Popular Posts

Sunday, July 1, 2018

ራእይ ለምን

ለተሳካ ህይወትና ለአገልግሎት ራእይ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ራእይ ከየት እንደመጣን ወዴት እንደምንሄድ ይጠቁመናል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ራእይ ሊጨበጥ የማይችል ሃይማኖታዊ ሃሳብ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች ስለህይወትህ ፣ ስለቤተሰብህ ፣ ስለአገልግሎትህና ስለስራህ ራእይ አለህ? ተብለው ሲጠየቁ ህይወታቸውን የሚያወሳሰብ ሊደረስበት የማይችል ረቂቅ ጥያቄ የተጠየቁ ይመስላቸዋል፡፡ ራእይ ውስብስብ ሊረዱት የማይችሉት ረቂቅ ነገር ይመስላቸዋል፡፡ ስለራእያቸው የሚጠይቃቸው ሰው የሚያካብድና ህይወታቸውን ማወሳሰብ የፈለገ ሰው ይመስላቸዋል፡፡
ራእይ በአጭሩ ምሪት ማለት ነው፡፡ ራእይ ማለት እግዚአብሄር በህይወታችን ፣ በአገልግሎታችን ፣ በስራችንና በትዳራችን ሊሰራ ያለውን ነገር አስቀድሞ የገለጠልን ምሪት ማለት ነው፡፡ ራእይ ማለት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ራእይ አለን ማለት የምንሄድበትን ቦታ እናውቃለን ማለት ነው፡፡ ራእይ ማለት በህይወት የምንከተለውን አቅጣጫ መረዳት ማለት ነው፡፡
ራእይ አለን ማለት እንዳመጣልን አንኖርም ማለት ነው፡፡ ራእይ አለን ማለት ወደነፈሰበት አቅጣጫ እንሄደም ማለት ነው፡፡ ራአየ አለን ማለት ውሃ ላይ እንሚንሳሰፈፍ ቀላል ነገር ውሃው በተንቀሳቀሰበት አቅጣጫ እንንሳፈፍም ማለት ነው፡፡
ራእይ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ለክብሩ ነው የፈጠረን፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን የራሳችንን ነገር አድርገን እንድናልፍ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን የልጅነት ምኞታችንን እንድንፈፅም አይደለም፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን እርሱ በህይወታችን ያለውን አላማ እንድንከተል ነው፡፡ እግዚአብሄር የፈጠረን በራእይ እንድንኖር ነው፡፡
ራእይ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ራእይ ለምን እንዳስፈለገ እንመልከት
በግምት ስለማይሳካልን
በክርስትና የእግዚአብሄርን መሪት ካልተከተልን በግምት አይሳካልንም፡፡ ክርስትና ሰፊ መንገድ አይደለም፡፡ ክርስትና ጥንቃቄን የሚፈልግ ጠባብ መንገድ ነው፡፡ በራእይ መንገድ እንጂ እንደፈለግን ኖረን እግዚአብሄርን አናስደስተውም፡፡
በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። የማቴዎስ ወንጌል 7፡13-14
ለምን እንዳልተጠራን ማወቅ ስላለብን፡፡
በአለም ላይ ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ በአለም ላይ ተከተለኝ ይሳካልሃል የሚሉ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ በአለም ላይ ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ እኛ ማድረግ የምንችለው ደግሞ አንድ ነገርን ብቻ ነው፡፡ በህይወትም የሚሳካልን በብዙ አማራጮች ሳይሆን በአንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በህይወት ያለን ጊዜና ጉልበት የሚበቃው እግዚአብሄር ለጠራን ስራ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ያለጠራንን ለማድረግ የሚበቃ ምንም ትርፍ ነገር የለንም፡፡ ራእይ አስፈላጊ የሆነበት ምክኒያት ለምን እንደተጠራን ብቻ ሳይሆን ለምን እንዳልተጠራን ማወቅ ስላለብን ነው፡፡ ለዚህ እግዚአብሄር ጠርቶኛል እንደምንል ሁሉ ለዚህ እግዚአብሄር አልጠራኝም የምንለው ነገር መኖር አለበት፡፡ ራአይ ያለው ሰው አግዚአብሄር ብሎኛል እንደሚል ሁሉ እግዚአብሄር አላለኝም የሚለውና ምንም መንፈሳዊ ነገር ቢሆን የማያደርገው ነገር አለ፡፡ ራእይ ያለው ሰው ያልተጠራበት ነገር ላይ ጉልበቱን ከማባከን ያርፋል፡፡
ኢየሱስ ሊያደርግ ስላለው ነገር ሁሉ ራእይ ስለነበረው ለዚህ አልተጠራሁም ይል ነበር፡፡  
ከሕዝቡም አንድ ሰው፦ መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው። እርሱም፦ አንተ ሰው፥ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ አንድሆን ማን ሾመኝ? አለው። የሉቃስ ወንጌል 12፡13-14
መንፈሳዊ አገልግሎትም ቢሆን እግዚአብሄር እንድንሰራው የጠራን አገልግሎት አለ እንዳንሰራው የሚፈልገው አገልግሎት ደግሞ አለ፡፡ ያንን መረዳት ባልተጠራንበት ፀጋው በሌለን ቦታ ህይወታችንን እንዳናቃጥል ያደርገናል፡፡
ለማጥመቅ ክርስቶስ አልላከኝምና፥ ወንጌልን ልሰብክ እንጂ፤ የክርስቶስ መስቀል ከንቱ እንዳይሆን በቃል ጥበብ አይደለም። 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡17
ራእትይ በጣም ወሳኝ የሆነበት ምክንያት ግባችን ስንደርስ እንድናውቅ ነው
ራእይ የሌለው ሰው ወደግቡ አነጣጠሮ ከመወርወር ይልቅ ከወረወረ በኋላ ይህ ነበር ግቤ ብሎ ያከብበታል፡፡ ራእይ የምንሄድበትን መንገስ ያሳያል ራእይ የህይወት ግብን ይሰጠናል፡፡ ራእይ የሌለው ሰው እና የሚሄደበትን የማያውቅ ሰው ሲደርስ አያውቅም፡፡ ራእይ የሌለው ሰው እንደደረሰ ስለማያውቅ እርካታ የለውም፡፡
በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ 2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4፡6-7
ራእይ የሌለው ሰው ሁኔታዎች ሲቃረኑ ራእዩን ያያል
ራእይ ያለው ሰው ሁኔታዎች እንደተፈለገው በማይሄዱት ጊዜ ተስፋ እንዳይቆርጥ ራእዩ ተስፋ ይሆነዋል፡፡ ሁኔታው ተስፋ ሲያስቆርጥ በራእዪ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ወደ ሮሜ ሰዎች 4፡18
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር   share ማድረግ ቢወዱ
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ራዕይ #ምሪት #የእግዚአብሄርአጀንዳ #የእግዚአብሄርፈቃድ #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment