Popular Posts

Thursday, July 7, 2016

ቤተ እግዚአብሄር

በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እግዚአብሄር የሚኖርበት ነው ብለው የሚያስቡትን ቤት ዋጋው እጅግ ውድ በሆነ በወርቅና በከበረ ድንጋይ ያሳምሩታል ያስጌጡታል፡፡ እግዚአብሄርም ቤቱ ውስጥ መጥቶ እንዲኖር ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፡፡

እግዚአብሄር ግን እጅ በሰራው በማንኛውም ቤት ውስጥ አይኖርም፡፡ እግዚአብሄር የሚኖረው ራሱ በፈጠረው በሰው ልጅ ውስጥ ነው፡፡

ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ ሃዋሪያት 17፡24

እየሱስ ስለ ሃጢያቱ እንደ ሞተለትና ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳ ወደሚያምንና ወደሚመሰክር ሰው የእግዚአብሄር መንፈስ ይመጣል በእርሱም ውስጥ ማደር ይጀምራል፡፡

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን . . . የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16-17

ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡19-20

እኛን ክርስቲያኖች ከሌሎች ሰዎች የሚለየን እግዚአብሄር በውስጣችን መኖሩ ነው፡፡

እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ለሰዎች መልካም ያደርጋል፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ለሰዎች ፍቅሩን ይገልጣል፡፡ እግዚአብሄር በእኛ ውስጥ ሰዎችን ያስጠነቅቃል፡፡ እንዲሁም እግዚአብሄር ከክፉ ስራቸውም እንዲመለሱ ይገስፃል፡፡

እግዚአብሄር በአፋችን ተጠቅሞ ይናገራል፡፡ እግዚአብሄር በእግራችን ተጠቅሞ ይሄዳል ለሰዎች ይደርሳል፡፡ እግዚአብሄር በእጃችን ተጠቅሞ ለሰዎች መልካም ያደርጋል፡፡ እግዚአብሄር በልባችንና ተጠቅሞ ሰዎችን ይወዳል፡፡ በስሜታችን ተጠቅሞ እግዚአብሄር ለሰዎች ይራራል፡፡

እግዚአብሄርን ያየው አንድስ እንኳን የለም፡፡ እግዚአብሄርን የምናየው ውስጣቸው እግዚአብሄር በሚኖር የእግዚአብሄር ቤተመቅደስ በሆኑ ክርስቲያኖች ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሄር መኖሪያ ቤቱ ነን፡፡

ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 2ኛ ቆሮንቶስ 6፡16

ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

No comments:

Post a Comment