Popular Posts

Saturday, July 30, 2016

እንደ ንጽሕት ድንግል

በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3 
ሃሳብ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ሃሳብ ይነፃል ሃሳብ ይበላሻል፡፡ ሃሳብ ሲበላሽ ቅንነትና ንፅህና ይለወጣል፡፡ ቅን እና ንፁህ የነበረው ሰው ጠማማ እና የተጣመመ ሃሳብ ያለው ሰው ይሆናል፡፡
ሰው ሃሳቡ ሲበላሽና ቅንነቱ ሲለወጥ በእግዚአብሄር ማመኑን ያቆማል፡፡ ይህ በእግዚአብሄር ላይ ያለው እምነቱ መቀነሱ የሚታወቀው በአፉ ተናግሮት አይደለም፡፡ እግዚአብሄርን ማመን የከበደው ሰው በድርጊቱ ይታወቃል፡፡ 
ሰው ቅንነቱ ሲለወጥ ለመንፈሳዊ መሪዎች ያለው አክብሮት ይቀንሳል፡፡ ሰው ሃሳቡ ሲበላሽ ለቤተክርስቲያን ያለው መሰጠት ይቀንሳል፡፡ ለቤተክርስቲያን ገንዘቡን ሰጥቶ የማይጠግበው ሰው ቅንነቱ ሲበላሽ መጠራጠር ይጀምራል፡፡ ሰው ቅንነቱ ሲበላሽ የእግዚአብሄርን ህዝብ ማገልገል መፍራት ይጀምራል፡፡ የእግዚአብሄርን ህዝብ በትጋት በማገልገል የሚታወቀው ሰው ሃሳቡ ሲበላሽ ጊዜውንና ጉልበቱን መሰሰት ይጀምራል፡፡ ሰው ቅንነቱ ሲበላሽ ከእግዚአብሄር ህዝብ ጋር ህብረት ላለማድረግ ሰንካላ ምክኒያቶች ይበቁታል፡፡ ሰው ቅንነቱ ሲበላሽ ለሰዎች ስለጌታ ከሃጢያት አዳኝነት መናገር ይቀንሳል፡፡ ሰው ቅንነቱ ሲበላሽ ከፀሎት ይልቅ ሌሎች ነገሮች ያምሩታል፡፡ 
ጌታ እንዲነግዱና እንዲያተርፉ ንጉስ መክሊትን ስለሰጣቸው ምሳሌ ሲናገር አንድ መክሊት የተሰጠው ለንጉሱ ያለው ሃሳብ ስለተበላሸና ቅንነቱ ስለተለወጠ መክሊቱን ወስዶ ቀበረው፡፡ 
አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ማቴዎስ 25፡18, 24-25 
እንዲነግድ እንዲያተርፍና እንዲያድግ እንዲሾም የተሰጠውን መክሊት የቀበረው ምክኒያቱ የንጉሱን አላማ ስለተጠራጠረና ለንጉሱ ያለው ሃሳብ ሰለተበላሸ በዚያም ቅንነቱ ስለተለወጠ ነው፡፡
እግዚአብሄርን ማገልገል ታላቅ ጥቅም እና ታላቅ እድል ነው፡፡ ራሳችሁን ተመልከቱ ተመለሱም፡፡ ሃሳባችሁ እንዳይበላሽና ቅንነታችሁ እንዳይለወጥ ትጉ፡፡ ሃሳባችሁ እንዲለወጥ የሚመጣውን ማንኛውንም ሃሳብ አትቀበሉ፡፡ የእግዚአብሄርን ቃል ብቻ እመኑ፡፡ 
በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። 2ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-3 
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ 
#አተረፈ #ንፅህና #ቅንነት #ንጉስ #መክሊት #ኢየሱስ #ጌታ #መፅሃፍቅዱስ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ስብከት #እምነት

No comments:

Post a Comment