ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር
ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4
ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን ይኸውም
ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤ ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት
መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
የውጭ ውበት መልካም ነው ዋጋም አለው፡፡ ነገር
ግን ከውጭው ውበት ጋር ሲነፃፀር የውስጡ ውበት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡
ከውስጡ ውበት አንፃር የውጭው ውበት ብዙ ዋጋ
አያስከፍልም፡፡ ከውስጡ ውበት አንፃር የውጭው ውበት ባነሰ ጊዜና ጥረት ይገኛል፡፡
የውጪው ውበት ለሰው የእግዚአብሄር ስጦታ ሲሆን
ማንም ሊመካበት የማይችል ውበት ነው፡፡ የውስጡ ውበት ግን የሰው ለእግዚአብሄር ስጦታና ሰውን የሚያስመሰግነው ውበት ነው፡፡ የውጭው
ውበት ራስን በማስለመድ የሚመጣ መልካም ባህሪ ነው፡፡
እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ
- 1ኛ ጢሞቲዮስ 4፡7
የውጭው ውበት አንዴ ተሰርተነው የምናስደንቅበት
ሲሆን የውስጡ ውበት ግን የህይወትን ዘመን ሁሉ ትጋትን የሚጠይቅ ዘለቄታዊ ውበት ነው፡፡
ውበት ሐሰት ነው፥ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች። ምሳሌ 31፡30
የውጭው ውበት እግዚአብሄርን አያስደንቀውም የውስጡ
ውበት ግን እግዚአብሄር ከሰው የሚፈልገው ስለሆነ እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘዋል፡፡ የውጭው ውበት እንደ ዛፍ ቅጠል ሲሆን የውስጡ
ፍሬ ግን እንደ ዛፍ ፍሬ ነው፡፡
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው። ገላትያ 5፡22
የውስጡ ውበት የሚለካው ተለዋዋጭ በሆነው በገፅታ
ሳይሆን በባህሪ ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በቅላት ሳይሆን በአመለካከት ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በርዝመት ሳይሆን በትግስት
ነው፡፡ የውስጡ ውበት የሚለካው በቅጥነት ሳይሆን በትህትና ነው፡፡
የውስጥ ውበት የሚለካባቸውን እግዚአብሄር ከእያንዳንዳችን
የሚፈልጋቸውን ሁለት ወሳኝ ባህሪያትን እንመልከት፡-
የዋህነት
የዋህነት ማለት ክፉን በክፉ ለመመለስ ሙሉ ሃይል
ይዞ ነገር ግን ሃይልን ለክፋት ላለመጠቀም መወሰንና ራስን ማግዛት ነው፡፡
የዋህ ማለት ሞኝ ማለት ሳይሆን ክፋትን በክፋት
ላለመመለስ ራሱን የሚገዛ ቁጥብ ሰው ማለት ነው፡፡ የዋህ ማለት ሃይል እንዳለው እያወቀ ሃይሉን ለክፋት ሳይሆን ለመልካምነት ብቻ
ለመጠቀም የወሰነ ራሱን የሚገዛ ማለት ነው፡፡
የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ማቴዎስ 5፡5
ዝግተኛነት
ዝግተኛ ማለት እግዚአብሄርን የማይቅድም ፣ እግዚአብሄርን
የሚያስቀድም ፣ እግዚአብሄርን የሚከተል ፣ የእግዚአብሄርን እርምጃ የሚታገስና በእግዚአብሄር የሚመራ ሰው ማለት ነው፡፡ ዝግተኛ
ወይም ጭምት ማለት በራሱ አነሳሽነት ድርሻዬ ነው ብሎ የፈለገውን የማይወስድ እግዚአብሄር ድርሻውን እስኪያሳየው የሚጠብቅ እግዚአብሄር
ካላሳየው በራሱ ማስተዋል የማይደገፍ በራሱ የማይመራ ማለት ነው፡፡
በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ ምሳሌ 3፡5
ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር
ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡3-4
ለተጨማሪ ፅሁፎች
https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
#ኢየሱስ #ጌታ #ባህሪ
#ፍቅር #ልብ
#የዋህ #ዝግተኛ #የመንፈስፍሬ #ውበት #የልብሰው #ቤተክርስትያን
#አማርኛ #ስብከት
#መዳን #መፅሃፍቅዱስ
#ሰላም #አቢይ
#አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ
#ወንጌል #መናገር
#ፅናት #ትግስት
#መሪ
No comments:
Post a Comment