Popular Posts

Monday, August 21, 2023

ንስሐ በራስ መንገድ እግዚአብሔርን እንደገና ማስደሰት አይደለም

እናንተም። እግዚአብሔርን በድለናል አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን ሁሉ እንወጣለን፥ እንዋጋማለን ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፥ ወደ ተራራማውም አገር መውጣትን አቀለላችሁት። እግዚአብሔርም፦ እኔ በእናንተ መካከል አይደለሁምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ፥ አትዋጉም በላቸው አለኝ። እኔም ተናገርኋችሁ እናንተ ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ አልሰማችሁም በትዕቢታችሁም ወደ ተራራማው አገር ወጣችሁ። በዚያም በተራራማው አገር ይኖሩ የነበር አሞራውያን ወጥተው ተጋጠሙአችሁ፥ ንብ እንደምታሳድድም አሳደዱአችሁ፥ እስከ ሔርማም ድረስ በሴይር መቱአችሁ። ኦሪት ዘዳግም 1፡41-44

እስራኤላዊያን ጠላቶቻቸውን ተዋግተው ወደ ከንአን መግባት በነበረባቸው ጊዜ አንወጣም አንዋጋም ብለው በእግዚአብሔር ትእዛዘ ላይ አመፁ፡፡

እግዚአብሔር በአመፃቸው ላይ ተቆጣ እና እንዲገስጻቸው ሙሴን ላከላቸው፡፡ እስራኤላዊያን እግዚአብሔር ደስ እንዳልተሰኘባቸው እና እንዳዘነባቸው ሲያውቁ አሁን እንወጣለን ጠላታችንን እንዋጋለን ብለው አቀዱ፡፡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት በመካካላችሁ አይደለሁም አትዋጉ ብሎ ተናገራቸው፡፡ በጠላቶቻችሁ ላይ የመውጣት ጊዜው አይደለም ብሎ የተናገራቸውን ትእዛዝ አልሰሙትም ቀጥለው አሞራዊያንን ለመግጠም ወደጦርነት ወጡ፡፡ ውጤቱም ሽንፈት ነበር፡፡

ከዚህ የእስራኤል ታሪክ እንደምንረዳው ንስሃ መግባት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ከንስሐ በኋላ እግዚአብሔርን ለማስደሰት በራሳችን የምንሄደው እርምጃ ትክክል እንዳልሆነ አንማራለን፡፡

እስራኤላዊያን ማድረግ የነበረባቸው ያለፈ አልፎዋል እግዚአብሔር አሁን ምን እንደሚለን እንሰማለን እንታዘዘዋለን በማለት ልባቸውን ለሚቀጥለው የእግዚአብሔር ትእዛዝ ማዘጋጀት ብቻ ነው፡፡

የእነርሱ በራሳቸው ጊዜ ለመዋጋት መውጣት አንዋጋም ለሚለው አመፅ ማካካሻ ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡ ያለፈው እግዚአብሔርን የመታዘዣ እድል አምልጦዋል፡፡ እስራኤላዊያን ሌላ እግዚአብሔርን የመታዘዣ እድል መጠበቅ አለባቸው እንጂ በራሳቸው ሌላን እድል መፍጠር አይችሉም፡፡

ንስሃ መግባት እግዚአብሔር አታድርግ ያለውን እሺ ጌታዬ አላደርግም ማለት እግዚአብሔር አድርግ ያለውን ደግሞ እሺ አደርጋለሁ ማለት ነው፡፡

ከዚህ ያለፈ ካለምንም የእግዚአብሔር ተጨማሪ ትእዛዝ ስለሰራነው ሃጢያት ማካካሻነት በራስ አነሳሽነት ለመካስ መሞከር ስህተት ውስጥ ይጨምረናል፡፡

በሰሩት ሃጢያት ተፀፅቶ በራስ አነሳሽነት ስህተትን በስህተት ለማስተካከል መሞከር ተጨማሪ ስህተተን መስራት ነው፡፡

ንስሃ እንደገባን እግዚአብሔርን ለመታዘዝ በተዘጋጀ ልብ ጌታ ሆይ አሁን ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ ብሎ መጠየቅ በቂ ነው፡፡

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

#ኢየሱስ #ጌታ #ንስሐ #አእምሮንማደስ #አሳብንመቀየር #መንገድንመቀየር #በረከት #ቤተክርስቲያን #መፅሐፍቅዱስ #ቃል #እግዚአብሔር #ክርስትና


 

No comments:

Post a Comment