Popular Posts

Follow by Email

Thursday, December 14, 2017

አዲሱ አመት በእውነት አዲስ የሚሆንበት ሶስቱ መንገዶች

አመት ሲለወጥ ሁልጊዜ ተስፋችን ይታደሳል አዲስን ነገር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ከተረዳነው የአመቱ ወሮችና ቀኖች በራሳቸው አዲስ አይደሉም ካለእኛም በራሳቸው አዲስን ነገር ሊያደርጉልን አይችሉም፡፡ ያው እሁድ ሰኞ ማክሰኞ ሮብ ሃሙስ አርብ ቅዳሜ ናቸው የአመቱም ወሮች ያው መስከረም ጥቅምት ህዳር ታህሳሰ ወዘተ ናቸው፡፡
አዲስን አመት አዲስ የሚያደርገው አዲሱን አመት የሚኖርበት ሰው አዲስ መሆኑና መታደሱ ነው፡፡ ምክኒያቱም አሮጌን ነገር በአዲስ ነገር ውስጥ ብንጨምር አይሰራም፡፡ አሮጌ ሰው በአዲስ አመት ውስጥ መኖሩ አመቱን በፍፁም አዲስ አያደርገውም፡፡ አሮጌ ሰው ከአዲስ አመት አዲስን ነገር መጠበቅ ነፋስን እንደመጨበጥ ከንቱ ድካም ነው፡፡  
በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ማቴዎስ 9፡17
ሰውን የሚለውጠው አመት አይደለም፡፡ ሰውን የሚለውጠው እና አዲስና በቀጣይነት የታደሰ የሚያደርገው የእግዚአብሄር ቃል ነው፡፡
የአዲስን አመት ጥቅም ለመጠቀም አዲስን ነገር በአዲስ ነገር ውስጥ መጨመር ግዴታ ነው፡፡ አዲሱን አመት በአዲስነት የምንቀበልበትና በአዲስነት የምናድስባቸው ሶስት መንገዶች፡-
1.      አዲስ ፍጥረት መሆን
ሰው ስለሃጢያቱ እንደሞተለት እና የሃጢያቱን ዋጋ ሁሉ እንደከፈለለት በእግዚአብሄር ካላመነ ፣ ኢየሱስን እንደ አዳኙ ካልተቀበለና እግዚአብሄር በኢየሱስ ያዘጋጀለትን የመዳኛ መንገድ ካልተቀበለ የህይወት አዲስነት በፍፁም አይገኝም፡፡ ሰው ኢየሱስን ካልተቀበለ የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም፡፡
በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም። ዮሃንስ 3፡36
ኢየሱስን የተቀበለ ሰው ግን እግዚአብሄር ልጅ አድርጎ ይቀበለዋል በክርስቶስም አዲስ ፍጥረት ይሆናል፡፡
ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡17
2.     አእምሮን ማደስ
አዲሱን አመት በአዲስነት እንድንደሰትበት አሮጌውን አስተሳሰባችንን በእግዚአብሄር ቃል በማደስ እንደ አዲስ ፍጥረትነታችን መኖር ይኖርብናል፡፡
የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። ሮሜ 12፡2
የእግዚአብሄርን ቃል በመቀበል በልባችን ያለውን አለማዊ አስተሳሰብ ካላስወገድን በስተቀር አዲስ አመት አዲስ ይሆንልናል ማለት ዘበት ነው፡፡
ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ያዕቆብ 1፡21
3.     አዲሱን ሰው መልበስ
ምንም እንኳን አዲስ ፍጥረት መሆን ወሳኝ ቢሆንም አዲስን አመት አዲስ የሚያደርገው አዲስ ፍጥረት መሆን ብቻ አይደለም፡፡ በአዲስ ህይወት ለመመላለስ አእምሮን በእግዚአብሄር ቃል ማደስና እንደ እግዚአብሄር ቃል መኖር መመላለስ ይጠይቃል፡፡   
ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ኤፌሶን 4፡22-24
ኢየሱስን ተቀብለን አዲስ ፍጥረት ብንሆን ፣ አእምሮዋችንን በእግዚአብሄር ቃል ብናድስና እንደ አዲስ ፍጥረትነታችንና እንደታደሰ አእምሮ ብንመላለስ አዲሱ አመት በእውነት አዲስ ይሆንልናል፡፡ ህይወታችን እስካልተለወጠ ዘመናችን አይለወጥም፡፡ ህይወታችን በተለወጠ ቁጥር ዘመናችን እየታደሰ ይሄዳል፡፡
የንስሃ ፀሎት
እግዚአብሄር ሆይ ይህንን ቃል እንደሰማ ስለረዳኽኝ አመሰግንሀለሁ፡፡ ኢየሱስ ስለሃጢያቴ እንደሞተ አምናለሁ ፣ እግዚአብሄር ስለሃጢያቴ ከሙታን እንዳስነሳው አምናለሁ ኢየሱስም ጌታ እንደሆነ በአፌም እመሰክራለሁ፡፡ ሃጢያቴን ሁሉ ይቅር ስላልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ልጅህ አድርገህ ስለተቀበልከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡
በኢየሱስ ስም፡፡
አሜን  
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #እግዚአብሔር #እውቀት #ጥበብ #ነፍስ #መዳን #ሃሳብ #መልካም #መታዘዝ #ቅድስና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መጋቢ #እምነት #ተስፋ #ፍቅር #ጌታ #ሰላም #ደስታ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #መናገር #አእምሮ #ነፍስ #ቃል #ልጅ

No comments:

Post a Comment