Popular Posts

Tuesday, July 31, 2018

የሁለቱ አለማት ጉዞ

በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡8-9
ክርስትና የሁለት አለም ጉዞ ነው፡፡ ክርስትና በአንድ በኩል በሰማያዊ ስፍታ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የመባረክ ስልጣን ነው፡፡ በሌላ በኩል ክርስትና የዚህ አለም ገዢ በሚገዛበት በምድር ላይ በተግዳሮት የመኖርና የእግዚአብሄርን መንግስት የማስፋት የእንግዳ አለም ተልእኮ ነው፡፡ በሰማያዊ ስፍራ መባረክና የህይወት ተግዳሮት ሁለቱ እርስ በእርሳአቸው የሚቃወሙ ሃሳቦች አይደሉም፡፡ ተግዳሮቱን በአሸናፊነት የምንወጣው በሰማያዊ ስፍራ ስለተባረክን ነው፡፡ ተግዳሮቱ ሁሉ የመጣብን ተግዳሮቱን ተቋቁመን የምናልፍበት በረከት ሁሉ በህይወታችን ስላለን ነው፡፡ ሁለቱ እርስ በእርሳቸው የሚደጋገፉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ አንዱን ብቻ ከለጠጥነው እንስታለን ሁለቱንም በሚዛናዊነት ከያዝነው እንበረታለን፡፡  
ክርስትና በአንድ በኩል የእግዚአብሄር ልጅነት ስልጣን ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ የዮሐንስ ወንጌል 1፡12
ክርስትና ከሞት የመነሳትና ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊ ስፍራ የመቀመጥ መንፈሳዊ ማእረግ ነው፡፡
በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2፡6-7
ክርስትና የንጉሱ የእግዚአብሄር ቤተሰብነት ማእረግ ነው፡፡ ክርስትና የነገስታት ቤተሰብን አባልነት ስልጣን ነው፡፡
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 2፡9
ክርስትና በጠላት ሃይል ሁሉ ላይ ያለ ታላቅ ስልጣን ነው፡፡
እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። የሉቃስ ወንጌል 10፡19
ክርስትና የእግዚአብሄር ሙሉ እርዳታ ያለበት የምድር ጉዞ ነው፡፡ ክርስትና ብዙ እንቅፋቶች ያሉበት የተግዳሮትም ጉዞ ነው፡፡
ታላቅ መዝገብ በህይወታችን አለ ነገር ግን ለሰው የሚደርሰው መከራ ሁሉ ደግሞ ይደርስብናል፡፡  
ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ 2 ቆሮንቶስ 47-9
1.      በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም
እግዚአብሄር ስለጠራን ብቻ ሁሉም ነገር ፀጥ ብሎ አይገዛልንም፡፡ ነገሮች የሚገዙልን በሃይል ነው፡፡ ሁሉም ነገር አቅማችንን የሚፈትሽ ይመስላል፡፡ ሁሉም ነገር ይፈታተነናል፡፡ ሁሉም ነገር ይገፋናል፡፡ ሁሉም ነገር አገራችን እንዳይደለ ያስታውሰናል፡፡ ሁሉም ነገር እንደማይወደን እንደማይቀበለን ተቃውሞውን ባገኘው አጋጣሙ ሁሉ ያሳየናል፡፡
ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። የማቴዎስ ወንጌል 11፡12
ነገር ግን የሚያስጨንቀንን በእርሱ ላይ ስለምንጥል አንጨነቅም፡፡ የእግዚአብሄርን መንግስትና ፅድቁን ስንፈልግ ሁሉ ነገር ስለሚጨመርልን አንጨነቅም፡፡ እኛ የእግዚአብሄርን ስራ ስንሰራ እርሱ የእኛን ስራ ስለሚሰራ ለእግዚአብሄር መንግስት ስራ እንጂ ለጭንቀት ጊዜ የለንም፡፡ ሁሉም ይገፋናል በማንም አንጨፈለቅም፡፡
ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።  ወደ ሮሜ ሰዎች 8፡35-37
2.       እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም
እግዚአብሄር እረኛችን ነው ሁልጊዜ ይመራናል፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ ነገሮች ሁሉ ጥቁርና ነጭ ሆነው በግልፅ አይታዩንም፡፡ አንዳንዴ እናመነታለን፡፡ አንዳንዴ ግራ እንጋባለን፡፡ አንዳንዴ ያልተመለሰ ጥያቄ ይኖረናል፡፡ አንዳንዴ እግዚአብሄር ለዚህ አሳልፎ አይሰጠኝም ያልነው ነገር ይደርስብናል፡፡ አንዳንዴ አስበን የማናውቅው መከራ ውስጥ እናልፋለን፡፡ አንዳንድ ነገሮች እንቆቅልሽ ይሆኑብናል፡፡ ነገር ግን በልባችን ያለው የተስፋ ድምፅ ከማመንታታችን ድምፅ ይበልጣል፡፡
ዘርህ እንዲሁ ሊሆን ነው እንደ ተባለ፥ ተስፋ ባልሆነው ጊዜ የብዙ አሕዛብ አባት እንዲሆን ተስፋ ይዞ አመነ። ወደ ሮሜ ሰዎች 4፡18
በተስፋ ደስ ስለሚለን በመከራ እንታገሳለን፡፡
በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 12፡12
የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡3-4
3.       እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም
የሚያሳድዱን አሉ እንጂ የሚቀበሉን አልጠፉም፡፡ የማይፈልጉን አሉ እንጂ በክብር የሚፈልጉን ብዙ አሉ፡፡ በውስጣችን ያለውን የሚንቁ አሉ እንጂ በውስጣችን ያለውን የእግዚአብሄርን ፀጋ የሚያውቁና የሚያደንቁ ሁልጊዜ አይጠፉም፡፡ ፊታችንን ማየት የማይፈልጉ አሉ እንጂ ፊታችንን ለማየት የሚናፍቁ አይጠፉም፡፡ ንግግራችንን የሚጠሉ  አሉ እንጂ የአፋችንን ቃል በጉጉት የሚጠብቁ የሚወዱን በዘመናት መካከል አይጠፉም፡፡
በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው? 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡15-16
ቢቻልስ ዓይኖቻችሁን አውጥታችሁ በሰጣችሁኝ ብዬ እመሰክርላችኋለሁ። ወደ ገላትያ ሰዎች 4፡15
4.       እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ነው ማለት አንወድቅም ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሄር አባታችን ነው ማለት እንወድቃለን አንጂ አንጠፋም ማለት ነው፡፡ ጠፉ ስንባል እንበዛለን፡፡ ሞቱ ስንባል በትንሳኤ እንነሳለን፡፡ ለጊዜው ሊጥለን እንጂ እግዚአብሄር ሃይላችን ስለሆነ ሊያጠፋን የሚችል ሃይል ከሰማይ በታች የለም፡፡
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። የዮሐንስ ወንጌል 12፡24
አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡8-10
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ  Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ክብር #መዋረድ #መከራ #ፈተና #ሞት #በሁሉ #እንገፋለን #አንጨነቅም #እናመነታለን #ተስፋአንቆርጥም #እንሰደዳለን #አንጣልም #እንወድቃለን #አንጠፋም #ህይወት #ስጋ #መፅናት #መታገስ #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ብፅእና #እምነት #አንድነት #ፀጋ  #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

Monday, July 30, 2018

ለሽማግሌዎች ተገዙ

እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡5-6
ሰው ለእግዚአብሄር እንደሚገዛ የሚታወቀው ለሰው ሲገዛ ነው፡፡  እግዚአብሄር በየደረጃው በህይወታችን ላይ ያስቀመጣቸው ባለስልጣኖች አሉ፡፡ እግዚአብሄር ከእናትና አባት ጀምሮ እስከ መንግስት ባለስልጣናት ድረስ እንዲመሩን ባለስልጣኖችን በህይወታችን ላይ አስቀምጧል፡፡
እግዚአብሄር በየደረጃው ያስቀመጣቸውን ባልስልጣናት መቃወም የእግዚአብሄርን ስርአት መቃወም ነው፡፡ እግዚአብሄር በየደረጃው በቤተሰብ በቤተክርስትያን በስራ ቦታ በህይወታችን ላይ ያስቀመጣቸውን ሰዎች መቃወም እግዚአብሄርን መቃወም ነው፡፡ እግዚአብሄር ከቤተሰብ እስከ መንግስትና ቤተክርስትያን በህይወታችን ላይ የሾማቸውን ባለ ስልጣናት ያለመታዘዝ ችግር እግዚአብሄርን ያለመታዘዝ ችግር ነው፡፡ እግዚአብሄር ከቤተሰብ እስከ ቤተክርስትያን በእኛ ላይ ያስቀመጣቸውን ባለስልጣናት አለማክበር እግዚአብሄርን አለማክበር ነው፡፡ እግዚአብሄር በየደረጃው ከቤት እስከ መንግስት በእኛ ላይ በየደረጃው ያስቀመጣቸውን መሪዎች መናቅ እግዚአብሄርን መናቅ ነው፡፡
ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 13፡1-2
ሰው የእግዚአብሄርን ስልጣን እንደሚያከብር የሚታየው እግዚአብሄር በህይወቱ ያስቀመጣቸውን ባለስልጣናት በማክበሩ ነው፡፡ ያየውን ሰውን ያላከበረ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊያከብር እንዴት ይችላል?
ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 4፡20
የሰው የስልጣን አለማክበር የሚጀምረው የሰውን ስልጣን ባለ ማክበት አይደለም፡፡ የሰው የሰውን ስልጣን አለማክበት የሚጀምረው የሰው የእግዚአብሄር ስልጣን ባለ ማክበት ነው፡፡ የሰው የእግዚአብሄርን ስልጣን አለማክበር ምልክቱ የሰው የሰውን ስልጣን አለማክበር ነው፡፡
ሰው አመፅን በቤተክርስትያን ሽማግሌዎች ወይም በሌሎች ባለስልጣኖች ላይ በማመፅ አይጀምርም፡፡ ሰው አመፅን የሚጀምረው በእግዚአብሄር ላይ በማመፅ ነው፡፡ የሰው ለቤተክርስተያን ሽማግሌዎች አለመገዛት ችግር ለእግዚአብሄር አለመገዛት ችግር ነፀብራቅ ነው፡፡ የሰው ለቤተክርስትያን መሪዎች አለመገዛት ችግር መፍትሄ የሚያገኘው የሰው ለእግዚአብሄር የመገዛት ችግር ሲፈታ ነው፡፡
ስለዚህ ነው መፅሃፍ ቅዱስ ለሽማግሌዎች ተገዙ ካለ በኋላ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ የሚለው፡፡ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሱን ያዋረደ ሰው ለሽማግሌዎች መገዛት ይችላል፡፡ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ማዋረድ ራሱን ያስለመደ ሰው ለሽማግሌዎች መገዛት አይከብደውም፡፡ ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሱን ያላዋረደ ሰው ግን ለሽማግሌዎች መገዛት አይችልም፡፡ የሰው ለሽማግሌዎች የመገዛት ችግር የሚፈታው የሰው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሱን የማዋረድ ችግሩ ሲፈታ ብቻ ነው፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡5-6
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #መገዛት #ሽማግሌ #ባለስልጣን #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

የትዳር ችግር የእግዚአብሄር ችግር ነው

የህይወትና የአገልግሎት ችግሮች ሁሉ የሚመነጩት ከእግዚአብሄር ችግር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሄር ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ ሰው ሲፈጠር ከእግዚአበሄር ጋር የነበረው ግንኙነት ፍፁም ነበር፡፡ ሰው ሃጢያትን ሲሰራ ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት በመበላሸቱ ሰው ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት ተበላሸ፡፡
የሰው ችግር የጀመረው ከእግዚአብሄር ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት መልካም እከነበረ ድረስ የሰው ግንኙነቶች ሁሉ መልካምና የተሳኩ ነበሩ፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ከተበላሸ በኋላ ከማንም ከጋር ያለው ግንኙነት ሊስተካከል አልቻለም፡፡
አሁንም የሰው ግንኙነት መስተካካል ካለበት የሚጀመረው ከእግዚአብሄር ጋር ባለው ግንኙነት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኘኙነት የሁሉም ግንኙነቶች መሰረት ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ሳይሳካ ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት ይሳካል ማለት ዘበት ነው፡፡
የሰው የግንኙነት ችግር ምንጩ የሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ችግር ነው፡፡ የሰው ከእግዚአብሄር ጋር ያለው ግንኙነት ችግር መፈታት የሰውን ማንኛውም የግንኙነት ችግሮች ይፈታል፡፡
የትዳር ችግር የእግዚአብሄር ችግር ነው፡፡
በትዳር ሚስት ለጌታ እንዴት እንደምትገዛ ካወቀች ለባልዋ እንዴት እንደምትገዛ ታውቃለች፡፡ ሚስት ለባልዋ የመገዛት ችግር ምንጩ የሚስት ለጌታ የመገዛት ችግር ነው፡፡  የሚስት ለጌታ የመገዛት ችግሯ መፍትሄ ሲያገኝ ሚስት ለባልዋ የመገዛት ችግሯ መፍትሄ ያገኛል፡፡ ሴት ለጌታ በመገዛት ከሰለጠነች ለባልዋ ለመገዛት አይቸግራትም፡፡ ሴት ለጌታ በመገዛት ምሳሌነት ለባልዋ መገዛት ትችላለች፡፡ ሴት ለጌታ በመገዛት ልምዷ ለባልዋ መገዛት ትችላለች፡፡
ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡21-22
ባል ሚስቱን የመውደድ ችግር የእግዚአብሄር ፍቅር ችግር ነው፡፡ ባል በእግዚአብሄር እንዴት እንደተወደደ ካላወቀ ሚስቱን እንዴት እንደሚወድ አያውቅም፡፡ ባል በእግዚአብሄር በመወደድ ልምዱ ሚስቱን ሊወድ ይችላል፡፡ ባል ከእግዚአብሄር ጋር ባሳለፈው የመውደድና የመወደድ ምሳሌነት ሚስቱን መውደድ ይችላል፡፡ ባል በጌታ እንዴት እንደተወደደ ሲረዳ ሚስቱን እንዴት እንደሚወድ ያውቃል፡፡ ባል በእግዚአብሄር በተወደደበት ፍቅር ጉልበት ሚስቱን ይወዳል፡፡
ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡25-26
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ህይወት #ጋብቻ #ትዳር #ባል #ሚስት #ፍቅር #መውደድ #መታዘዝ #ይተዋል #ይጣበቃል #አንድስጋ #እውነት #ትህትና #ትንሳኤ #ህይወት #ወንጌል #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

Sunday, July 29, 2018

እግዚአብሄር የሚያደርገው እንደዚህ ነው

ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። የያዕቆብ መልእክት 4፡6
እግዚአብሄር ከትእቢተኛ ጋር ምንም የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ እግዚአብሄር ከትእቢተኛ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ እግዚአብሄር ከትእቢተኛ ጋር ምንም ቅርርብ የለውም፡፡ እግዚአብሄር ከትእቢተኛ ጋር ምንም ዝምድና የለውም፡፡ እግዚአበሀር ቅዱስ ነው ትእቢትን ይፀየፋል፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛን መቅረብ እንኳን አያስፈልገውም፡፡  እግዚአብሄር ትሁት ነው ኩሩ መንፈስን ከሩቅ ይለየዋል፡፡
እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል። መዝሙረ ዳዊት 138፡6
እግዚአብሄር ለትእቢተኛ ያው አንድ ነገር ተቃውሞ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለትእቢተኛ የሚሰጠው አንድ ነገር የተቃውሞ ስጦታ ነው፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛ እንዳይሳካለት ይሰራል፡፡ እግዚአብሄር የትእቢተኛን መንገድ ይዘጋል፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛ እንዳይከናውንለት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያደርጋል፡፡
እግዚአብሄር የማይረዳው የተቸገረ ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄር የማያነሳው የተዋረደ ሰው የለም፡፡ እግዚአብሄር ከፍ የማያደርገው ዝቅተኛ ሰው የለም፡፡ ትእቢተኛን ግን ከመቃወም ውጭ ፍላጎቱን እንዲያሟላ የሚረዳው ምንም ነገር የለም፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 5፡5-6
እግዚአብሄር ትእቢተኛን ይቃወማል ለትሁታን ግን ፀጋን ይሰጣል፡፡
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። የያዕቆብ መልእክት 4፡6
እግዚአብሄር የትእቢተኛን መንገዱን ይዘጋል ለትሁታን ግን የተዘጋ በርን ይከፍታል፡፡ እግዚአብሄር ትእቢተኛን ሞገስ ያሳጣዋል ለትሁታን ግን ሞገስ ይሆናቸዋል፡፡
በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። መጽሐፈ ምሳሌ 3፡34
እግዚአብሄር ትእቢተኛን አይረዳም ለትሁታን ሃይል ይሆናቸዋል፡፡ በትሁታን ቦታ የራሱን ሃይል መግለጥ እግዚአብሄር ይወዳል፡፡
እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና። አሁንም ስንፍና አድርገሃል፥ ስለዚህም ከዛሬ ጀምሮ ሰልፍ ይሆንብሃል። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 16፡9
እግዚአብሄር ትእቢተኛን ያዳክማል ትሁታንን ያበረታል፡፡
አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። የኃያላንን ቀስት ሰብሮአል፥ ደካሞችንም በኃይል ታጥቀዋል። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2፡3-4
እግዚአብሄር ትእቢተኛን ያዋርዳል ትሁታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡  
ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል። የማቴዎስ ወንጌል 23፡12
ሰው ትእቢቱ ከክብር ያዋርደዋል፡፡ ሰው ትህትናው ከውርደት ያከብረዋል፡፡
ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ መንፈሱን የሚያዋርድ ግን ክብርን ይቀበላል። መጽሐፈ ምሳሌ 29፡23
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ

ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 47
እግዚአብሄር ትሁት እንድንሆን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሄር እንድመካ አይፈልግም፡፡ ሰው የተሰጠውን ስጦታ የራሱ እንደሆነ ከመጀመሪያውም እንደነበረው እንዲያስመስል እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ተቀብሎ እንዳልተቀበለ እንዲመካ እግዚአብሄር አይፈልግም፡፡  
እግዚአብሄር ታላላቅ መዝገቦችን በውስጣችን አስቀምጧል፡፡
የእግዚአብሄር መንፈስ በእኛ ውስጥ ይኖራል፡፡
ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።  1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 6፡19-20
እግዚአብሄር መንፈሱን ሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሄር ቅባትን ሰጥቶናል፡፡ የቀባን እግዚአብሄር ነው፡፡
በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡20-21
እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፥ ሁሉንም ታውቃላችሁ። እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ። 1ኛ የዮሐንስ መልእክት 2፡20፣27
እግዚአብሄር ስጦታዎችን ሰጥቶናል፡፡
ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 4፡10-11
እግዚአብሄር የተለያዩ አገልግሎቶችን በእኛ ውስጥ አስቀምጧል፡፡
እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፡11
የእግዚአብሄር ሃይል ታላቅነት ከእኛ እንዳልሆነ የሚያሳውቀው ታላቁ ሃይል ታላቅ እቃ ውስጥ ስላልተቀመጠ ነው፡፡ ታላቁ ሃይል ታላቅ እቃ ውስጥ ቢቀመጠ ኖሮ ሰው የሃይሉ ታላቅነት ከእኛ የሆነ ይመስለው ነበር፡፡ ታላቅ መዝገብ በታላቅ እቃ ውስጥ ቢቀመጥ ኖሮ እኛም የሃይሉ ታላቅነት ከእኛ እንደሆነ ይመስለን ነበር፡፡
ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡7
በውስጣችን ያለው መልካም ነገር ሁሉ የተቀበልነው እንደሆነና የእኛ እንዳልሆነ ግልፅ ምልክት አለው፡፡ በውስጣችን ያለው ይህ መዝገብ ከእኛ እንዳልሆነ የሚያሳየው መዝገቡ የተቀመጠው በከበረ እቃ ውስጥ ሳይሆን በሸክላ እቃ ውስጥ ነው፡፡ እግዚአብሄር የከበረውን መዝገብ በእኛ ውስጥ ያስቀመጠው በሚሰበር በሸክላ እቃ ውስጥ ነው፡፡
ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን ምንም ሰው የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ያውቃል፡፡ ይህ ታላቅ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ስለ አለን እኛም የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ከጊዜ ወደጊዜ ያስታውሰናል፡፡
አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #ያልታወቁ #የታወቅን #የምንሞት #ሕያዋን #የተቀጣን #አንገደልም  #ኀዘንተኞች #ደስ #ድሆች #ባለጠጎች #የሌለን  #ሁሉየእኛነው #ጭንቀት #የባለጠግነትማታለል #የኑሮሃሳብ #የእለትእንጀራ #የባለግነትምቾት #ዘር #መሰረታዊፍላጎት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

Saturday, July 28, 2018

ትእቢት ለምን

የእግዚአብሄር ቃል ስለ ትእቢት አስከፊነት ብዙ አስፈሪ ነገሮችን ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር ትዕቢተኞችንም ከሩቅ እንደሚያውቅ መፅሃፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል። መዝሙረ ዳዊት 138፡6
እግዚአብሄር ስለትእቢት ውጤት የተረጋገጠና እርሱም ውድቀት እንደሆነ ያስተምራል፡፡
እገዚአብሄር ብዙ አላዋቂ ሰዎችን ያስተምራል ይለውጣል፡፡ እግዚአብሄር የተለያየ ችግር ላለባቸው ሰዎች እነርሱን የሚያነሳበት መፍትሄ አለው፡፡ እግዚአብሄ ግን ለትእቢተኛ ማድርግ የሚችለው አንድ ነገር መቃወም ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሄር ግን ለምንድነው ግን እግዚአብሄር ትእቢኛን እንደዚህ የሚቃወመው ብለን መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡
1.      ትእቢተኝነት ሰይጣንን መከተል ነው
ሰይጣን ከእግዚአብሄር ዘንድ የተጣለው በትእቢቱ ነው፡፡ ትእቢተኝነት ሰይጣንን ማድነቅ ነው፡፡ ትእቢት ሰይጣንን እንደ ምሳሌ መከተል ነው፡፡ ሰይጣን እግዚአብሄር የሰጠውን ስልጣን በመናቅና አንደኛ ለመሆን በመመኘት የእግዚአብሄርን ስልጣን በመፈለጉ ከሰማይ ተጣለ፡፡
አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቈረጥህ! አንተን በልብህ፦ ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። ትንቢተ ኢሳይያስ 14፡12-15
እግዚአብሄር ትሁት ነው፡፡ ትእቢተኝነት የእግዚአብሄርን ትህትና ሳይሆን የሰይጣንን ትእቢት መከተል ነው፡፡
መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል። የይሁዳ መልእክት 1፡6
2.     ትእቢተኝነት የተፈጠሩበትን አላማ መሳት ነው
እኛ ስንፈጠር ለእግዚአብሄር እየተገዛንና እያመለክነው በትህትና እንድንኖር ነው፡፡ ሰው ግን የተፈጠረበትን አላማ ሲስት እግዚአብሄር ከመቃወም ውጭ ከሰው ጋር ምንም ግንኙነት ማድረግ አይፈልግም፡፡ ሰው ትህትናውን ሲጥል እግዚአብሄር ሊጠቀምበትም ይቅርና አብሮት ምንም ነገርን ሊያደርግ አይችልም፡፡
እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው፦ ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና። ኦሪት ዘፍጥረት 2፡16-17
ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? ትንቢተ ሚክያስ 6፡8
3.     ትእቢት መልከ ጥፉነት ትህትና ውበት ነው
እግዚአብሄር የፈጠረው ሰው ሁሉ ውብ ነው፡፡ እግዚአብሄር ውብና ድንቅ ተደርጎ ያልተፈጠረ ሰው የለም፡፡ ነገር ግን ሰው ሰይጣንን ተከትሎ ውበቱን ሲያጣው አስቀያሚ ይሆናል፡፡ ሰው ትእቢተኛ ሲሆን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረውን የልቡን ውበት ያጣዋል፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡4
4.     ትእቢተኝነት በራስ ሃይል መተማመን ነው
ሰው በጉልበቱ ካልታመነ ትሁት ይሆናል፡፡ ሰው ግን በራሱ ጉልበት ከተማመነ ትእቢተኛ ይሆናል፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፦ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 9፡23-14
5.     ትእቢተኝነት ለእግዚአብሄር እምላክነት እውቅና አለመስጠት ነው
ትእቢተኝነት በራስ ላይ ራስ ጌታ መሆን ነው፡፡ ሰው የሚሳካለት እግዚአብርን አምላክነት እውቅና ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡
የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች 1፡20-21
6.     ትእቢተኝነት እግዚአብሄርን አላዋቂ ራስን አዋቂ ማድረግ ነው፡፡
ትእቢት ከእግዚአብሄር በላይ የአዋቂነት ስሜት ነው፡፡ ካለአዋቂነት ስሜት ሰው ትእቢተኛ ሊሆን አይችልም፡ 
አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2፡3
ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል። 1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8፡1
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ትህትና #መዋረድ #ባህሪ #ዝቅታ #ትዕቢት #ትምክህት #መመካት #ኢየሱስ #ጌታ #መሪነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ