Popular Posts

Friday, December 15, 2017

ኢየሱስ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ እንዳለ እኛም የእርሱን ፈቃዱን ልናደርግ ተወልደናል

ሰው በድንገት ወደ ምድር አልመጣም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ለክብሩ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው አቅዶና አልሞ በአላማ ነው፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ሰው ሲፈጠር እንዴት እንደሚኖር ፣ ምን እንደሚያደርግና እንዴት እንደሚሆን ሁሉ ታቅዶ ነው፡፡
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ዘፍጥረት 1፡26
ኢየሱስ አንዲሁ በድንገት ወደ ምድር አልመጣም፡፡ የሃጢያቱን እዳ በመክፈል በሃጢያት የወደቀውን ሰው ለማዳን ኢየሱስ ወደምድር መጣ፡፡ ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት እንዴት እንደሚመጣ ፣ ለምን እንደሚመጣ ፣ ምን እንደሚያደርግና ምን እንደሚሆን ሁሉ በመፅሃፍት ተፅፎ ነበር፡፡
ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ፦. . . ። በዚያን ጊዜ፦ እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ይላል። ዕብራውያን 10፡5-7
ኢየሱስ ወደምድር ሲመጣ የመጣበትንና ያልመጣነበትን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡
ጲላጦስም፦ እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው። ዮሃንስ 18፡37
ኢየሱስ አለምን አሸንፎ የሄደው ወደምድር የመጣነበትን አላማ ጠንቅቆ ስለሚያውቅና ያልተጠራበትን አላማ ላለማድረግ እጅግ ስለሚጠነቀቅ ነበር፡፡
ከሕዝቡም አንድ ሰው፦ መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው። እርሱም፦ አንተ ሰው፥ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ አንድሆን ማን ሾመኝ? አለው። ሉቃስ 12፡13-14
ታእምር በማድረግ ኢየሱስ ሲያስደስታቸው ህዝቡ ንጉስ ሊያደርጉት ሊሾሙት ሲሞክሩ አምልጧል፡፡ ንጉስ መሆን ጥሩ ነገር ቢሆንም ነገር ግን የተጠራበት አላማ አልነበረም፡፡
በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ። ዮሃንስ 6፡15
ኢየሱስ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች ባለ ጊዜ እንኳን ያንተ ፈቃድ ይሁን የእኔ ፈቃድ አይሁን በማለት ወደምድር ለመጣበት አላማ ራሱን ሙሉ ለሙሉ እንደሰጠ አሳይቷል፡፡
ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ሉቃስ 22፡42
ኢየሱስ በሚያልፍበት ነገር እየፀለየና ራሱን ለእግዚአብሄር አይሰጠ ፈቃዱን እያስገዛ ያለፈ የነበረው እንደተፃፈለት ይሄድ ስለነበረ ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሄርን በታዘዘ መጠን ከተፃፈው ውጭ እንደማይደርስበት መተማመኑ ስለነበረው ነው፡፡
የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ማቴዎስ 26:24
አሁንም እኛ በምድር የተወለድነው የምንፈልገውን ነገር አድርገን ለማለፍ ሳይሆን የእግዚአብሄርን አላማ ለመፈፀም ነው፡፡ ወደ ምድር ከመምጣታችን በፊት ብሎም ወደ እግዚአብሄር መንግስት ከመግባታችን በፊት በእግዚአብሄር መንግስት ውስጥ የምንሰራው ነገር ነበር፡፡ በስማችን የተዘጋጀ መልካም ስለነበረ ነው ወደፍቅሩ ልጅ መንግስት የፈለስነው፡፡
እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን። ኤፌሶን 2፡10
ስኬት የእግዚአብሄርን አላማ መፈፀም ነው፡፡ በምድር ላይ ስኬታማ ለመሆን እግዚአብሄር ያዘጋጀልንን አላማ ፈልገን ማግኘት ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሄር በምድር ላይ የፈጠረንን አግኝተን ከፀናንበት በሚገባ የተኖረ ህይወት ይኖረናል፡፡ የተወለድንበት አላማ ላይ ሳናተኩር የፈለግነውን ነገር አድርገን ካለፍን ህይወታችን ይባክናል፡፡
. . . የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡1-2
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#የእግዚአብሄርምክር #የእግዚአብሔርፈቃድ #እግዚአብሔር #እንደተፃፈ #እምነት #የሰውአሳብ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment