Popular Posts

Saturday, December 30, 2017

ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም

የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም። መክብብ 1፡9
በምድር ላይ ቢሆንልኝ ብለን እጅግ ስንመኘው የነበረ ስናገኘው ለዚህ ነው እንደዚህ የሆንኩት ብለናል፡፡ በምድር ላይ እንደተራራ ገዝፎብን የነበረ ነገር ስንደርስበት ትንሽነቱ አስገርሞናል፡፡ በምድር ላይ ስንናፍቀው የነበረ ስናገኘው ሰልችቶናል፡፡ በምድር ላይ እንደ አድማስ ርቆብን የነበረ ነገር ስንቀርበው ምንም አዲስነት አላገኘንበትም፡፡ እደርስበት ይሆን ብለን እጅግ የፈለግነው ውይ ይሄ ነው እንዴ ብለናል፡፡
በምድር ላይ ብናገኘው ህይወታችን ይለወጣል ብለን አስበን የነበረው ነገር ህይወታችንንን ሊለውጥ ሳይችልና ሲቀር ቅር ሲያሰኘን ምስክር ሆነናል፡፡
በምድር ላይ ይህ ያላቸው ሰዎች የታደሉ ናቸው ብለን ያሰብናቸው ሰዎች ያገኙትን ስናገኝ ቀድሞ እንዳስብነው እንዳልታደሉ ደርሰንበታል፡፡ አሁንም ሰዎች እኛ ፈልገን ስናገኘው የተሰናከልንበትን ነገር እጅግ ሲፈልጉ ስናይ ይህ የተሳተ ግምታቸው ነግሩን ባገኙት ጊዜ ቅር እንደሚያሰኛቸው ስለምናውቅ እናዝናላቸዋለን፡፡
በምድር ላይ አንዲህ ብሆን እኮ ብለን የተመኘነውን ስንሆን ወዲያው ረስተነው አሁን ደግሞ ፍላጎታችን እጅግ የተለየ ሆኗል፡፡
ከሰማይት በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ አዲስ ነገር ያለ ከመሰለን ስላልደረስንበት ብቻ ነው፡፡ የደረሱበት ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ እንደተረዱት ስንደርስነበት ምንም አዲስ ነገር እንደሌለ ይገባናል፡፡ ውይ እነርሱን ባደረገኝ የምንላቸው ሰዎች ከዚህ መቼ በወጣሁ ብለው ሲመኙ ደርሰናል፡፡
ብቻኛው አዲሱ ነገር የእግዚአብሄርን ስራ በምድር ላይ ሰርቶ እግዚአብሄርን በህይወታችንና በአገልግሎታችን ማክበር ነው፡፡
እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤ ዮሃንስ 17፡4
ብቸኛው አዲሱ ነገር ሰውን መውደድ ፣ ሰውን ማገልገል ፣ ሰውን መጥቀምና ሰውን ማንሳት ነው፡፡
በምድር ላይ አዲሱ ነገር በዘላለማዊ እይታ የምድር ህይወትን እንደ እንግድነት መኖር ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ነገር በምድር ላይ እንደ እግዚአብሄር መልክተኛ ፈቃዱን ፈፅሞ ማለፍ ብቻ ነው፡፡ በምድር ላይ አዲሱ ነገር በሰማይ መዝገብን መሰብሰብ ነው፡፡
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ ማቴዎስ 6፡19-20
በምድር አዲሱ ነገር በዘላለማዊ ሽልማትን እንደሚቀበል ራስን መግዛት ነው፡፡ በምድር አዲሱ ነገር በምድር ገንዘብ የዘላለም ወዳጆችን ማፍራት ነው፡፡
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9
ብቸኛው አዲስ ነገር በምድር ለሚቀር ዘላለማዊ ላልሆነ ለጊዜያዊ መብል አለመስራትና ዘላለማዊ ለሆነ ለማይጠፋ መብል መስራት ነው፡፡
ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና። ዮሃንስ 6፡27
ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል። 1ኛ ዮሃንስ 2፡17
አዲሱ ነገር ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ከጌታ ጋር መኖር ነው፡፡ አዲሱ ነገር ጌታን መውደድ ነው፡፡ አዲሱ ነገር ጌታን ኢየሱስን መከተል ብቻ ነው፡፡ ዘመን የማይሽረው አዲሱ ነገር ጌታን መውደድ ጌታን መከተል ጌታን ማገልገል ብቻ ነው፡፡ 
ከላይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው፤ ከምድር የሚሆነው የምድር ነው የምድሩንም ይናገራል። ከሰማይ የሚመጣው ከሁሉ በላይ ነው። ዮሃንስ 331
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes

#ኢየሱስ #ጌታ #ዘላለማዊ #አዲስ #ልብ #ሰማይ #ዘላለም #ጌታ #ከፀሐይበታች #ያልፋሉ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #ወንጌል #መናገር #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment