Popular Posts

Tuesday, December 5, 2017

የንግድ ጥበብ እና ንግድ አላግባብ የሚያዝባቸው መንገዶች

ንግድ እንደማንኛውም ሙያ ጠቃሚና ግለሰብንም ሆነ ሃገርን የሚያሳድግ ምርታማ የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ እውነት ነው በአገራችን ካለፍንበት የኮሚኒዝም ስርአት አንፃር ይህ ሙያ እንደጨቋኝ ርህራሄ የሌለው ፍትህ ያለሆነ በዝባዥ ተደርጎ ተቆጥሮ ነበር፡፡
የኮሚኒዝሙ መንግስት ነጋዴውን የሚያይበት የነበረው አሉታዊ አስተያየት ከሰው አስተሳሰብ ውስጥ በቀላሉ የሚለቅ አይደለም፡፡
እውነት ነው ከፖለቲካ እስከ መምህርነት ማንኛም ሙያ በክፉ ሰዎች እጅ አላግባብ እንደሚያዝ ሁሉ ንግድም አላግባብ ሊያዝ ይችላል፡፡
የቱም ሙያ በራሱ ቅዱስም እርኩስም አይደለም፡፡ ቅዱስን እርኩስ የሚያደርገው የሚሰራው ሰው ነው፡፡ ስግብግብ ነጋዴ ንግዱን ያረክሰዋል፡፡ ስግብግብ ሃኪም የሰውን ህይወት የሚያተርፈውን የህክምና ሙያ አላግባብ ይይዘዋል ያጎሳቁለዋል፡፡
ንግድ ሰዎች የሚፈልጉትን እቃ በማቅረብ የሚያገለግል ሙያ ነው፡፡ ነጋዴ ሰዎች የሚፈልጉትን እቃ ከሚገኝበት ቦታ ፈልጎ በመግዛትና በማቅረብ ገዢዎቹን ያገለግላል፡፡ ነጋዴ የህብረተሰብ አገልጋይ ባለሙያ ነው፡፡
ንግድ አላግባብ የሚያዝባቸው መንገዶች
በጥራትና በመጠን ማጭበርበር
ሰው ስለሚገዛው ነገር ትክክለኛ መረጃ አግኝቶ መግዛት ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው፡፡ ሰው የፈለገውን ውሳኔ አነዳይወስን የተሰሳተ መረጃ በማቅረብ የሚያሳስት ሰው የንግድን አላማ እየሳተና የንግድን ሙያ እያጎሳቆለው ነው፡፡ ሰው ማወቅ የሚገባውን መረጃ ሁሉ ሰጥተን ሰው በራሱ እንዲወስን ስናደርግ እግዚአብሄር ደስ ይሰኛል፡፡ ለግል ጥቅማችን ሰውን ስናታልል እግዚአብሄር ደስ አይሰኝም፡፡
አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል። ምሳሌ 11፡1
እግዚአብሔር የተጭበረበረ ሚዛንን ይጸየፋል፤ ትክክለኛ መለኪያ ግን ደስ ያሰኘዋል። ምሳሌ 11፡1 (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ክፉ ፉክክር
የአለም ሃብት ለሁሉም ሰው በቂ ሆኖ እያለ ገዢን ወይም ተጠቃሚን በማገልገል ላይ ሳይሆን ሌላውን ነጋዴ ለመጣል ያነጣጠረ ዋጋን ያለአግባብ የመቀነስ ተንኰል ነጋዴውን ፣ ሃገርንና ተጠቃሚውን አያሳድግም፡፡ ንግድ እንደማንኛውም ሙያ ቀስ ተብሎ የሚታደግበት እንጂ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኮልበት በፍጥነት የሚወነጨፉበት ምትሃት አይደለም፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 1311
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 2820
ነጋዴ በራስ ወዳድነት ትንንሽ ነጋዴዎች በመጣል ንግዱን ራስ ብቻ ለመቆጣጠርና ዋጋውን ራሱ ብቻውን ለመወሰን መሞከር ክፉ የሃይል ጥማት ፍላጎት ነው፡፡     
ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት በልባችሁ ቢኖርባችሁ፥ አትመኩ በእውነትም ላይ አትዋሹ። ይህ ጥበብ ከላይ የሚወርድ አይደለም፤ ነገር ግን የምድር ነው፥ የሥጋም ነው፥ የአጋንንትም ነው፤ ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። ያዕቆብ 3፡14-16
ግብር አለመክፈል
መንግስት የተለያዩ የህዝብ የጋራ መጠቀሚያዎችን መንገድን ፣ ድልድይን ፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫና የመሳሰሉትን የሚሰራው ከግብር በሚሰበሰበው ገንዘብ ነው፡፡ መንግስት ለዜጋው ነፃ አገልግሎት የሚሰጡትን ሰራተኞች የሚከፍለው ከግብር ከሚሰበሰበው ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ግብርን መክፈል ትክክለኛ ነገር ነው፡፡ ምግብን በልተን ሳይከፍል ለመሄድ ህሊናችን እንደማይፈቅድልን ሁሉ በሃገሩ ላየ እየሰራን እና እያተረፍን ግብርን አለመክፈል ህሊናችንን እምቢ ሊለን ይገባል፡፡
ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። ሮሜ 13፡5፣6
ትርፍ ላይ ማተኮር
ነጋዴ የመጀመሪያው ትኩረቱ ሰዎች የሚፈልጉን እቃ በቅርብ ለተጠቃሚ ማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን ነጋዴ የሰውን ፍላጎት ከማቅረብ ይልቅ ከፍተኛ ትርፍ ማትረፍ ላይ ብቻ ካተኮረ ይስታል፡፡ አንዳንድ ዝቃዎች ሲጠፉ ልክ ሲወደዱ ለመሸጥ የሚደብቅና በዚያም እጠረት እንዲፈጠር የሚያደርግ ነጋዴ እግዚአብሄር ደስ አይሰኝበትም፡፡ ቢጠፋም ባይጠፋም ሰዎችን በማገልገል ላይ የሚያተኩር ነጋዴ እግዚአብሄር ይባርከዋል፡፡  
እህልን የሚያስቀር ሰው በሕዝብ ዘንድ ይረገማል፤ በረከት ግን በሚሸጠው ራስ ላይ ነው። ምሳሌ 11፡26
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ንግድ #መሸጥ #መለወጥ #ስኬት #ነጋዴ #ግብር #ታክስ #ትርፍ #ኪሳራ #መታዘዝ #ጥበብ #ሚዛን #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አላግባብ #መስፈርት #ማጎሳቆል #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment