Popular Posts

Monday, August 7, 2023

የተመሳሳይ ፆታን መቃወሚያ ስምንቱ ስልቶች

 

በሰፊው የተከፈተውን የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ለማስፋፋት የተከፈተውን ዘመቻ ለመመከት ከዚህ በታችን የተዘረዘሩትን ስምንት መፍትሄዎች አቅርቤያለሁ መጨመር አለበት መቀነስ አለበት የምትሉትን አስተያየት ስጡበት፡፡

1.       በእግዚአብሔር ቃል ራሳችንን ማስታጠቅ

መፅሃፍ ቅዱስ ስለሁሉም ችግር መፅሃፍ ቅዱስ መልስ አለው፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ስለተመሳሳይ ፆታ ምንነት በሚገባ ያስተምራል፡፡

ተቃውሞዋችን በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ላይ ብቻ መመስረት አለበት፡፡ መፅሃፍ ቅዱስ ሰውን እንዴት ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠረው እና የወንድ እና የሴት ግንኙነት በአንድነተ የእግዚአብሔርን ሙሉ መልክ አንደሚገልፅ ማጥናት ራስን ማስታጠቅ ይጠይቃል፡፡

የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው። እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፥ ባረካቸውም። ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው። ኦሪት ዘፍጥረት 5፡1-2

2.       አለመፍራት

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ሃጢያት ሃያል ቢመስልም ባዶ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ላይ መታመን እንጂ በፍርሃት የምናደርጋቸው ነገሮች ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፡፡

ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡15

እነርሱ የእግዚአብሔርን ቃል የተቃወሙ እነርሱ ይፍሩ እንጂ እኛ እንዴት እንፈራለን?ለአላማቸው ትልቁ እንቅፋት የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያውቁታል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ብዙ ሰዎች ተነስተዋል ግን ጠፍተዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ለዘላም ይኖራል፡፡

3.       የእነርሱ መጠቀሚያ አለመሆን

ሰይጣን ትኩረት ይፈልጋል፡፡ ሰይጣን መረሳት አይፈልግም፡፡  አንዳንድ ጊዜ እነርሱ ይቆሰቁሱን እና እኛ በፍርሃት ስንወራጭ እናራግብላቸዋለን፡፡ እጅግ ተስፋፍቶዋል በተባለው በአሜሪካ እንኳን በአጠቃላይ 4 በመቶ አይሆኑም፡፡ እነርሱ ግን በላናችሁ በማለት በማስፈራራት 96 በመቶውን ህዝብ ያናውጣሉ፡፡ ከአራት በመቶ በታችን የሆኑ ጥቂቶች ከ96 በመቶ በላይ የሆነውን ህዝብ ህግ ካላስለወጥን በማለይ ያስፈራራሉ፡፡ አንዳንዴ ሰይጣንን የምንቀጣበት እንዱ መንገድ ንቆ ማለፍ ነው፡፡ https://williamsinstitute.law.ucla.edu/publications/how-many-people-lgbt/

በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና። 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 2፡11

4.       ይህ የተመሳሳይ ፆታ ችግር አዲስ እንዳልሆነ መረዳት

ይህ ችግር አዲስ ችግር አይደለም፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረ አመፅ ነው፡፡ እንዲሁም ሃዋርያው ጳውሎስ መልስን የመለሰበት አሮጌ ችግር ነው፡፡  ሃጢያት በአለም ላይ እንዳለ ሁሉ የተመሳይ ፆታ ሃጢያት ነበረ አለ ይኖራል፡፡

 

ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤

እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ። ወደ ሮሜ ሰዎች 1፡26-27

5.       መውደድ

በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ላሉ ሰዎች ይታዘንላቸዋል እንጂ አይጠሉም፡፡ የፍቅር ልብን ማሳየት ወሳኝ ነው፡፡ ወደድናቸው በፍቅር እና በርህራሄ ተመለከትናቸው ማለት ሃጢያቱን ተቀበልነው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የማንወደውን ሰው ልንፀልይለት እና ልናገለግለው ስለማንችል በፍቅር አይን ማየት ወሳኝ ነው፡፡

6.       ባገኘነው አጋጣሚ እንደ እግዚአብሄር ቃል መቃወም

ባገኘነው አጋጣሚ የተቃውሞ ድምፃችንን ማሰማት ይጠበቅብናል፡፡ ነገር ግን በአክብሮት እና በትህትና ማድረግ ደግሞ አለብን፡፡

በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3፡15

7.       የጠላት ጥቃት እንደሆነ መገንዘብ

የእግዚአብሔር ሙሉ መልክ የሚንፀባረቀው በወንድ እና በሴት ግንኙነት ነው፡፡ ጋብቻ በዝምታ ስለእግዚአብሄር ህልውና ይናገራል፡፡ ታዲያ ሰይጣን ይህን መልክ ለማጥፋት ላጲስ ይዞ ተነስቶዋል፡፡ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን መለማመድ ከሰው የተፈጥሮ ፍላጎት በላይ የሰይጣን መጠቀሚያነት መሆኑን አውቀን በእምነት ፀንተን መቃወም አለብን፡፡ የሰይጣንን መንፈሳ ጥቃት በሰውኛ መመለስ አንችልም፡፡

በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡10-12

8.       ብሄርተኝነትን አለመቀላቀል

በእኛ ባህል ብለን ከመቃወም ከጀመርን ልንሳሳት እንችላለን፡፡ መቃወም ያለብን እንደእግዚአብሄር ቃል እንጂ እንደ ባህላችን አይደለም፡፡ እንደ ባህላችን ከተቃወምን ክርክሩ ይበዛል፡፡ አንድ አስተማማኝ ባህል ያለን የእግዚአብሔር ቃል ባህል ነው፡፡ የማይናወጠው የማይስተካከልው ባህል እግዚአብሔርን የመፍራት ባህል እንጂ የኢትዮጲያዊነት እና የአሜሪካዊነት ባህል አይደለም፡፡ ባህል በየጊዜው ይለዋወጣል፡፡ የማይለወጥ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ ተቃውሞዋችንን ያጠናከርን መስሎን እንደ ባህላችን በማለት መቃወም የለብንም፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

#ኢየሱስ #ጌታ #ጋብቻ #ፍቅር #ተቃራኒፆታ #ወንድ #ሴት #ወንድእናሴት #ተመሳሳይፆታ #መፅሐፍቅዱስ #ቃል #እግዚአብሔር #ትዳር  #ግብረሰዶም #ግብረሰዶማዊነት


No comments:

Post a Comment