Popular Posts

Sunday, August 20, 2023

ንስሐ መዞር ነው

 

በስህተት ወደ ምእራብ 100 ሜትር የተራመደ ሰው ወደ ምስራቅ ለመዞር መቶ ሜትር መራመድ አይጠበቅበትም፡፡ ወደ ምስራቅ ለመዞር የሚጠበቅበት መዞር ብቻ ነው፡፡

ንስሐን ከሚገባው በላይ ውስብስብ የምናደርገው መፅሃፍ ቅዱስ ስለንስሐ ያላለውን ስንል ነው፡፡

እግዚአብሔር ለመፈፀም የሚቻልን እንጂ የማይቻልን ነገር እንድናደርገው አያዘንም፡፡ ንስሐ መግባት ይቻላል፡፡ መመለስ ይቻላል፡፡ ንስሐ መግባት የማይቻል እና የማይደረስበት ረቂቅ ነገር አይደለም፡፡

ንስሐ ማለት የተራመድነውን ርቀት ያህል ተመልሶ መራመድ ስለሚመስለን ስለንስሐ ስናስብ እንደክማለን፡፡ ንስሐ ለመግባት እና ለመመለስ የተሳሳትንበትን ጊዜ ሁሉ እንደገና ወደተቃራኒው አቅጣጫ መድገምን የሚጠይቅ ስለሚመስለን አስቀድመን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡

ንስሐ የቀደመው ሐጢያታችንን ዋጋ ሁሉ ዋጋ መክፈል ስለሚመስለን ንስሐ ከመግባት ይልቅ በጥፋታችን መቀጠል እንመርጣለን፡፡

ንስሐ የቀደመውን መንገድ ትቶ ለእግዚአብሔር መንገድ እሺ ማለት ነው፡፡ በንስሐ ስለቀደመው ሃጢያታችን ዋጋ መክፈልን የሚያስተምር የተሳሳተ ሃይማኖት የአምልኮ መልክ እንጂ ክርስትና አይደለም፡፡

ንስሐ ለእግዚአብሔር ሃሳብ እሺ ማለት ነው፡፡ ንስሐ ከእግዚአብሔር ሃሳብ ጋር መስማማት ነው፡፡ ንስሃ እንደገና እግዚአብሔርን ለማስደሰት መወሰን ነው፡፡

ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች። እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ ትንቢተ ኢሳይያስ 1፡18-19

አቢይ ዋቁማ ዲንሳ Abiy Wakuma Dinsa

#ኢየሱስ #ጌታ #ንስሐ #አእምሮንማደስ #አሳብንመቀየር #መንገድንመቀየር #በረከት #ቤተክርስቲያን #መፅሐፍቅዱስ #ቃል #እግዚአብሔር #ክርስትና


No comments:

Post a Comment