Popular Posts

Follow by Email

Tuesday, December 19, 2017

የዓመቱ ስኬት በታማኝነት ሲለካ

እግዚአብሄር ስራውን ሰርቶ ይመዝነዋል፡፡ እግዚአብሄር ምድርን ሲፈጥር ስራውን ፣ ያደረገውንና የፈጠረውን ያይና መልካም ነው ይል ነበር፡፡  
እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን። ዘፍጥረት 1፡31
እግዚአብሄር ስራውን ይመዝናል፡፡
አትታበዩ፥ በኩራትም አትናገሩ፤ እግዚአብሔር አዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ሥራውን የሚመዝን ነውና፥ ከአፋችሁ የኵራት ነገር አይውጣ። 1ኛ ሳሙኤል 2፡3
ስራን ስለመመዘን እግዚአብሄር ታላቁ ምሳሌያችን ነው፡፡ የእኛም ህይወትና አካሄድ በየጊዜው መመዘን አለበት፡፡ እግዚአብሄር ጊዜን በቀን ፣ በሳምንት ፣ በወርና በአመት ሲከፋፍለው ቆም ብለን ራሳችንን እንድናይ እያመቻቸልን ነው፡፡ እግዚአብሄር ቀንና ለሊትን የለየው ሰው በምሽት ዝግ እንዲልና የእግዚአብሄርን ስራ ዞር ብሎ እንዲያስብ ነው፡፡
ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። ኢዮብ 37፡7
የማይመዘን ህይወት ትክክል መሆኑ ስለማይታወቅ ለወደፊት ድፍረትን አይሰጥም፡፡ የማይመዘን ህይወት ስህተት መሆኑም ስለማይታወቅ በጊዜ ለመመለስ አይጠቅምም፡፡ የማይመዘን ህይወት ከንቱ ህይወት ነው፡፡  
ህይወታቸነ መመዘን እንዳለበት ከተረዳን በአመቱ ውስጥ በህይወታችን ስኬታማ መሆናችንን የምናውቅው እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው፡፡ ለመሆኑ ስኬታማነት ሊመዘን ይችላል? ስኬታማነት ከተመዘነስ የስኬታማነት መመዘኛው ምንድነው? ስኬታማ መሆናችንን በምን እናውቃለን? የሚለውን ጥያቄ በትክክል መመለስ ስኬታማ ስንሆን እንድናውቅ ስኬታማ ካልሆንን በጊዜ መንገዳችንን ቀይረን ለወደፊት ለስኬታማነት እንድንዘጋጅ ይረዳናል፡፡
በአለም ብዙና የተለያዩ የስኬታማነት መመዘኛ ነጥቦች አሉ፡፡ የአለምን የስኬታማነት መመዘኛ ከተከተልን እንስታለን፡፡ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው አንድ የስኬተማነት መለኪያ ብቻ ነው፡፡ ይህ የስኬታማነት መለኪያ ሰው በምንም ሁኔታ ውስጥ ይሁን ፣ ምንም ደረጃ ይኑረው ፣ ምንም ያግኝ አያግኝ ካለአድሎ ስኬቱን በትክክል ሊለካው ይችላል፡፡
ይህ የስኬታማነት ብቸኛ መለኪያ ታማኝነት ነው፡፡
የሰው ሰኬት ባለው ሃብት መጠን አይለካም ሃብቱን ለምን ምክኒያት እንዳዋለው ታማኝነቱ እንጂ፡፡
በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፥ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው። እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡17-19
አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው። ማርቆስ 12፡44
የሰው ስኬታማነት ባለው ተሰሚነት መጠን አይለካም ተሰሚነቱን ለምን እንደተጠቀመበት በታማኝነቱን እንጂ፡፡ የሰው ስኬት በዝናው አይለካም ዝናውን በታማኝነት ለእግዚአብሄር መንግስት ጥቅም ማዋሉ እንጂ፡፡ ሰው ዝናውም ለራሱ የግል ጥቅም በማዋሉ እግዚአብሄር ዝናውን አይሸልምም፡፡
በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ 1 ጴጥሮስ 5፡2
ሰው ስኬቱ ባለው ጥበብ አይለካም በጥበቡ ለሰዎች ጥቅም ወይም ለራሱ የግል ጥቅም ወይስ ለሰዎች ውድቀት በመስራቱ እንጂ፡፡
እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። 1 ቆሮንቶስ 2፡4-5
የሰው ስኬት የሚለካው በታማኝነት መመዘኛ ብቻ ነው ፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው በአደራ ለተሰጠው ነገር ታማኝ መሆኑን አይቶ ስኬታማ መሆኑንና አለመሆኑን ሊያውቅ ይችላል፡፡
መክሊት ስለጠተሰጣቸው ሰዎች መፅሃፍ ቅዱስ ሲናገር አንዱንም ስለተሰጠው መክሊት ብዛትና ማነስ አልተናገረውም እንዲሁም አንዳቸውም በመክሊታቸው ብዛትም አልተለኩም፡፡ እንዲያውም የተለኩት በጥቂቱ ነው፡፡
ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ማቴዎስ 25፡23
በህይወታችን የተሰጠን መክሊት ምንም ትንሽ ቢሆንም ታማኝነታችን ሊያመለክት ግን በቂ ነው፡፡
በዚህ አመት የህይወታችንንና የአገልግሎታችንን ስኬት የምንመዝነው እግዚአብሄር ለሰጠኝ ነገር ታማኝ ነበርኩ ወይ? የሚለውን ጥያቄ በታማኝነት በመመለስ ብቻ ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ታማኝነት #መክሊት #ጊዜ #ጉልበት #እውቀት #ኢየሱስ #ክርስቶስ #ጌታ #ጊዜ #ዘመን #አመት #ቀን #አዲስአመት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #እምነት #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ምህረት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment