Popular Posts

Monday, July 25, 2016

ብፁሃን የዋሆች

የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ማቴዎስ 5፡5 
የዋህ በአማርኛ መዝገበ ቃላት " ገር ፣ ቅን ፣ መሠሪነት የክፋት ብልጠት የሌለው " በማለት ተተርጉሟል፡፡ 
የዋህ ማለት በሰው ላይ ክፉ ለማድረግና ለግሉ አላግባብ ለመጠቀም አቅሙና ችሎታው እያለው ሰውን ላለመጉዳት የሚጠነቀቅ ሃይሉን ለክፋት የማይጠቀምና ከክፋት የሚከለከል ሰው ማለት ነው፡፡
የዋህነት ደካማነት አይደለም፡፡ የዋህነት እንዲያውም ብርታት ነው ፡፡ ጀግና የሚባለው ራሱን የማይገዛ ሰው ሳይሆን ክፋት ለማድረግ ሲፈተን ራሱን የሚገዛ ለክፋት እጅ የማይሰጥ ብርቱ ሰው ነው፡፡ 
የዋህነት ሞኝነት አይደለም፡፡ እንዲያውም የዋህነት ሁኔታውን ጥበበኛው እግዚአብሄር እንዲይዘው ለጌታ የመተው ብልጠት ነው፡፡ የዋህነት ራስ የመበቀልን ፈተና በማለፍ ብድራቱን ለሚመልሰው ለእግዚአብሄር እድሉን መስጠት ነው፡፡ 
ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ሮሜ 12:19 
የዋህነት የሰው ቁጣ የእግዚአብሔርን ፅድቅን እንደማይሰራ በመረዳት ለእግዚአብሄር ገዢነት እውቅና መስጠት ነው፡፡ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና። ያዕቆብ 1፡20 
የዋህነት "ብትበደሉ አይሻልምን?" የሚለውን የእግዚአብሄርን ቃል አምኖ ሌላውን ከመበደል ይልቅ ራስ በመበደል ከእግዚአብሄር ሽልማት መቀበል ነው፡፡ እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡7
የዋህነት ለእግዚአብሄር አምላክነት እውቅና መስጠት ነው፡፡ የዋህነት እግዚአብሄርን ምንጭ ማድረግ ነው፡፡ የዋህነት አላግባብ ከሰው አለመጠበቅ ነው፡፡ የዋህነት የስኬት ቁልፍ ያለው በምድር እንዳይደለ ማወቅ ነው፡፡ የዋህነት በጥበብ በሃይል በባለጠግነት አለመመካት ነው፡፡ ይልቁንም የዋህነት ፅድቅና ፍርድን ምህረትን የሚያደርግ እግዚአብሄር መሆኑን በማወቅ መመካት ነው፡፡ 
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ ነገር ግን የሚመካው። ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር፦ ኤርምያስ 9፡23-24 
የዋህነት እግዚአብሄርን ያስደስተዋል፡፡ በየዋህነት እግዚአብሄርን ካስደሰትነው ምድርን እንወርሳለን፡፡ የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ማቴዎስ 5፡5 
ይህን ፅሁፍ ለሌሎች ሼር share ማድረግ ቢወዱ 
 

No comments:

Post a Comment