Popular Posts

Wednesday, December 6, 2017

የማንነት ጥያቄ ሲመለስ- ሰው ገዢ ተደርጎ ተፈጥሮአል

የእግዚአብሄርን የጥንቱን አላማ የምናውቀው ወደ ጥንት አፈጣጠሩ ተመልሰን የእግዚአብሄርን ቃል ስናጠና ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ሲመለስ ብዙ የህይወት ጥያቄዎቻችን ይመለሳሉ፡፡
ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር ክብር ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል ነው፡፡ እግዚአብሄር የዘላለም ንጉስ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሄር መልክና አምሳል የተፈጠረው እንዲገዛ ነው፡፡ ሰው የተፈጠረው እግዚአብሄርን ወክሎ በእግዚአብሄር ቦታ በስልጣን እንዲገዛ ነው፡፡
እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ዘፍጥረት 1፡26
ሰው የተባረከው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተለቀቀው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የታጠቀው ለገዢነት ነው፡፡ ፈቃድ የተሰጠው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው ብቁ የተደረገው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተላከው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተወከለው ለገዢነት ነው፡፡ የተባረከው ሞገስ የተሰጠው ለገዢነት ነው፡፡ ሰው የተቀባው ለገዢነት ነው፡፡  
እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው። ዘፍጥረት 1፡26-28
ህዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት እግዚአብሄር ሙሴን ሲጠራው ለነፃነት አላማው የሚያስፈልገውን ስልጣን ሁሉ ሰጥቶት ነው፡፡ እግዚአብሄር ሙሴን ሲጠራው ማንም እንዳያቆመው በፈርኦን ላይ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶት ነው፡፡ ለዚህ ነው እግዚአብሄር ሙሴን እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ ያለው፡፡
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። ዘጸአት 7፡1
እኛንም ሲጠራን እግዚአብሄር አልሰሰተም፡፡ እግዚአብሄር የጠራን የመለኮታዊ ባህሪው ተካፋዮች እንድንሆን ነው፡፡ እግዚአብሄር የጠራን በህይወት በአሸናፊነት እግዚአብሄር የጠራንን ስራ ፈፅምን እንድናከብረው ነው፡፡ እግዚአብሄር የጠራን ምንም ሃይል እስከማያደናቅፈን ድረስ የሚያስፈልገንን የገዢነት ስልጣን ሁሉ ሰጥቶን ነው፡፡
የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። 2 ጴጥሮስ 1፡2-3
ኢየሱስ በምድር ሲመላለስ የዘመኑ ሃይማኖት መሪዎች ሊወግሩት በፈለጉ ጊዜ ሃጢያት ስለሰራ እንደማይወግሩት ነገር ግን የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ በማለቱ እንደሚወግሩት ነገሩት፡፡ 
ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። ዮሃንስ 10፡32-33
እርሱ ግን ለሰው ልጅ ገዢ ወይም አምላክ መባል ብርቅ እንዳይደለ አስረዳቸው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል የመጣላቸው ሰዎች እግዚአብሄር ቃል በመጣላቸው ክልል ገዢዎችና አማልክት እንደሆኑ በመፅሀፍ ቅዱስ እንደተፃፈ ኢየሱስ ቃሉን ጠቅሶ አስታወሳቸው፡፡ ኢየሱስ ስለማንም ሰው አመለካከት የእግዚአብሄር ቃል እንደማይሻር አስረዳቸው፡፡
ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ እኔ፦ አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን? መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ስላልሁ እናንተ አብ የቀደሰውን ወደ ዓለምም የላከውን፦ ትሳደባለህ ትሉታላችሁን? ዮሃንስ 10፡34-36 
አንዳንድ ሰው ለእግዚአብሔር ከአግዚአብሄር በላይ ፃዲቅ ሊሆን ሲሞክር የእግዚአብሄርን ቃል የሚለውን ለማለት እንኳን ይሳሳል፡፡ ከእግዚአብሄር በላይ ለእግዚአብሄር ልንቀናለት አንችልም፡፡ እግዚአብሄር ሰውን ካለስስት በመልኩና በአምሳሉ ስለፈጠረ በመልኩና በአምሳሉ ተፈጥሬያለሁ ማለት መፍራት የለብንም፡፡
ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና የሚለውን እንዳለ መቀበል እንጂ ለእግዚአብሄር ካለእውቀት በመቅናት ለማሻሻል መሞከር የለብንም፡፡

ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። መዝሙር 139፡14
ሰዎች የእግዚአብሄርን ቃል እንዳለ ካልተቀበሉትና በሰው ትምህርት ለማሻል ከሞከሩ ሃይሉን ያሳጡታል፡፡
ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ እንደዚሁም ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ። ማርቆስ 7፡13
ሰዎች ለእግዚአብሄር ከራሱ ከእግዚአብሄር በላይ ሲጠነቀቁለት ይስታሉ፡፡ ጌታን ማምለክ ማለት እግዚአብሄር በቃሉ ናችሁ ያለንን ነን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄርን መፍራት እግዚአብሄር በቃሉ አይደለህም ያለኝን አይደለሁም ብሎ መቆም ነው፡፡ እግዚአብሄርን ማክበር የእግዚአብሄርን ቃል ሳያሻሽሉ ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ አንዳለ አሜን ብሎ መቀበል ነው፡፡  
መፅሃፍ ቅዱስ ያለውን ላለማለት ሰዎች አጉል ትህትና ሲይዛቸው ከእግዚአብሄር በረከት ይጎድላሉ፡፡ ሰዎች ቃሉ ያለውን ለማለት ካልፈለጉ ትህትና ሳይሆን ትእቢት ነው፡፡ ትህትና እንደ ማሪያም የእግዚአብሄርን ቃል አሜን ብሎ መቀበል ነው፡፡ ሉቃስ 1፡38
ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ። ቆላስይስ 2፡18
መፅሃፍ ቅዱስ የመለኮት ሙላት በተሞላ ኢየሱስ ተሞልታችኋል ሲል ትሁት ሰው አሜን ይላል፡፡
በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና፤ ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። ቆላስይስ 2፡9-10
እግዚአብሄርን የምናመለከው በእውነትና በመንፈስ እንጂ በራሳችን አነሳሽነት በገዛ ፈቃዳችን እና ፍልስፍናችን አይደለም፡፡  
ይህ እንደ ገዛ ፈቃድህ በማምለክና በትሕትና ሥጋንም በመጨቆን ጥበብ ያለው ይመስላል፥ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅምም። ቆላስይስ 2፡23
በእውነትና እንደ እግዚአብሄር ቃል የሆነን አምልኮ እንጂ በገዛ ፈቃዳችን ራሳችንን ቃሉ እንደማይለው ማዋረድ "የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል" 2ኛ ጢሞ 3፡5 የተባሉ ባዶ የሃይማኖት መልክ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡ ክርስትና እግዚአብሄር ምንም ይሁን በቃሉ ነህ ያለውን ነኝ ብሎ መቀበል ነው፡፡ ክርስትና በቃሉ እግዚአብሄር አይደለህም ያለውን አይደለሁም ብሎ ለመቀበል ትሁት መሆን ነው፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #በክርስቶስ #መልክ #አምሳል #የእግዚአብሄርልጅ #ወዳጅ #የንጉስልጅ #ልጅነት ##መንፈስ #ነፍስ  #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ማየት #የእግዚአብሄርመንግስት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #አዲስፍጥረት #ክርስቶስ #የእግዚአብሄርቤተሰብ #ማእረግ #ስልጣን #ዳግመኛመወለድ

No comments:

Post a Comment