Popular Posts

Follow by Email

Saturday, December 2, 2017

ከወገዛ ውስጥ የተሻለን ነገር ማውጣት

ከዚህ በፊት ወገዛን የምንመልስበት የተሳሳቱትን መንገዶችን ለውግዘት የተሳሳቱ መልሶች በሚለው በአጭር ፅሁፌ አስረድቼ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ከወገዛ ውስጥ እንዴት የተሻለን ነገር ማውጣት እንደምንችል እንመለከታለን፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የወገዛ አላማ ሰዎችን መመለስ ማቅናት መሆን አለበት፡፡
ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ገላትያ 6፡1
የወገዛ አላማ ሰዎችን መመለስ ማቅናት ይሁን አይሁን መነሻ ሃሳቡን መመርመር ወይም መፅሃፍ ቅዱሳዊ  ቅደም ተከተሉን ይከተል አይከተል ራሱን ማየት የአውጋዡ ሃላፊነት ነው፡፡
ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። ማቴዎስ 18፡15-18
የአውጋዡ አላማ ማቅናት ይሁንም አይሁን ወይም መፅሃፍ ቅዱሳዊ ቅደም ተከተሉን ይከተል አይከተል ተወጋዡ ሁልጊዜ ከወገዛው ውስጥ በጥበብ የሚያወጣቸው ጠቃሚ ነገሮች አሉ፡፡
ወገዛ ራሳችንን የምናይበት ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎት ሩጫ ባተሌ ስለምንሆን የሚገባንን ያህል ራሳችንን ማየት ያቅተናል፡፡ ወገዛ ሲደርስብን ግን ሳንወድ በግዳችን ስለህይወታችን ስለትምህርታችንና ስለኑሮዋችን እንደገና በደንብ እንድናስብ ያስገድደናል፡፡ ህይወታችንን በቅንነት ካየን ወገዛ በህይወታችን ያለውን ትክክለኛ ትምህርትና ልምምድ አጠንክረን ለመቀጠል የምንወስንበት ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ትምህርታችንና አካሄዳችን ደግሞ እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆነና ጥበብ የጎደለው ከሆነ እንዴት አድርገን እንደምናስተካክል የምንወስንበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡
እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ገላትያ 2፡2
ወገዛ ወደ እግዚአብሄር የምንቀርብት አጋጣሚ ነው፡፡
ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሄር የምንቀርብ ቢሆንም ነገር ግን ማንም ተሳስቶ ህይወቱን ማባከን ስለማይፈልግ በወገዛ ወቅት ይበልጥ ወደ እግዚአብሄር መቅረብ ያስፈልገናል፡፡ ስለትምህርታችን ስለአካሄዳችን ወደ እግዚአብሄር መቅረብ እና ልባችንን መፈተሽ ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ለእግዚአብሄር ለመኖር እስከወሰንን ድረስ በእግዚአብሄር ፊት በመቅረብና መንፈስ ቅዱስ ልባችንን እንዲፈትሽ በመፍቀድ  የምናጣው ምንም ነገር የለም፡፡
አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። መዝሙር 51፡10
መንፈስ ቅዱስ በሚያሳየን ነገር ብቻ ንስሃ ገብተን መመለስ ሲኖርብን መንፈስ ቅዱስ ባላሳየን ነገር ግን ራሳችንን ላለመኮነን መጠንቀቅ አለብን፡፡  
ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 4፡3
ወገዛ ልንወድቅ እንድምንችል የሚያስታውስ አስታዋሽ ነው፡፡
የወደቁ ሰዎች የጋራ ባህሪያቸው ልወድቅ አልችልም ከመውደቅ አልፌያለሁ ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ ሰው ልወድቅ እችላለሁ ብሎ ከተጠነቀቀ ላለመውደቅ ሃይል ይሆነዋል፡፡ ሰው ግን ልወድቅ አልችልም ካለ መጠንቀቁን ይተዋል ይወድቃል፡፡ ሰው ልወድቅ እችላለሁ ካለ በራሱ ጉልበት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሄር ሃይል ላይ ይታመናል፡፡ 
ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡12
ወገዛ ሰውን በማዋረድ የእግዚአብሄር ፀጋ እንዲበዛለት ያደርጋል
ሰው በትምህርቱ ከተሳሳተ እና በአካሄዱ ከሳተ መመለስ አለበት፡፡ ሰው ራሱን አዋርዶ ከተመለሰ የእግዚአብሄር ሃይል በእርሱ ላይ በሃይል ይሰራል፡፡ የእግዚአብሄር አላማ የሰዎች መመለስ ብቻ ነው፡፡ የሰዎች ውድቀት አግዚአብሄርን አያስደስተውም፡፡ ሰው የወደቀውን ሰው ላይረሳ ይችላል፡፡ እግዚአብሄር ግን ከተሳሳተበት አቅጣጫ በዞረ ጊዜ ስህተት እንዳልሰራ አድርጎ ተቀብሎታል፡፡ ሰው በሳተበት ነገር ራሱን ትሁት ካደረገና ከተመለሰ የእግዚአብሄር ፀጋ ይበዛለታል፡፡  
ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። ያዕቆብ 4፡6
የተወገዘ ሰው ስለአውጋዦች እግዚአብሄርን ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡
የተወገዘ ሰው ብወድቅ እንኳን የሚነግሩኝ ሰዎች አሉ ብሎ ስለአውጋዦች እግዚአብሄርን ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡ የሚመረምር ሰውን ማግኘት ትልቅ እድል ነው፡፡ የሰው ፍርድ ሁሌ ትክክልም ባይሆን በትክክሉ ፍርድ ተጠቃሚ ለመሆን የሚመርመር ሰው በአካባቢ ማግኘት በረከት ነው፡፡ የሚተቹና የሚመረምሩ ሰዎች በአጠገቡ የሌለ ሰው መቼ እንደወደቀ አያውቅም፡፡
ለተጨማሪ ፅሁፎች https://www.facebook.com/abiy.wakuma/notes
ለቪዲዮ መልእክቶች https://www.youtube.com/user/awordm/videos
#ኢየሱስ #ጌታ #አገልጋይ #ወገዛ #ስህተተ #ልብ #መሪ #ህሊና #ቀራጭ #ወገዛ #ትህትና #ፀጋ #ተቃውሞ #ቤተክርስትያን #አማርኛ #ስብከት #መዳን #መፅሃፍቅዱስ #መነሻሃሳብ #ነቢይ #አቢይ #አቢይዋቁማ #አቢይዋቁማዲንሳ

No comments:

Post a Comment