Popular Posts

Follow by Email

Saturday, December 2, 2017

በቃሉ መኖር

በፍሬያማነት ለመኖር በኢየሱስ መኖር ወሳኝ ነው፡፡ በኢየሱስ መኖር የተፈጠሩበትን አላማ መፈፀም ነው፡፡ በኢየሱስ መኖር ፍሬያማነት ነው፡፡
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። ዮሐንስ 154
በኢየሱስ መኖር ደግሞ በአጭሩ በቃሉ መኖር ነው፡፡ በቃሉ ከኖርን በኢየሱስ ኖረናል፡፡ በቃሉ ካልኖርን በኢየሱስ አልኖርንም፡፡
በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ዮሐንስ 15፡7
በቃሉ መኖር ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት
በቃሉ መኖር ማለት ቃሉን ምንጭ ማድረግ ማለት ነው፡፡
በህይወታችን ለሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ቃሉን ምንጭ ካደረግነው በቃሉ እየኖርን ነው፡፡ ቃሉን ለምሪታችን ምንጭ ፣ ቃሉን ለሃይላችን ምንጭ ፣ ቃሉን ለመፅናናታችን ምንጭ ፣ ቃሉን የደስታችን ምንጭ ካደረግነው በቃሉ እየኖርን ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህን በህይወት አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ከቃሉ ውጭ የምንፈልግ ከሆነ በቃሉ እየኖርን አይደለንም፡፡ በቃሉ መኖር ማለት ቃሉ የማይሰጠኝ ነገር የእኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ በቃሉ መኖር ማለት ቃሉ የሚሰጠኝ ነገር ብቻ ነው የእኔ እውነተኛ ሃብት ማለት ነው፡፡  
ለእግዚአብሔርም ክብር እየሰጠ፥ የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፥ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም። ሮሜ 4፡20-21
በቃሉ መኖር ማለት ቃሉን መልስ ማድረግ ማለት ነው፡፡
ሰው በህይወቱ ለሚነሳው ጥያቄ የእግዚአብሄር ቃል ምን ይላል የሚል ከሆነና ቃሉን የሚያጣቅስ ከሆነ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው በህይወቱ ለሚገጥመው ተግዳሮት ወደቃሉ የሚሮጥ ከሆነ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው በህይወቱ ለሚገጥመው ማንኛውም ጥያቄ ቃሉን እንደ መልስ ካየውና ካረፈ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ለህይወቱ ጥያቄ የቃሉ መልስ የእኔ መልስ ነው ብሎ ከተቀበለ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡
የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና። ዕብራውያን 12፡2
በቃሉ መኖር ማለት በቃሉ መደገፍ ማለት ነው
በቃሉ መኖር ማለት ቃሉን ማመን በቃሉ መገደፍ ማለት ነው፡፡ በቃሉ መኖር ማለት በቃሉ መተማመን ማለት ነው፡፡ በቃ መኖር ማለት ቃሉ አይጥልም ብሎ ህይወትን በቃሉ ላይ መጣል ማለት ነው፡፡ በቃሉ መኖር ማለት ወደፊትን በቃሉ ላይ መተው ማለት ነው፡፡ በቃሉ መኖር ማለት ቃሉን ታዝዤ ቃሉ ያደረገኝን መሆን እፈልጋለሁ ማለት ነው፡፡ በቃሉ መኖር ማለት ቃሉ የሚያደርገንን መሆንን እንደክብር መቁጠር ነው፡፡  
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ማቴዎስ 16፡25
በቃሉ መኖር ማለት ቃሉን ብቻ የደህንነት ምንጭ ማድረግ ማለት ነው፡፡
ሰው የህይወት ደህንነቱን ከቃሉ ውጭ  ከፈለገ በቃሉ እየኖረ አይደለም፡፡ ሰው ደህንነት የሚሰማው ቃሉን ሲያደርግ ከሆነ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ በተቃራኒው ቃሉን ሳይታዘዝ ደህንነት ካልተሰማው በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው ቃሉን የደህንነቱ ምንጭ ካደረገ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው ቃሉን አስተማማኝ ጥላ ካደረገው በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው ግን ለህይወቱ የደህንነት ስሜት የሚሰጠው እንደ አለም ሃብት ሲያከማችና ዝና ሲኖረው ከሆነ በቃሉ እየኖረ አይደለም፡፡  
የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና። ሉቃስ 19፡48
በቃሉ መኖር ማለት በእግዚአብሄር ቃል መመካት ማለት ነው
ሰው የሚያስደስተውና የሚያኮራው የእግዚአብሄር ቃል ከሆነ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው ግን የሚያስመካው ከቃሉ ውጭ የሆኑ ነገሮች ከሆኑ ሊመስለው ይችላል እንጂ በቃሉ እየኖረ አይደለም፡፡ ሰውን ከምንም በላይ የሚያስደስተው ቃሉ ከሆነ በቃሉ እየኖረ ነው
ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ። መዝሙር 119፡162
በቃሉ መኖር ማለት የእግዚአብሄርን ቃል ማክበር ማለት ነው፡፡
ሰው ከምንም ነገር በላይ የእግዚአብሄርን ቃል ካከበረ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡ ሰው ግን ለእግዚአብሄር ቃል ግድ ከሌለው በቃሉ እየኖረ አይደለም፡፡ ሰው ከእግዚአብሄር ቃል በላይ የሚፈራው ነገር ካለ በቃሉ እየኖረ አይደለም፡፡
እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። ኢሳይያስ 66፡2
ቃሉን ለማድረግ ምንም ነገር ለማጣት የተዘጋጀ ሰው በቃሉ እየኖረ ነው፡፡
ቃሉን ለማድረግ ምቹ ጊዜ እስኪያገኝ እየጠበቀና እያመቻመቸ ያለ ሰው ቃሉን እየጠበቀ አይደለም፡፡ ቃሉን ግን በሚመችም በማይመች ሁኔታ ውስጥ የሚያደርገው ከሆነ በቃሉ እየኖረ ነው፡፡  
ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።2 ጢሞቴዎስ 4
ቃሉ እንደሚሰራ እንደህያው ካየው በቃሉ እየኖረ ነው፡፡
ቃሉ እንደሚሰራ እንደሚለውጥ ካየ በቃ እየኖረ ነው፡፡ ቃሉ ግን እንደማይሰራ እንደማይለወጥ እንደአንድ ባዶ ሃይማኖታዊ ትእዛዝ ካየው በቃሉ እየኖረ እንዳይደለ በቂ ምልክት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ ዕብራዊያን 4፡12
በእኔ ኑሩ፤ እኔም በእናንተ፤ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ከአልኖረ ብቻውን ሊያፈራ እንደማይችል እናንተም እንዲሁ በእኔ ካልኖራችሁ ፍሬ ማፍራት አትችሉም። በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል። ዮሐንስ 15፡4፣7
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ሬያማነት #ፍሬ #ማፍራት #ስኬት #በእኔኑሩ #ቃል #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #መመዘኛ #መስፈርት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment