Popular Posts

Thursday, December 21, 2017

የሃቀኛው ንጉስ ታሪክ

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት ምክኒያቶች አሉ፡፡ ኢየሱስ ራሱን ሳያዋርድ በእግዚአብሄር መልክ እየኖረ እኛን ያላዳነበት ምክኒያት አለው፡፡ ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት 5 ምክንያቶችን ከእግዚአብሄር ቃል እንመልከት፡፡
ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት 5 ምክንያቶች፡-
የእግዚአብሄር ፅድቅ ስለሚጠይቀው ነው፡፡
በድሮ ዘመን በአንድ አገር ውስጥ አንድ ሀቀኛ ንጉስ ይኖር ነበረ ይባላል ፡፡ አንድ ጊዜ ይህንን ጥፋት ያጠፋ ሰው በአርባ ግርፋት ይቀጣል ብሎ ህግ ያወጣል፡፡ ንጉስ ሲኖር ሲኖር ቆይቶ አንድ ቀን ይህን ያደረገ አርባ ይገረፋል ብሎ የተናገረበትን ጥፋት ያጠፋ ሰው ይዘውለት ይመጣሉ፡፡ ያ ጥፋተኛ እናቱ ነበረች፡፡ ንጉሱ እናቱ ጋር ሲደረስ ህጉን ለመሻር አልቻለም፡፡
ስለዚህ እንዲህ አለ፡፡ ስለ እናቴ ስል የሃገሩ ህግ ብሽር እውነተኛ አልሆንም፡፡ ነገር ግን ስለእናቴ ስል አርባውን ግርፋት እኔ ራሴ እገረፍላታለሁ በማለት ህጉንም ሳይሽረው ህጉንም ለመፈፀም በእናቱ ፋንታ አርባውን ግርፋት ተገረፈላት ይባላል፡፡
ሃጢያትን የሰራች ነፍስ እርሱዋ ትሞታለች ያለው እግዚአብሄር ቃሉን አይለውጥም፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እግዚአብሄር በመልክና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ለዘላለም ከእርሱ ሲለያይ ማየት አልወደደም፡፡ ስለዚህ ህጉንም ሳይለውጥ ህጉን የሚፈፅምበትን መንገድ አዘጋጀ፡፡ ስለዚህ ሃጢያት ያላቀውን ልጄን እልካለሁ፡፡ ስለሃጢያታቸው ሙሉውን የሞት ዋጋ ይከፍላል በማለት አብ ኢየሱስን ወደ ምድር ላከው፡፡
ኢየሱስ ወደምድር የተላከው ሃጢያትን የሰራች ነፍስ እርስዋ ትሞታለች የሚለው የፅድቅ ቃል ሙሉ ለሙሉ እንዲፈፀም ነው፡፡
ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች፤ ሕዝቅኤል 18፡20
የሰው ልጅ ሊፈፅም ያልቻለውን እግዚአብሄር በሃጢያተኛ ልጅ ምሳሌ አድርጎ ኢየሱስን በመላክ የህጉን ፍላጎት ሁሉ ፈፅሞታል፡፡
ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በማንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ። ሮሜ 8፡3-4
ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ምንም ቢወደንም ስለሚወደን እኛ ጋር ሲደርስ ህጉን ስለማይሽር ፃዲቅ ስለሆነ ነው፡፡
ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት - ለእኛ የትህትናና የልጅነት ክብር ምሳሌ ለመሆን ነው
እግዚአብሄርን ያየው አንድስ እንኳን የለም፡፡ እግዚአብሄርን ወደምድር ወርዶ በሰው ቋንቋ የተረከው ኢየሱስ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ በአባቱ ዘንድ ያለውን ክብር በተግባር ያየነው በኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስን አይተን ነው የልጅነት ስልጣናችንን የምንረዳው፡፡ ኢየሱስን አይተን ነው ፀሎታችን በእግዚአብሄር ዘንድ እንዴት እንደሚሰማ የምናውቀው፡፡ እግዚአብሄር ኢየሱስን እንዴት እንደወደደው አይተን ነው እኛን እንዴት እንደወደደን የምናውቀው፡፡
እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል። ዮሃንስ 17፡22-23
እግዚአብሄር በተለያየ መንገድ ራሱን በከፊል ቢገልጽፅም ኢየሱስ ግን የእግዚአብሄር ሙሉ ነፀብራቅ ነው፡፡
መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። ዮሃንስ 1፡18
ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ዕብራውያን 1፡1-3
ኢየሱስ በስጋ መወለድ የነበረበት - ሰይጣንን እንደ ሰው ለመርታት ነው
እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው በመልኩና በአምሳሉ ነው፡፡ እግዚአብሄረ ሰውን የፈጠረው እንዲገዛ ነው፡፡ የዚህ አለም ገዢ ሰው ነበር፡፡ ሰው ግን እግዚአብሄርን መታዘዝ ትቶ የሰይጣንን ቃል ሲሰማ የልጅነት የገዢነት ስልጣኑን አጣው፡፡ ሰው በራሱ እጅ ነው ስልጣኑን ለሰይጣን አሳልፎ የሰጠው፡፡ ሰይጣን የዚህ አለም ገዢ እንዲሆን ያደረገው ሰው ነው፡፡
ስለዚህ በሰው አለመታተዘዝ የታጣውን ስልጣን መመለስ የሚቻለው በሰው መታዘዝ ነው፡፡ በሰው ሃጢያት የተነጠቀውን የሰውን ስልጣን መመለስ የሚቻለው ሃጢያት በሌለበት ሰው ነው፡፡ በሰው የተነጠቀውን ስልጣን በአምላክ መመለስ አግባብ አይደለም፡፡
እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ። ዕብራውያን 2፡14-15
አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።  ቆላስይስ 2፡15
ኢየሱስ በምድር ላይ እንደፍፁም ሰው ባይመላለሰ ኖሮ ኢየሱስን እንድንመስል አይጠበቅብንንም ነበር፡፡ ኢየሱስ እንደ እኛው በነገር ሁሉ ተፈትኖ እንደ ሰውነት ባይኖር ኖሮ ክርስቶስን መምሰላችን ተግባራዊ አይሆንም ነበር፡፡
ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። ሮሜ 8፡29-30
እግዚአብሄር ለሰው ያለውን ክብር ለማሳየት ነው
አንዳንድ ጊዜ አንድን እቃ ለመግዛት እንፈልግና የእቃውን ጥራቱን ለማወቅ እውቀቱ ከሌለን ዋጋውን እናያለን፡፡ ለእቃው የሚጠየቀውን ዋጋ አይተን የእቃውን ጥራት እንገምታለን፡፡ ብዙ ገንዘብ የሚጠየቅለ እቃ ዋጋው ከፍ ያለ ውድ እቃ ነው፡፡ ትንሽ ገንዘብ የሚጠየቅለት እቃ ደግሞ ዋጋው ዝቅ ያለ ርካሽ እቃ ነው፡፡ እኛን ለማዳን የተከፈለውን ዋጋ ስናይ የእኛን ዋጋ እናይበታለን፡፡ የክብራችንን ከፍተኝነት የምናውቅው ከእኛ የተከፈለውን ዋጋ በማየት ነው፡፡
ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን፥ ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡18-19
እንዲያውም በምድር ላይ በአምላክነት መመላሱ ሳይሆን እንደ እኛ በስጋ መመላለሱን አለማመን ነው ከእምነት የሚያወጣው፡፡
የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። 1 ዮሐንስ 4፡2-3
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos

#ኢየሱስ #ጌታ #ስጋናደም #የልጅነትክብር #ክብር #የልጅነትስልጣን #ሰውነት #ህይወት #ትንሳኤ #ሃይል #ስልጣን #ፋሲካ #ትንሳኤ #ሞት #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መንፈስቅዱስ  #ፌስቡክ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ  

No comments:

Post a Comment