እግዚአብሄር የአላማ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት እንደዚህ ሰውን እንፍጠር ብሎ እንዳቀደና እንደፈጠረ
ሁሉ እኛም ሳንወለድ በፊት የተወለድንበት አላማ ነበረ፡፡ እንጂ በምድር ላይ የተወለድነው በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ ከተወለድን
በኋላ አይደለም የህይወት አላማ የተፈለገልን ፡፡ ከመወለዳችን በፊት የነበረን አላማ ለመፈፀም ተወልደናል፡፡
በምድር ላይ ሰርተን ለመፈፀምና ለእግዚአብሄር ክብር የምናመጣለት ከመወለዳችን በፊት የነበረ የመኖራችን ልዩ ምክኒያት
ነበረ፡፡
እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ ዮሃንስ 17፡4
ስለዚህ በማለዳ ከአልጋችን የሚያስነሳን እግዚአብሄርን የማክበር አላማን የመፈፀም ረሃብ እንጂ የምግብ ረሃብ አይደለም፡፡
ከአልጋችን የሚቀሰቅሰን ሰዎችን የማገልገል ጥማት እንጂ ለራስ መኖር አይደለም፡፡ ከአልጋችን የሚያስነሳን እግዚአብሄርን በምድር
ለማክበር ያለብን መቃጠል እንጂ የሚበላና የሚጠጣ ፍላጎት አይደለም፡፡
እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ማቴዎስ 6፡31-32
በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው ሁሉ የሚበላውንና የሚጠጣውን ይፈልገዋል፡፡ አህዛብ በምድር ላይ ዋነኛ አላማቸው መብላት
መጠጣት እንደ ማንኛውም ሰው ኖሮ ኖሮ መሞት ነው፡፡ እንዲያውም አህዛብ ከሚበላና ከሚጠጣ በስተቀር እግዚአብሄርን የማክበር ምንም
አላማ የላቸውም፡፡
እየሱስ አህዛብ የሚኖሩለት የህይወት አላማ የእናንተም የኑሮ አላማ መሆን የለበትም እያለ ነው፡፡ እግዚአብሄርን ከማክበር
የህይወት አላማችን ጋር ሲተያይ ይህ ለእኛ ተራ ነገር ነው፡፡ ይህ ለእግዚአብሄር ልጆች አይመጥንም፡፡ ይህ ለእግዚአብሄር ክብር
ለሚኖሩ ሰዎች አይገባም፡፡ ይህ ለእግዚአብሄር ለሚኖሩ ሰዎች ከመለኪያ ደረጃ በታች የሆነ የህይወት ደረጃ ነው፡፡
ይህንስ
ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ማቴዎስ 6፡32-32
No comments:
Post a Comment