለሚወላውል ሰው እምነት አይሰራለትም፡፡
ነገር ግን በምንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን፤ የሚጠራጠር ሰው በነፋስ የተገፋና የተነቃነቀ የባሕርን ማዕበል ይመስላልና።ሁለት አሳብ ላለው በመንገዱም ሁሉ ለሚወላውል ለዚያ ሰው ከጌታ ዘንድ አንዳች እንዲያገኝ አይምሰለው። የያዕቆብ መልእክት 1፡6-8
የእምነት አለም ነፍስህን ለማዳን ከመያዝ ይልቅ በእግዚአብሄር እጅ ላይ የምትጥልበት የውርርድ አለም ነው፡፡
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። የማቴዎስ ወንጌል 16፡25
7. የእምነት አለም የክብር አለም ነው
የእምነት አለም እግዚአብሄር ትክክል ነው ብሎ ለእግዚአብሄር ቃል እውቅና መስጠት ነው፡፡ የእምነት አለም ቃሉን በመስማትና በመታዘዝ ለእግዚአብሄር እውቅና መስጠት ነው፡፡ የእምነት አለም የሚታየውን ባለማየት የማይታየውን በማየት እግዚአብሄርን ደስ ማሰኘት ነው፡፡ የእምነት አለም እግዚአብሄርን ማክበር ነው፡፡ የእምነት አለም የተፈጠሩበትን አላማ በመፈፀም ከእግዚአብሄር ጋር የመክበር አለም ነው፡፡
ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና። ወደ ዕብራውያን 11፡6
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#እምነት #ማየት #አለማየት #ቃል #የእምነትተጋድሎ #የእግዚአብሄርቃል #ቃሉንመስማት #ደስታ #ሰላም #እርካታ #ክብር #ገድል #ነፃነት #ሞገስ #ሃይል #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
No comments:
Post a Comment