እየሱስን እንደ አዳኝና ጌታችን አድርገን በመቀበላችን ንጉሱ እግዚአብሄር ልጆቹ አድርጎናል፡፡ የነገስታት ቤተሰብ አባላት ነን፡፡ የንጉሱ ወንድና ሴት ልጆቹ ሆነናል እንደንጉስ በመመላለስ ሌሎች ምስክር መሆን እንችላለን፡፡
ግን ስንቶቻችን ነን እንደ ንጉስ ለቀቅ ያለና ሰፋ ያለ ኑሮ የምንኖረው?
እንደንጉስ ልጅ ማለቴ እንደ ምድራዊ ንጉስ በቤተመንግስት ውስጥ የሚኖር ማለት አይደለም፡፡ ንጉስ ማለት በ2017 ሞዴል ማርቼዲስ መኪና የሚሄድ ማለት አይደለም፡፡ ንጉስ ማለት በወርቅ የተሰራ የሚያብለጨልጭ ልብስ የሚለብስ ማለት አይደለም፡፡ ይህንማ ተራም ንጉስ ያደርገዋል፡፡
ምንም ሃብት ቢኖረው ተበድያለሁ አሳየዋለሁ የሚል ይቅር ለማለት የሚከብደው ሰው ንጉስ አይደለም፡፡ ንጉስ እቃዬን ወሰደብኝ ብሎ ለጥቂት ነገር የሚጣላ ቋጣሪ አይደለም፡፡ ንጉስ ካልነኩኝ አልነካም ከነኩኝ ግን እዘርራቸዋለሁ የሚል አይደለም፡፡
ይልቁንም ንጉስ ማለት ህይወቱ ለቀቅ ያለ ሰው ማለት ነው፡፡ ንጉስ ማለት ልብሱ ሳይሆን አእምሮው የበለፀገ ማለት ነው፡፡ ንጉስ ማለት ቤቱ ሳይሆን ልቡ የሰፋ ማለት ነው፡፡ ንጉስ ማለት በወርቅ ልብስ ሳይሆን በየዋህነት የጠሽቆጠቆጠ ልብ ያለው ማለት ነው፡፡ ንጉስ ምህረት የማያልቅበት ትግስቱ የበዛ ከእርሱ ለተለዩ ሰዎች ልቡ የሰፋ ለቀቅ ያለ ሰው ነው፡፡
እየሱስ ስለዚህ የህይወት ንግስና ሲናገር እንዲህ አለ፡፡
39 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ 40 እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ 41 ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። 42 ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። 43 ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። 44-45 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። 46 የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? 47 ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? 48 እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። ማቴዎስ 5፡39-48
የንግስናችን ብልጫ በህይወት ጥራት ነው፡፡ የንግስናችን ብልጫ በምህረት ብዛት ነው፡፡ የንግስናችን ብልጫ በይቅርታችን ብዛት ነው፡፡የንግስናችን ብልጫ ጠላቶቻችንን በመውደድ ነው፡፡ የንግስናችን ብልጫ ሌላውን በመሸከም ነው፡፡ የንግስናችን ብልጫ በልብ ስፋት ነው፡፡
የእኛ ባለጠግነት በእግዚአብሄር ስለሆነና የእኛን ንብረት ወስዶ ደሃ ሊያደርገን የሚችል ማንም ሰው እንደሌላ ተረድተን በብዙ በመተው የንግስናችንን ብዛት እናሳያለን፡፡ ንግስናችን ማንም ሊኖረው የሚችለው የቁሳቁስ ብልጫ ሳይሆን የህይወት ጥራት ነው፡፡ የንግስናችን ብልጫ የእግዚአብሄር ባህሪ ማንፀባረቃችን ነው፡፡ የንግስናችን ብልጫ የተቀበልነውን ታላቅ ፀጋ /የሚያስችል ሃይል/ ማሳየት ነው፡፡
የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ማቴዎስ 5፡46-47
በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። ሮሜ 5፡17
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ያድርጉ!
No comments:
Post a Comment