Popular Posts

Follow by Email

Sunday, December 24, 2017

የእኔ ምስክርነት

አቢይ እባላለሁ፡፡ ጌታን ያገኘሁት በ 17 ዐመቴ ነበር፡፡
ጌታን ያገኘሁት በአክስታችን ምስክርነት ነበር፡፡ አክስታችን ጌታን የምታውቀው በደርግ ዘመን ነው፡፡ በደርግ ዘመን ጌታን በመመስከር ታስራ ታውቃለች ስለጌታ ብዙ ዋጋን የከፈለች የእምነት ሴት ነች፡፡ ሁሌ ስለጌታ ትመሰክርልን ነበር፡፡ ቤተክርስትያን ልዩ ፕሮግራም ሲኖር ዛሬ ድራማ አለ ኑ እዩ እያለች ባገኘነው አጋጣሚ ቃሉን እንድንሰማ ትጋብዘን ነበር፡፡
እኔ ለሃይማኖት ግድ አልነበረኝም፡፡ እንዲያውም 2 ሰአት ቤተክርስትያን መቀመጥ ጊዜን እንደማባከን ነበር የምቆጥረው፡፡
አባቴና እናቴ በትምህርት በጣም ያምኑ ስለነበረ እኔም በትምህርት በጣም አመን ነበር፡፡ ሰው ተምሮ ዲግሮ ካለው በቃ የህይወት ጥያቄው ይመለሰላ ብዬ አስብ ነበር፡፡ ስለዚህ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እያለሁ ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቼ አጠና ነበር፡፡ ወላጆቼ በጣም እንዳጠና ያበረታቱኝና እንደሚቻል ይነግሩኝ በእኔም ይተማመኑ ስለነበር እወድቃለሁ ብዬ አላስብም ነበር፡፡
ነገር ግን ማትሪክ አልመጣለኝም ነበር፡፡ የማትሪክ ውጤቴ ለዲግሪም ሆነ ለዲፕሎማ አለማሳለፉ የህይወት አመለካከቴን ቀየረው፡፡ ልቤን ያለዘጋጀሁለት ውድቀት ነበር፡፡ ህይወት ጨለመብኝ፡፡ የተለያዩ ኮርሶችን ለመውሰድ ሞክሬም እልተሳካልኝም፡፡
ያን ጊዜ ነው ጌታ ትኩረቴን ያገኘው፡እስከዚያ ድረስ ለጌታና ለመንፈሳዊ ነገር ትኩረት አልሰጥም ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ተስፋ የሚሆነኝን አገኘሁ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበር ጌታን የተቀበልኩት፡፡
ነገር ግን ጌታንም ተቀብዬ እንደሚገባ አልመላለስም ነበር፡፡ ሁልጊዜ አልፀልይም፡፡ ሁልጊዜ አላነብም፡፡ የምፀልይ የነበረው ችግር ሲገጥመኝ ብቻ ነበር፡፡ ጌታንም ብቀበል በእኔነት የተሞላሁ ነበርኩ፡፡ ጌታ ለሁሉም ነገሬ እንደሚያስፈልገኝ አላምንም ነበር፡፡
ነገር ግን አንድ ወንድም ወደ አንድ የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ይዞኝ ሄደ፡፡ የመፀሃፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቱ ከገባሁ ጀምሮ የእግዚአብሄርን ቃል በሃይል የሚያስተምሩ አስተማሪ ስለነበሩ እጅግ ወደድኩት በተከታታይ መማር ጀመርኩ፡፡ እዚያ እያለሁ ነበር እንግዲህ ጌታን ለማገልገል የወሰኩት፡፡ በተለይ የሚያስተምሩን አስተማሪ ጌታ እንዳገለግለው ሲጠራኝ ማቴዎስ 6፡25-33 ሰጠኝ ብለው ብዙ ጊዜ ስለ እምነት ያስተምሩን ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ስለምበላውና ስለምለብሰው መጨነቅ ከህይወቴ ሞተ፡፡
ጌታን ከመከተሌ ባሻገር ጌታን የማገልገል ውሳኔዬን ወላጆቼ በቀላሉ አላዩትም፡፡ በጊዜው ስራ አልሰራም ትምህርትም አልማርም በማለቴ እጅግ ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡ እኔ ግን የአገልግሎት ጥሪ በህይወቴ በግልፅ ስለሰማሁ በመንፈሳዊ የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርትና በአገልግሎት ቀጠልኩ፡፡
በዚያን ጊዜ አገልግሎት የጀመርኩት እኛ ቤት እሁድ ከሰአት 120 ፕሮግራም ሊያዩ የሚመጡትን ልጆች ሰብስቤ በማስተማር ነበር፡፡
አሁንም ጌታን በተለይ በማስተማር አገለግላለሁ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የማስተማር ፀጋ በህይወቴ እንደሚሰራ አይቻለሁ፡፡ በውስጤ የሚፈሰው ትምህርት ብዛት ለራሴም ያስደንቀኛል፡፡ ይህ የእኔ ችሎታ እንዳልሆነ ስለምረዳ ሁልጊዜ ትሁት ያደርገኛል፡፡ በእኔ ውስጥ ከሚሰራው የእግዚአብሄር ፀጋ ውጭ ምንም የሚያስመካ ነገር የለኝም፡፡ እግዚአብሄር ስለተጠቀመብኝ እንጂ እኔ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ፡፡
አሁን በዛን ጊዜ በወሰንኩት ጌታን እስከ መጨረሻው የመከተል ውሳኔ ደስተኛ ነኝ፡፡ ጌታን ለማገልግል እንደገና እንድወስን እድል ቢሰጠኝ ጌታን ለማገልግል የወሰንኩት ውሳኔ እንደገና እወስነዋለሁ፡፡ ጌታን ለማገልገል በመወሰኔ ሁሌ ከመደሰት በስተቀር አንድ ቀንም ተፀፅቼ አላውቅም፡፡ አንዳንዴ እንዲያውም ምነው አንድ ብቻ ሳይሆን ከአንድ በላይ ነፍስ ቢኖረኝና ለጌታ ባስገዛሁለት ብዬ አስባለሁ፡፡   
እግዚአብሄር በእነዚህ ሁሉ ዘመናት እንደ አይኑ ብሌን ሲንከባከበኝ አይቻለሁ፡፡ እግዚአብሄር በሁሉ ነገር ባርኮኛል፡፡ የሚያስፈልገኝ ነገር ሁሉ አለኝ፡፡ ስወድቅ ሲያነሳኝ ፣ ሳዝን ሲያኝናናኝ ፣ ስደክም ሲደግፈኝ አይቼዋለሁኝ፡፡ ከዚህ በላይ እንክብካቤ ከእግዚአብሄር አልጠብቅም፡፡ ከሚያደርግልኝ እንክብካቤ በላይ እንክብካቤ ያለም አይመሰለኝም፡፡
እንደተራራ የገዘፉትንና ይደረስባቸው ይሆን ብዬ ደጋግሜ የጠየኩትን ብዙ ህልሞቼን እግዚአብሄር አሳይቶኛል፡፡ ህልሜን እየኖርኩት ነው፡፡ ብዙ የሚፈፀሙ ህልሞች ደግሞ አሉኝ፡፡  
አሁን በህይወቴ እግዚአብሄር ደስተኛ ነኝ፡፡ አሁን ባለሁበት እግዚአብሄር ባደረሰኝ ደረጃ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ምንም እንደ ጎደለኝ አይሰማኝም፡፡ ከእኔ በላይ ደስተኛ ሰው በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የእግዚአብሄር ሰላም በውስጤ እንደወንዝ ይፈስሳል፡፡ በክርስቶስ ይህ ሁሉ ነፃነት አለ እንዴ ብዬ እስከማስብ ድረስ እጅግ ነፃነት ይሰማኛል፡፡
እነዚህን ሁሉ አመታት በድል የጠበቀኝን እንዳገለግለው ታማኝ አድርጎ የቆጠረኝን እግዚአብሄርን አመሰግነዋለሁ፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ገና #በዓል #ፍቅር #ተስፋ #ደስታ #መስዋእት #ምስክርነት #መዳን #ምስጋና #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #ብርሃን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ #ህይወት #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  #ኢየሱስ #ጌታ

No comments:

Post a Comment