Popular Posts

Follow by Email

Saturday, December 23, 2017

አንድም አሳብ ይሁንላችሁ

በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ፊልጵስዩስ 2:1-2
እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡1-3
የእግዚአብሄር መንግስት ስራ ሁሉም ያለውን ፀጋ የሚያዋጣበት የህብረት ስራ እንጂ የአንድ ሰው ስራ አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ስራ የህብረት ስራ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መንግስት መፍትሄ ሁሉ በአንድ ሰው ውስጥ ብቻ አልተቀመጠም፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት ብዙ ብልቶች እንዳሉት አካል ይመሰላል፡፡  
አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 12፡12
በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። ሮሜ 12፡4-5
የእግዚአብሄር ስራ የህብረት ስራ በመሆኑ አንድነት ወሳኝ ነው፡፡ በሰዎች መካከል አንድነት ከፈረሰ ህብረት ይፈርሳል፡፡ አንድነት ከፈረሰ መንግስት አይቆምም፡፡
እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? ማቴዎስ 12፡26
በመፅሃፍ ቅዱስ አንድነት እንዲኖረን አንድነታችንን ተግተን እንድንጠብቅ አበክሮ የሚያስጠነቅቀን ለዚህ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር የሚሆንበትን ምክኒያት ከመግለፅ ይልቅ አንድ ነገር የማይሆንበትን ምክኒያት መግለፅ ይቀላል፡፡ አንድነት አሁንም አንድነት የሚጠበቅበትን ሁኔታ ከማስረዳት ይልቅ አንድነት የማይጠበቅበትን ሁኔታ ማስረዳት ስለ አንድነት ያለንን መረዳት ይጨምራል፡፡
አንድነት የማይጠበቅበትን ምክኒያትና አንድነትን መጠበቅ የማይፈልጉ አምስት አይነት ሰዎችን እንመልከት፡፡
1.      ሰዎች ከጋራ አጀንዳ ይልቅ የራሳችው የግል አጀንዳ ሲኖራቸው አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡
ሰዎች ህብረትን የሚፈልጉት የእግዚአብሄርን መንግስት ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሆን ህብረትን አይፈልጉም፡፡
ሰው የእግዚአብሄርን ፈቃድ ሳይሆን ምኞቱን ከተከተለ አንድነትን ሳይሆን መለየትን ይፈልጋል፡፡  
መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል። ምሳሌ 18፡1
2.     ሰዎች ጨካኞችና የማይራሩ ሲሆኑ አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡
ሰዎች ለእግዚአብሄር መንግስት ስምረት ግድ ሳይኖራቸው ሲቀር ለአንድነት ግድ አይኖራቸውም፡፡ ሰዎች ከእግዚአብሄር ምነገሰት ሸክም ይልቅ የሚያከብሩት ሌላ አለማ ካላቸው ለአንድነት ዋጋ ለመክፈል ዝቅ ማት ያቅታቸዋል፡፡ አንድነት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አንድነት እኛን የማይመስሉንን ሰዎች መቀበል ይጠይቃል፡፡ አንድነት የተለያየን ሰዎች ለአንድ አላማ መቀራረብን ይጠይቃል፡፡ ለመንግስቱ እውነተኛ ሸክም ያለው ሰው ለአንድነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ይከፍላል፡፡ ለመንግስቱ ሸክም ያለው ሰው ከእርሱ ስሜት ይልቅ የአንድነት የጋራ ጥቅም ይበልጥበታል፡፡
እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት። ቆላስይስ 3፡13-14
3.     ሰዎች ሰነፍና ሀሞተ ቢስ ሲሆኑ አንድነትን መጠበቅ አይፈልጉም፡፡
አንድነትን መጠበቅ ለሰነፍ ሰው አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ ትጋት ይጠይቃል፡፡ አንድነትን መጠበቅ መነጋገር መወያየት በቀጣይነት በትጋት ችግሮችን መፍታት ይጠይቃል፡፡ አንድነትነ መጠበቅ የደካማ ሰዎች አይደለም፡፡ አንድነትም መጠበቅ የፈሪዎች አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ የደካ ሰዎች አይደለም፡፡ አንድነትን መጠበቅ የእምነት ሰዎች ነው፡፡ አንድነትን መጠበቅ የልበ ሰፊ ሰዎች ነው፡፡  አንድነትን መጠበበቅ የደፋር ሰዎች ነው፡፡
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። ኤፌሶን 4፡3

ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። ኤፌሶን 4፡12-13
4.     ትእቢተኛና ትምክተኛ ሰዎች አንድነትን መጠበቅ አይችሉም፡፡
ሰዎች ከሌላው እበልጣለሁ ሲሉና ሁሉንም የሚያውቁ ሲመስላቸው አንድነትን መጠበቅ ያቅታቸዋል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን አዋርደው ወደ አንድነት ሃሳብ ከመምጣት ይልቅ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይሁን ካሉ አንድነት ሊጠበቅ ይችልም፡፡ ሰዎች ለመሸነፍ ሲፈቅዱ አንድነት ይመጣል፡፡ ሰዎች የእኔ ሃሳብም ባይሆን የሚበልጠው ይሁን ካሉ አንድነት ይመጣል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሁሌ የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክለ ካሉ ከማንም ጋር መስማማትና መስራት ያቅታቸዋል፡፡
በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡8
እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ሮሜ 12፡16
5.     ሰዎች ስስታም ሲሆኑ አንድነትን አይፈልጉም፡፡  
ሰዎች ስስታም ሲሆኑ ህይወታቸውን ለሌላ ሰው ለማካፈል ሲሰስቱ አንድነትን ይቃወማሉ፡፡ በማካፈልና በመስጠት ብቻ ላይ ነው አንድነት የሚመሰረተው፡፡ ሰዎች ግን መስጠት ሲሰስቱ ለማካፈል ፈቃደኛ ሳይሆኑና መቀበል ብቻ እንደሚገባቸው ሲያስቡ አንድነት አይታሰብም፡፡
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡10
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment