Popular Posts

Sunday, July 10, 2016

ኢየሱስን ተመልክተን

ሰዎች ሁል ጊዜ የተሳካለትንና ለስኬታቸው ምሳሌ የሚሆናቸውን ሞዴል ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ነው የተሳካላቸውን የፊልም ተዋናኞችና ታዋቂ ሰዎች ልብሳቸውንና የፀጉር ስታይላቸውን ሳይቀር የሚኮርጁትና እነርሱን ለመምሰል የሚሞክሩት፡፡

በክርስትናም እንዲሁ ሞዴል የሚሆኑ የክርስትና ህይወታቸውን ፍሬ እያየን የምንከተላቸው የቀደሙ ሰዎች ያስፈልጉናል፡፡

የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው።ዕብራውያን 13፡7

እንደ እየሱስ በክርስትናችን እንዲሳካልንና በነገር ሁሉ አሸንፈን እግዚአብሄርን ደስ ለማሰኘት የእየሱስን ህይወት መመልከት አለብን፡፡ እየሱስን በመምሰላቸው የምንመስላቸው ሰዎች ቢኖሩም ፍፁም ምሳሌያችን ግን እየሱስ ነው፡፡

እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2

ኢየሱስን የሚመስሉትንና እየሱስን የምንመለከተውና የምንመስለው

• ሩጫን በትግስት መሮጥ

ክርስትና እንደ መቶ ሜትር ሩጫ ውድድር አይደለም፡፡ ክርስትና እንደማራቶን ውድድር ነው፡፡ ክርስትና እንደ መቶ ሜትሩ የሩጫ ውድድር ጉልበት አለኝ ተብሎ የሚገሰገስበትና በሰከንዶች የሚጨረስ ሩጫ አይደለም፡፡ ማራቶን ጉልበት ቢኖረንም ጉልበታችን ለረጅም ጊዜ እንዲጠቅመን ሳንቸኩል ፡ ሳንሰለች ፡ በንቃት ፡ በድካም ሳናቋርጥ ፡ ለሰዓታት በትግስት የምንሮጠው ሩጫ ነው፡፡

• ነውርን መናቅ

ሌላው እየሱስን የምንመስለው በሰዎች ዘንድ ነውር የሚባለውንና ሰዎች የሚያንቋሽሹትን እንደ ሞኝነት የሚቆጥሩትን የእግዚአብሄርን ቃል በየዋህነትና በሞኝነት ተቀብሎ ማድረግ ነው፡፡ በሰው ዘንድ እንዳንናቅ እና እንዳንጠላ ፈርተን የማንታዘዘው የእግዚአበሄር ቃል የለም፡፡ ቃሉን እንጂ ነውርን አናከብርም፡፡ ነውረኛ እንዳንባል በመፍራት ቃሉን ከመታዘዘ ወደኋላ አንልም፡፡ በሚንቁና በሚያጥላሉ መካከል እየሱስ ጌታ እንደሆነ እንናገራለን እንመሰክራለን፡፡ በድፍረትም ቃሉን እንኖራለን፡፡ 
• የወደፊት ሽልማት ላይ እንጂ መከራው ላይ አለማተኮር

በፊታችን ስላለ ሽልማት በመከራ በመታገስ እርሱን ልንመስለው ይገባል፡፡ ምክኒያቱም ሁል ጊዜ "ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ" እንቆጥራለን፡፡ ሮሜ 8፡18

የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን "መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ" ተብለን ሽልማታችንን ከእግዚአብሄር ለመቀበል እንትጋ ፡፡ ማቴዎስ 25፡23

ይህን ኝሁፍ ለሌሎች ሼር ያድርጉ

No comments:

Post a Comment