Popular Posts

Monday, December 11, 2017

አያዋጣም

በንግድ አንድን እቃ ሸጠን የምናገኘውን ገንዘብ ብቻ አይተን ያዋጣል ማለት አንችልም፡፡ የአንድን ነገር አዋጪነቱን ለማወቅ አንድን ነገር የሸጥንበትን ዋጋ ብቻ ሳይሆን የገዛንበትን ዋጋም ከግምት ውስጥ እናስገባዋለን፡፡ ምንም በውድ ዋጋ ቢሸጥ በውድ ዋጋ የተገዛ ከሆነና ትርፉን እጅግ የሚቀንስ ከሆነ አዋጭ አይደለም እንላለን፡፡ እንደ ነጋዴ አዋጪ ያልሆነን ነገር ለመሸጥ ፍላጎት አይኖረንም፡፡
በህይወታችን ጊዜያችንን ፣ ጉልበታችንንና እውቀታችንን የምናፈስባቸው ነገሮች ብዙን ጊዜ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ነገር ግን የምንከፍለው ዋጋ ከምናገኘው ውጤት ከበለጠ ወይም እኩል ከሆነ አዋጭ አይደለም፡፡ አንዳንድ የምናደርጋቸው ነገሮች በእርግጥ ይከናወናሉ ነገር ግን ካወጣነው ጉልበት አንፃር አዋጪ አይደሉም፡፡ በጥበብ ነው ያደረግነው አዋጪ ነው የሚባለው ነገር የምንከፍለው ዋጋ ሲያንስ የምናገኘው ሲበዛ ነው፡፡
በክርስትናም እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮች ጥሩ ናቸው ነገር ግን ከፍተኛ ጥቅም አይሰጡንም፡፡ አንዳንድ ነገሮች አይጎዱም ነገር ግን ከፍተኛን ጥቅም አይሰጡም፡፡ በክርስትና አዋጪ ስለሆኑ የጥበብ ውሳኔዎች እንመልከት፡፡
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው ነፍሱን አይዝም በጌታ ላይ ይጥላል፡፡ አዋጪነቱን የተረዳ ሰው የእግዚአብሄርን ቃል ታዞ ከነፍሱ ድምፅ በላይ የጌታን ድምፅ ይሰማል ይታዘዛል፡፡ አዋጪነቱን የተረዳ ሰው   
ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ማቴዎስ 16፡25
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ብልሃተኛ አናፂ ዋጋ መክፈል በሚገባው በጥራት ላይ ዋጋ ይከፍላል፡፡
ጥበበኛ ሰው ዋጋ በሚያስከፍል እውነተኛ ነገር ላይ በደስታ ዋጋ ይከፍላል፡፡ አሁን ዋጋ የከፈለበት ነገር ነገ በብዙ እጥፍ ይጠቅመዋል፡፡ ብልሃተኛ አናፂ ለትክለክለኛ ነገር ዋጋ ይከፍላል፡፡ ትክክለኛ አናፂ ቤቱን ቶሎ ሰርቶ መጨረሱን ብቻ ሳይሆን ቤቱ በትክክለኛ ነገር መሰራቱን ያረጋግጣል፡፡ ትክክለኛ አናፂ ገንብቶ ለመጨረስ አይቸኩልም ነገር ግን በሚቆይ በሚበረክትና ዘላቂ ነገር ላይ ዋጋ ለመክፈል ይታገሳል፡፡   
ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፥ እርሱ ራሱ ግን ይድናል ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል። 1ኛ ቆሮንቶስ ሰዎች 3፡12-15
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው የጊዜው መከራ በመታገስ የሚበልጠውን ክብር ይጠብቃል፡፡
ሰው ማለፍ ያለበትን የጊዜውን መከራ በራሱ መንገድ ለመሸወድ ቢሞክር አያዋጣም፡፡ ሰው በራሱ መንገድ ከእግዚአብሄር ሃሳብ ወጥቶ ማለፍ ያለበትን መከራ ሊሸውደው ይችላል፡፡ ይህ ግን ትርፉና ኪሳራው ሲታይ አዋጪ አይደለም፡፡ የሚያዋጣው ከሚመጣው ክብር ጋር ሲመዛዘን ቀላል የሆነውን የጊዜውን ስቃይ መታገስ ነው፡፡
የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው። 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡17-18
ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። ሮሜ 8፡18
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰባኪ የሰዎችን እምነት በእግዚአብሄር ሃይል ላይ እንዲሆን ዋጋ ይከፍላል፡፡
ጠቢብ ሰባኪ ህይወቱን በንግግር ብልጫ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሄር ቃልና ሃይል ላይ ይመሰርታል፡፡ ጠቢብ ሰው በእምነት እንጂ በብልጣብልጥነት አይኖርም፡፡ ጠቢብ ሰባኪ የሚሰሙትን ለእምነት ኑሮ እንጂ ለብልጣብልጥነት ምሳሌ አይሆናቸውም፡፡ ጠቢብ ሰባኪ ሰዎች በእግዚአብሄር ቃል ጥበብ ላይ እንጂ በሰው ጥበብ ላይ እንዲታመኑ አያደርጋቸውም፡፡ ሰው ካገለገለና ከሰበከ ላይቀር እውነተኛውን ነገር ሰብኮ እውነተኛውን ነገር ኖሮ ህይወቱን ቢያሳልፍ ብቻ አዋጪ ነው፡፡     
እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። 1 ቆሮንቶስ 2፡1፣4-5
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ኢንቨስተር በሰው ልጆች መዳን ላይ ገንዘቡን ያፈሳል፡፡
አዋጪነቱን የተረዳ ባለገንዘብ በምድር ላይ የሚቀር ጊዜያዊ ነገርን ሲሰራ አይኖርም፡፡ አዋጪነቱን የተረዳ ሰው ገንዘቡን ዘላለማዊ ዋጋ ያለው ነገር ላይ ያጠፋል፡፡ አዋጪነቱን የተረዳ ሰው የሰው ልጆችን ወደ መግስተ ሰማያት እንዲሄዱ በመርዳት የላቀ ዋጋ ያለው የሰዎች መዳን ላይ ያውለዋል፡፡ አዋጭነቱን የተረዳ ሰው ብዙዎችን ለመታደግ የሚውለውን ሃብቱን ሁሉ በራሱ ላይ ብቻ አውሎ እየጨርሰውም፡፡  
እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ሉቃስ 16፡9
ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። ማቴዎስ 6፡19-21
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ባለጠጋ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለእውነተኛ ህይወት በመልካም ስራ ባለጠጋ ይሆናል፡፡
አዋጪነቱን የተረዳ ባለጠጋ ባለጠግነት ግብ እንዳልሆነ ይረዳል፡፡ ባለጠግነት የመልካም ስራ ባለጠግነት የመጀመሪያ ደተረጃ እንጂ የመጨረሻው ደረጃ እነዳልሆነ ይረዳል፡፡ የገባው ባለጠጋ ባለጠግነቱ ታማኝነቱ የሚፈተንበት መልካም አጋጣሚ ብቻ እንደሆነ ይረዳል፡፡ የገባው ባለጠጋ በገንዘብ ባለጠግነቱ ልክ የመልካም ባለጠጋ ለመሆን ይተጋል፡፡ የገባው የገንዘብ ባለጠጋ የገንዘቡን ባለጠግነት ወደ እውነተኛ የመልካም ስራ ባለጠግነት ይለውጠዋል፡፡
እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ፥ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፡18-19
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው አለሙን ሁሉ አትርፎ ነፍሱን ማጉደል አይፈልግም፡፡
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው አለሙን ሁሉ አጥቶ ነፍሱን ቢያጎድል ይመርጣል፡፡
ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ማቴዎስ 16፡26
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው ስሜቱን ይገዛል እንጂ የከበረውን ብኩርናውን በጊዜያዊ ጥቅም አይለውጠውም፡፡
ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ። ዕብራውያን 12፡16
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው በታማኝነት ይጠብቃል እንጂ መሰረት ለሌላት ፈጥና ለምትከማች ሃብት አይጓጓም አላስፈላጊ ዋጋም አይከፍልም፡፡
በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች። ምሳሌ 13፡11
የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም። ምሳሌ 28፡20
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው እግዚአብሄር እንዲያከብረው ቀድሞ ራሱን ያዋርዳል፡፡
ራስን ማክበር ከንቱ ድካምና ንፋስን እንደ መከተል መሆኑን የተረዳ ሰው ራሱን ለማክበር ሲሯሯጥ አይታይም፡፡ ራስን ማክበር ወጭው ብዙ ገቢው ግን ጥቂት መሆኑን የተረዳ ሰው እራሱን ለማክበር መውጣት መውረዱን ትቶ እግዚአብሄር እንዲያከብረው ለእግዚአብሄር ጊዜ ይሰጣል፡፡ አዋጭነቱን የተረዳ ሰው እግዚአብሄር ያልሰጠውን ክብር እጁን ተንጠራርቶ እራሱ እይወስድም እግዚአብሄር እስኪሰጠው የእግዚአብሄርን ጊዜ በትግስት ይጠብቃል፡፡
እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡5-6
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው ይባርካል በረከትን ይወርሳል እንጂ ማንንም አይረግምም፡፡
ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡9
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው ራሱን ለመንፈሳዊ ነገር ያስለምዳል፡፡
ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፥ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 4፡8
አዋጪነቱን የተረዳ ብልሃተኛ ሰው ለዘላለም በሚኖረው በቃሉ ለመኖር የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ይከፍላል፡፡
አዋጭነቱ የተረዳ ሰው ከእግዚአብሄር ቃል ውጭ ያለን ማንኛውንም ነገር ላለማድረግና ህይወቱን ላለማባከን ይሳሳል፡፡ አዋጭነቱን የተረዳ ሰው አስቸጋሪ ቢሆን እንኳን ለእግዚአብሄር ቃል ዋጋን በደስታ ይከፍላል፡፡ አዋጭነቱን የተረዳ ሰው ምንም ወደታች ቢያስወርደውና ቢያስቆፍረውም በቃሉ የተመሰረተ አስተማማኝ ህይወትን ለመገንባት ይተጋል፡፡
ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ። ሉቃስ 6፡47-49
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ራእይ #መዳን #እምነት #አንድነት #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ህብረት #መፅሃፍቅዱስ #ሰላም #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ #እወጃ #የዘላለምህይወት #ፅናት #ትግስት #መሪ

No comments:

Post a Comment