Popular Posts

Friday, July 1, 2016

ጣሉት





የህይወት ስጦታ ሃላፊነትም ነው፡፡ በተለያየ አቅጣጫ ብዙ የህይወት ሃላፊነቶች አሉብን፡፡ አንዳንዶቹ ሃላፊነቶች የሚያስጨንቁ ናቸው፡፡ ጭንቀት ደግሞ መከራ ነው፡፡ መጨነቅ እስራት ነው፡፡ መጨነቅ በህይወት አለመደሰት ነው፡፡ ጭንቀት ክፉ ነው፡፡ 


አለመጨነቅ ማለት ለህይወት አለማቀድና አለማሰብ ማለት አይደለም፡፡ የማይጨነቅ ሰው ስናይ በህይወቱ ተስፋ የቆረጠ ሁሉ ሊመስለን ይችላል፡፡ ምክኒያቱም ስንጨነቅ ውጤት ባይኖረውም ስራ የሰራንና ውጤት ያገኘን ስለሚመስለን ነው፡፡ ስንጨነቅ ወደፊት የሄድን ወይም ቢያንስ የሞከርን ይመስለናል ስለዚህ በጭንቀታችን እንፅናናለን፡፡ 


ነገር ግን መጨነቅ ፍሬ የሌለውና እንዲያውም ጊዜያችንን ጉልበታችንን ሁሉ በከንቱ የሚበላና የሚያደክም ነገር ነው፡፡
መጨነቅ ማለት እግዚአብሄር ብቻ ማድረግ የሚችለውን እኛ ማድረግ የማንችለውን ነገር ለማድረግ መጣጣር ነው፡፡ መጨነቅ ማለት ልክን አለማወቅ ከአቅም በላይ መፍጨርጨር ነው፡፡ መጨነቅ ማለት የራስን ድርሻ ትቶ የእግዚአብሄርን ድርሻ ለመስራት መሞከር ነው፡፡ 

እግዚአብሄር የእርሱን ድርሻ ለመስራት እንድንሞክርም እንኳን አይፈልግም፡፡ ምክኒያቱም እንደማንችለው ስለሚያውቅ ነው፡፡ የእርሱን ድርሻ ለመስራት ስንሞክር መስራት የምንችለውን የራሳችንን ድርሻ መስራት ያቅተናል ፡ ከሁለት ያጣ እንሆናልን ፡፡ ውጤቱም ውድቀት ብቻ ይሆናል፡፡  

እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7

አትጨነቁ ሲባል የሚመስለን የህይወት ሃላፊነታችሁን ተዉት መሬት ላይ ጣሉት ማለት ስለሚመስለን ባንችለውም እስከመጨረሻው ለመታገል እንመርጣለን፡፡ አትጨነቁ ማለት ግን ነገራችሁን በተሻለ በእግዚአብሄር እጅ ላይ ጣሉት ማለት ነው እንጂ በመሬት ላይ ጣሉት ማለት አይደለም፡፡ 

የእኛ የስራ ድርሻ ስላይደለ ለእኛ የማንችለው ሸክም የሆነው ነገር ለእግዚአብሄር ግን የስራ ድርሻው ስለሆነ ሃሳብ እቅድ እንጂ ጭንቀት አይሆንበትም፡፡  እግዚአብሄር የተሻለ ሃሳቢ ብቻ ሳይሆን እኛ መስራት የማንችለውን ነገር ሁሉ የሚሰራው ትክክለኛ የስራ ድርሻው ባለቤት ስለሆነ ነው፡፡ 

እኛን የሚያስጨንቀን ነገር እርሱ ግን ስራው ነው፡፡ እኛን የሚያስጨንቀን እርሱ ያስበዋል ያቅዳል፡፡ 

ስለዚህ የማንጨነቅበትን ምክኒያት መፅሃፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል በግልፅ ይናገራል፡፡ እርሱ ስለናንተ ያስባልና፡፡ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡7
በዚህ ቀን የሚያስጨንቀንን በእርሱ ላይ ጥለን በልጅነታችንን እንደሰት፡፡ 

No comments:

Post a Comment