Popular Posts

Follow by Email

Wednesday, July 18, 2018

የሰው የጥላቻ ችግር የእግዚአብሔር ችግር ነው

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ፍፁም ተደርጎ ነው፡፡ ሰው እንደተፈጠረበት አላማ እግዚአብሄርን እየታዘዘ እግዚአብሄርን እየሰማ ይኖር ነበር፡፡ ሰው በህይወቱ ምንም ችግር አልነበረበትም፡፡
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ኦሪት ዘፍጥረት 1፡27
በሰው ህይወት ውስጥ ችግር የተጀመረው ሰው እግዚአብሄር አትብላ ያለውን ያንኑ ፍሬ በመብላት ከእግዚአብሄር ጋር ችግር ውስጥ በወደቀበት ጊዜ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ችግር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ምንም ችግር በህይወቱ አልነበረም፡፡
ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ። የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፥ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤ የበለስንም ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ። ኦሪት ዘፍጥረት 3፡6-7
ሰው የተፈጠረው በየዋህነት እግዚአብሄርን በፍፁም እያመነ እየተደገፈው በመታዘዝ እንዲኖር ነበር፡፡ ሰው ግን የሰይጣንን ምክር በመስማት እግዚአብሄር ላይ ያለውን እምነት አጣው፡፡ ሰው ሃሳቡ ተበላሸ ለእግዚአብሄር ያለው ቅንነት ተመታ፡፡ ሰው በእግዚአብሄ ላይ በማመፁ ለከእግዚአብሄ ጋር ተጣላ፡፡
ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 11፡3
በሰው ህይወት ውስጥ ጦርና ጠብ የተጀመረው ሰው በእግዚአብሄር ላይ በማመፁ ነው፡፡ የሰው የጦርና የጠብ ችግር የመነጨው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሰላሙን ሲያጣ ሰው ከራሱ ጋር ሰላም አጣ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሲጣላ ከሰው ጋር ተጣላ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሰላሙን ሲያጣው ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ጋር ሰላምን አጣ፡፡
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ሰላም የነበረ ጊዜ ሰው ከራሱ ጋር ያለው ግንኙነትና ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት ሰላም ነበረ፡፡ አሁንም ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ሰላም ሲሆን ሰው ከራሱ ጋር ያለው ግንኙነትና ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት ሰላም ይሆናል፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም ካልሆነ ከራሱ ጋር እንዲሁም ከሌላ ሰው ጋር ሰላም አይሆንም፡፡
መፅሃፍ ቅዱስ በሰው ዘንድ ጦርና ጠብ የሚመጡበትን ምንጭ ሲናገር ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት መበላሸት ጦርና ጠብና እንደሚያመጣ ይናገራል፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር ሰላም የሌለው ሰው ለማንም ሰላም ሊሰጥ አይችልም፡፡
በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? ትመኛላችሁ ለእናንተም አይሆንም፤ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፥ ልታገኙም አትችሉም፤ ትጣላላችሁ ትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም፤ ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም። የያዕቆብ መልእክት 4፡1-3
ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን ግንኙነት ሲያስተካክል በህይወቱ ያሉት ሌሎች ግንኙነቶች ሁሉ ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን ግንኙነት ሲዛባ ሌሎች ግንኙነቶች ሁሉ ይዛባሉ፡፡
ሰው የጥላቻ ችግር የተጀመረው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው የጥላቻ ችግሩ የሚፈታው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ሲስተካከል ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄርን የሚወድና ከእግዚአብሄር ጋር ያልተጣላ ሰው ሰውን ይወዳል ከሰውም ጋር አይጣላም፡፡ ሰው ሰውን የሚወደውና ከሰው ጋር የማይጣላው እግዚአብሄርን እንደሚገባ ሲወድ ነው፡፡
ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡20
ከሰው ጋር የሚጣላ ሰው በሆነ መልኩ መጀመሪያ ከእግዚአብሄር ጋር በሆነ ነገር አልተግባባም፡፡ ሰው ቢጣላችሁ በእናንተ አልጀመረም፡፡ እናንተን እንዲጣላችሁ ያደረገው ያ ጥል የመነጨው ከእግዚአብሄር ጋር ሰላምን በማጣትና ከእግዚአብሄር ጋር በመጣላት ነው፡፡
ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። የዮሐንስ ወንጌል 15፡18
የሰው የጦርና የጠብ ችግር ከስር መሰረቱ የሚፈታው ከእግዚአብሄር ጋር እንጂ ከሰው ጋር አይደለም፡፡ ከሰው ጋር ያለው ጦርና ጠብ ፍሬው እንጂ ስሩ አይደለም፡፡
ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። የማቴዎስ ወንጌል 12፡33
ሰው ከሰው ጋር ያለውን ችግር በቴክኒክና በታክቲክ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለውን ግንኙነት ቢያስተካከል ሌሎች ሁሉ ግንኙነቶች ይስተካከላሉ፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሰላም #እምነት #ሃሳብ #ጥበብ #ማስተዋል #እግዚአብሔርንመፍራት #ምንጭ #ክፉ #ጦር #ጠብ #መልካም #ፍርድ #እውቅና #ፍፁም #ችግር #መፍትሄ #አላማ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ  #እምነት #ቃል  #ማደስ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment