Popular Posts

Monday, December 18, 2017

በበረት የተወለደው ኢየሱስ በልባችን ካልተወለደ አይጠቅመንም

እግዚአብሄር ሰውን ሁሉ ፈጥሮታል፡፡ ሰው ሁሉ በሃጢያት ወድቋል፡፡ ሁሉም ሰው የእግዚአብሄር ፍጥረት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ግን የእግዚአብሄር ልጅ አይደለም፡፡ ወይም ኢየሱስ ስለሰዎች ሁሉ በመስቀል ላይ ሊሞት በምድር ላይ ስለተወለደ ብቻ ሰው ሁሉ ከመቀፅበት የእግዚአብሄር ልጅ አይሆንም፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ ለመሆን መመዘኛ አለው፡፡ ለእግዚአብሄር ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሄር ልጅ ለመሆን ብቸኛው መመዘኛ ኢየሱስን መቀበል ነው፡፡
ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሃንስ 1፡12
በበረት የተወለደው ኢየሱስ በልባችን ካልተወለደ አይጠቅመንም፡፡ ሃይማኖተኛ ልንሆን እንችላለን፡፡ ብዙ ነገሮችን ለእግዚአብሄር ብለን ልናደርግ እንችላለን፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሰራልንን ለእኔ ነው ብለን ኢየሱስን በመቀበል ዳግመኛ ካልተወለድን ግን የኢየሱስ በምድር ላይ መወለድ አይጠቅመንም፡፡ ኢየሱስን ያደንቀው ለነበረ ኒቆዲሞስ ለተባለ የህግ መምህር ኢየሱስ ያለው ይህንን ነው፡፡
ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ዮሃንስ 3፡3፣5
በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርአቶች ገናን በፍቅር ልናከብረው እንችላለን፡፡ ኢየሱስን ከልባችን ልናደንቀው እንችላለን፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ በልባችን ካልኖረ ወደ ምድር የመጣበትንና ከድንግል ማርያም የተወለደበትን አላማ ስተነዋል፡፡
ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ዮሃንስ 1፡21
ኢየሱስ በምድር ላይ ስለተወለደ ብቻ ከመቀፅበት አንድንም፡፡ ኢየሱስ ስለተወለደ ብቻ ሰዎች ከመቀፅበት የሚድኑ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ስበኩ ብሎ ባላዘዘን ነበር፡፡ የምስራቹን ቃል ሰምተው የሚያምኑ ብቻ ናቸው የሚድኑት፡፡
እንዲህም አላቸው፦ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። ማርቆስ 16፡15-16
የሚድኑት ኢየሱስን እንደ አዳኝ የተቀበሉ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ የምንም ሃይማኖት ተከታዮች ስለሆንን ብቻ አንድንም፡፡ ከሃጢያት የሚያድነን ኢየሱስን እንደ አዳኝና ጌታ አድርገን መቀበላችን ብቻ ነው፡፡
በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዮሃንስ 3፡16
ሰዎች በየእለቱና በየደቂቃው ኢየሱስን እየተቀበሉና እየዳኑ ነው፡፡ እኛ ግን ኢየሱስን ወደ ልባችን ሳናስባውና በልባችን ሳይወለድ ኢየሱስ በምድር ላይ ስለተወለደ ብቻ ድነናል ብለን ካሰብን ተታለናል፡፡ የኢየሱስ መወለድ እንዲጠቅመን ወንጌልን ማመን ይጠበቅብናል፡፡ የሚያድነን የእግዚአብሄር ሃይል የኢየሱስ ስለሃጢያታችን መሞቱን የምስራች ማመን ነው፡፡
በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ሮሜ 1፡16
 ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#እምነት #ወንጌል #ስብከት #ቃል #ገና #ልብ #ዳግመኛመወለድ #የማዳንሃይል #የእግዚአብሄርሃይል #መንፈስቅዱስ #ቃሉንመስማት #እወጃ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment